የአይፎን ስልክን ልዩና ትርፋማ ያደረጉት ቴክኖሎጂዎች ምንድን ናቸው?

ስቲቭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የአፕል ኩባንያ መስራቹ ስቲቭ ጆብስ

ዳር 9. 2007 (እአአ) ዓለማችን ካፈራቻቸው ድንቅ ስራ ፈጣሪያን መካከል አንዱ ሰው ከዚህ በፊት ታይቶ ማይታወቅ ምርት ለዓለም አስተዋወቀ። በዓለም ታሪክ በጣም ትርፋማውን ምርት. . . አይፎን። ከቀናት በፊትም ይበልጥ የዘመነውን አይፎን ኤክስ የተሰኘ አዲስ ምርቱን ይፋ አድርጓል።

አይፎን የዓለማችንን ምጣኔ ሀብት ዝማኔ በብዙ መልኩ መቀየር ችሏል። አፕል የተሰኘው ኩባንያ ከአይፎን ምርቱ የሚያገኘውን ያህል ትርፍ ያህል በአለማችን ላይ ማግኘት የቻሉት ሦስት ኩባንያዎች ብቻ ናቸው።

የአይፎን ገበያ ላይ መዋል ዓለማችን ስማርት ፎን ወደተባለ የዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ዘመን እንድትገባ አደረጋት። የአይፎን ምርት ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ያልነበረ አሁን ግን የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ወደ መሆን የተጠጋ ቴክኖሎጂ ለመሆን በቅተቷል። አይፎን ከዘመናዊ ስልክነት አልፎ የሙዚቃውን፣ የማስታወቂያውን እንዲሁም የሶፍትዌር ገበያውን ማንቀጥቀጥ ችሏል።

እንግዲህ ከላይ የዘረዘርናቸው ስለ አይፎን የሚታወቁ የሚባሉትን እውነታዎች ነው። በጥልቅ ሲገባ ግን ስለ አይፎን የሚታወቀው ነገር እጅጉን ሊያስደንቆት ይችላል። ስቲቭ ጆብስን ጨምሮ የአፕል ኩባንያ መስራቾች እነ ስቲቭ ወዝንያክ፣ የጆብስ ምትክ ቲም ኩክ እንዲሁም ሰር ጆኒ አይቭ ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው ሚገባ ቢሆንም አይፎንን እውን ያደረጉ በርካቶች ግን ተረስተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አስቲ ራሳችንን እንጠይቅ. . . አይፎንን አይፎን ያደረገው ምንድነው? አስደናቂ ንድፉ፣ ለተጠቃሚ ምቹ መሆኑ፣ በሶፍትዌር እና በሀርድዌር አማካይነት ለጥቃቅን ነገሮች የሚሰጠው ትልቅ ቦታ? ለኛ ጎልቶ ከሚታየን በዘለለ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን ለአይፎን ታላቅነት ዋጋ ያበረከቱ ቴክኖሎጂዎችን አቅፏል. . . አይፎን።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዋ ማርያና ማዙካቶ አይፎንን ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚያስብሉ አስራ ሁለት ነገሮችን ታስቀመጥለች።

1. ጥቃቅን ማቀናበሪያዎች ወይም ማይክሮፕሮሰሰሮች

2. የማስታወሻ ቅንጣቶች ወይም ማይክሮ ቺፕሶች

3. ሃርድ ድራይቮች

4. ሊክዊድ ክሪስታል እየተባለ የሚጠራው ነገሮችን ማያ የፊትለፊት ገጽ

5. በሊቲየም ሀይል የሚሰሩ ባትሪዎች

እንግዲህ እኚህ ልንዳስሳቸው የምንችላቸው ወይም የምንመለከታቸው አካላት ናቸው። ወደ ተቀሩት ስንመጣ ደግሞ

6. ፋስት ፉርየር አልጎሪዝሞች፦ ይህ ቴክኖሎጂ ድምጽን፣ ብርሃንን እንዲሁም የራዲዮ ዌቭን ወደ ዲጂታል የሚቀይር ነው።

7. በይነ-መረብ ወይም ኢንተርኔት፦ዘመናዊ ስልኮችን በተለይ ደግሞ አይፎንን ያለ በይነ-መረብ ማሰብ እጅጉን ከባድ ነው።

8. ኤችቲፒፒ ወይም ኤችቲኤምኤል፦ ይህኛው ቴክኖሎጂ ለማንበብ ከባድ የሆኑ የኮምፒውተር ቋንቋዎችን ለማንበብ እንዲቀሉ አድርጎ ይቀይራቸዋል።

9. የተንቀሳቃሽ ስልክ አውታረ-መረቦች ወይም ሴሉላር ኔትዎርክ፦ ይህኛው ቴክኖሎጂ ያለ ገመድ እርዳታ በይነ-መረብ ወይም ኢንተርኔት እንድንጠቀም የሚያግዘን ነው።

10. አቅጣጫ መጠቆሚያ ወይም ጂ.ፒ.ኤስ

11. የአይፎን የሚነካ ገጽታ ወይም ተችስክሪን

12. ሲሪ፦ ሲሪ የተሰኘችው የሴት ድምጽ የተላበሰች አጋዠ መሳሪያ የአይፎን ልዩ ገጽታ ነች።

ሁሉም ከላይ የተገለጹት የአይፎን ገፅታዎች ተንቀሳቃሽ ስልኩን ዘመናዊ የሚያደርጉ ባህሪያት ናቸው። እኚህ ባህርያት ለአይፎን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮችም ይሰራሉ። አነዚህን ባህርያት በጥልቀት ያጠናችው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዋ ማርያና ማዙካቶ እንደምትናገረው ከሆነ አይፎን እዚህ ደርሶ ለማየት ብዙ ነገር እንደታለፈ ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, SHAUN CURRY

ለአይፎን እውን መሆን ከአፕል ኩባንያ መስራቹ ስቲቭ ጆብስ ይልቅ የአሜሪካ መንግሥት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ከላይ ከተጠቀሱት አስራ ሁለት የዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ባህርያት አብዛኛዎቹ በአሜሪካ መንግሥት እርዳታ የተሰሩ ናቸው።

በይነ-መረብ ወይም ኢንተርኔት እንደ ጎርጎሪዮሳውያን አቆጣጠር በ1960 ዓ.ም. በአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር የገንዘብ ድጋፍ ኮምፕዩተሮችን እርስ በርስ ለማስተሳሰር በሚል ነበር የተፈጠረው። አቅጣጫ መጠቆሚያ ወይም ጂ.ፒ.ኤስ ደግሞ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ መዋል የጀመረ እና በ1980ዎቹ (እአአ) ለሲቪል ማህበረሰብ ጥቅም አንዲበቃ የተደረገ ቴክኖሎጂ ነው።

ከዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ባህርያት ዋነኛው የሆነው በእጅ የመንካት ገጽታ ወይም ተችስክሪን የተፈጠረው በእንግሊዛዊው ኢንጅነር ኢኤ ጆንሰን በ1960ዎቹ ሲሆን ጆንሰን ስራውን የሰራው ለእንግሊዙ ኩባንያ ሮያል ራዳር ኢስታብሊሽመንት ነበር።

ለጠቅ ስንል ደግሞ 'ድመፀ ስርቅርቋን' ሲሪን እናገኛታለን።

አይፎን ከመፈጠሩ ሰባት ዓመት በፊት እንደ ጎርጎሪዮሳውያን አቆጣጠር 2000 ዓ.ም. የአሜሪካ መከላከያ ሰራዊት በመደበው ገንዘብ እንደ ሲሪ ያለች ቢሮ ውስጥ መከላከያ ሰራዊቱን የምታግዝ ድምፅ አሰራ። ከሰባት ዓመታት በኋላ ቴክኖሎጂውን የአሜሪካ መከላከያ ሰራዊት ለገበያ አቀረበው። ከዛም በ2010 ዓ.ም. አፕል ኩባንያ መሳሪያውን ይፋ ባልሆነ ዋጋ በመግዛት ለአይፎን አዋለው።

በሊቲየም ሀይል የሚሰሩ ባትሪዎች እንዲሁም ሊክዊድ ክሪስታል ማሳያዎችን ጨምሮ ሌሎችም ቴክኖሎጂዎች ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ናቸው። በሁሉም ቴክኖሎጂዎች ላይ ግለሰባዊ ልቀት ቢታይም በገንዘብ እና ሌሎች እርዳታዎች የአሜሪካ መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል።

እርግጥ የአሜሪካ መንግሥት አይፎንን አልሰራም፣ ፌስቡክን ወይም ጉግልን አልፈጠረም። ዛሬ ዓለም ጠዋት ማታ የሚጠቀማቸውን እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በግለሰብ ተሰርተው ለገበያ ቢቀርቡም፤ የመንግሥት የገንዘብ እርዳታ እና የአደጋ-መጋፈጥ አቅም ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock

ስቲቭ ጆብስ እጅግ የላቀ ችሎታ ያለው ሰው እንደሆነ የማይካድ ሀቅ ነው። ከእርሱ ፈጠራዎች መካከል አኒሜሽን ስቱድዮ ፒክሳር እየተባለ የሚጠራው እና በፊልሙ ዓለም ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው አንዱ ነው።

ከሚነካ ገጽታ ወይም ተችስክሪን እንዲሁም በይነ-መረብ ወይም ኢንተርኔት ፈጠራ ውጭም ቢሆን ሌላ ዓለምን የሚያስደንቅ ፈጠራ ሊኖረው ይችል ነበር። ግን እንደ አይፎን በተፅዕኖው ዓለምን ያዳረሰ ፈጠራ ይሆናል ብሎ ማሰብ ግን ከባድ ነው።