በኬንያ ሙስናና ዝርፊያን እየመከተ ያለው የኤም ፔሳ አብዮት

Image copyright AFP

እ.አ.አ. አቆጣጠር 2009 ዓ.ም። ሀምሳ ሶስት አፍጋኒስታውያን ፖሊሶች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው የተላከውን የጽሁፍ መልዕክት ሲመለከቱ አንድ የሆነ የተሳሳተ ነገር እንዳለ ገምተዋል።

ኤም-ፔሳ የተሰኘው ደሞዝን በተንቀሳቃሽ ስልክ የመክፈል የሙከራ ፕሮግራም አካል መሆናቸውን ቢያውቁም የደረሳቸው የገንዘብ መጠን ከዚህ በፊት ከሚያገኙት የላቀ ሆኖ በመምጣቱ አንድ የሆነ ሰው ስህተት እንደሰራ አልተጠራጠሩም።

ነገር ግን የደረሳቸው ትክክለኛው የገንዘብ መጠን ነበር። ከዛ በፊትም አሁን እንደደረሳቸው ዓይነት የገንዘብ መጠን ሊደርሳቸው በተገባ ነበር። ከሙከራ ፕሮግራሙ በፊት ደሞዛቸውን በጥሬ ገንዘብ ነበር የሚቀበሉት። በዚህም ሂደት እስከ ሰላሳ በመቶ የሚሆን ገንዘብ ያጡ ነበር።

በዚህ ለውጥ ትክክለኛውን ወርሃዊ ደሞዛቸውን ማግኘት የቻሉት ፖሊሶቹ እጅጉን ተደሰቱ። የሚደርሳቸው ድርሻ የቀረባቸው ሞሳኝ አዛዦቻቸው ግን ፊታቸው ጠቆረ።

አፍጋኒስታን ገንዘብን በተንቀሳቃሽ ስልክ በማንቀሳቀስ ሂደት ምጣኔ ሀብታቸው እጅጉን ለውጥ ካሳዩ አዳጊ ሀገሮች መካከል አንዷ ነች።

Image copyright Getty Images

ይሄንን ቴክኖሎጂ መጀመሪያ ተግባራዊ ያደረግችው ሀገር ጎረቤት ኬንያ ነች። ሀሳቡን ያቀረቡት ደግሞ ቮዳፎን የተሰኘው የሞባይል ኔትወርክ አቅራቢ ድርጅት ሰራተኛ የሆኑት ኒክ ሂዩጌስ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ ነበር። መነሻ ሀሳባቸውም አነስተኛ ብድር አቅራቢዎችን ማገዝ ነበር።

ከታዳሚዎቹ መካከል ደግሞ የእንግሊዙ ዲ.ኤፍ.አይ.ዲ ሰራተኛ ይገኙበታል። ሰውየም ለሀሳቡ መሳካት ዲ.ኤፍ.አይ.ዲ አንድ ሚሊዮን ዩሮ እንደሚበጅት ተናገሩ። እናም የሙከራ ትግበራው በኬንያ ተጀመረ።

ከታሰበው በላይ

አነስተኛ ሱቆች እንደ ባንክ ቅርንጫፍ ያገለግላሉ። ገንዘብዎን ማስቀመጥ ይችላሉ። ወይም በተንቀሳቃሽ ስልክዎ አማካኝነት ጥሬ ገንዘብ መቀበል ይችላሉ። ለወዳጅ ዘመድዎ ገንዘብ ማስተላለፍም በጣም ቀላል ነው። ይሄን ሁሉ ተግባር ለመፈጸም የሚያስፈልጎት ተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ ነው። የበይነመረብ ወይም ኢንተርኔት አገልግሎትም አይጠይቅም።

በስምንት ወር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮን የሚቀጠሩ ኬንያውያን ኤም-ፔሳ የተሰኘውን ይህን አገልግሎት ለመጠቀም ተመዘገቡ። አሁን ላይ ወደ ሀያ ሚሊዮን የሚሆኑ ኬንያውያን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይነገራል። አገልግሎቱ ከኬንያን ጥቅል ሀገራዊ ምርት ወይም ጂዲፒ ግማሽ በመቶ የሚሆነውን ይይዛል።

አገልግቱን የሚሰጡ አነስተኛ ሱቆች በሀገሪቱ ከሚገኙ ጥሬ ገንዘብ መቀበያ ማሽኖች በመቶ እጥፍ በቁጥር ይበልጣሉ። በጣም አነስተኛ ገቢ የሚያገኙ ኬንያውያን ጭምር አሁን ላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ናቸው።

አገልግሎቱ በኬንያ ያገኘው ስኬት

ኤም-ፔሳ በኬንያ ስኬት ያገኘበት ዋነኛ ምክንያት የባንኮች እና የኔትወርክ አቅራቢ ድርጅት ተቆጣጣሪዎች ያሳዩት ቀናነት እንደሆነ ይነገራል። አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ከሆነ አብዛኛው ኬንያውያን ስለ አገልግሎቱ የሚወዱት አንድ ነገር ቢኖር በቀላሉ እርስ በርስ ገንዘብ መላላካቸው ነው።

ከዚያ በላይ ግን ሁለት ጥቅሞች ጎልተው ይታያሉ። ሙስናና እና ዝርፊያ ማስወገድ።

አንድን አሽከርካሪ መንገድ ላይ አስቁሞ ገንዘብ መቀበል የፈለገ የትራፊክ ፖሊስ አሽከርካሪው ጥሬ ገንዘብ ካልያዘ ምንም ማድረግ አይችልም። ምክንያቱም የኤም-ፔሳ መለያ ወይም አካውንት የትራፊክ ፖሊሱን ስም እና ስልክ የመሳሰሉ መረጃዎችን ይይዛል። ይሄንን ደግሞ አሽከርካሪው እንደ ማስረጃ ሊጠቀም ይችላል።

እንደ ኬንያ መንግስት ዕቅድ ከሆነ በቀጣይ በህዝብ ትራንስፖርቶች ላይ ኤም-ፔሳን መጠቀም ግዴታ ይሆናል።

ቴክኖሎጂው ሙስናና ዝርፊያን ከመከላከሉም በላይ መንግስት የታክስ ሄደቱን በስርዓት እንዲቆጣጠርም ያደርገዋል። ይሄም የኤም-ፔሳ አገልግሎት ቀጣዩ ትልቅ ጥቅም ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል። ከሙሰኛ የፖሊስ አዛዦች እስከ ታክስ የማይከፍሉ የታክሲ አሽከርካሪዎች ገንዘብን በተንቀሳቃሽ ስልክ መያዝ ቴክኖሎጂ ምክንያት ለህጉ ተጘዘዚ ይሆናሉ ማለት ነው።