'ጉግል ያርጉት' ዓለምን የቀየረው የሁለቱ ተማሪዎች ፕሮጀክት!

Image copyright Getty Images

ልጅ፦ "አባዬ አንተ ብትሞት ምን ይፈጠራል?"

አባት፦ "እኔ ምን አውቄ ልጄ። ስንሞት ምን እንደሚፈጠር ማወቅ የሚችል ይኖራል ብለህ ነው?። ለምን ጉግል አታረገውም?"

እርግጥ ከሞት በኋላ ሕይወት ይኑር አይኑር በእርግጠኝነት ሊነግረን ባይችልም ጉግል የሚለው ቃል በንግግራችን ውስጥ መስረጽ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል።

ከጉግል በፊት ነገሮችን በይነ-መረብ ወይም ኢንተርኔት ላይ መፈለግ ምን ያህል ከባድ እንደነበረ እንድንረሳ ያደረገን ጉግል በካሊፎርኒያ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪ ፕሮጀክትነት ተነስቶ አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ ሁለት አስርት ዓመታት ፈጅቶበታል።

የጉግል ፈጣሪዎቹ ሌሪ ፔጅ እና ሰርጌይ ብሪን የመጀመሪያ ዕቅዳቸው የመፈለጊያ መሳሪያ መስራት አልነበረም። ፕሮጀክታቸው ምሁራዊ መነሳሳትን ይዞ ነበር የጀመረው።

በትምህርት ዓለም አንድን የታተመ ጽሁፍ እንደ ታማኝ ምንጭ መጥቀስ የተለመደ ነው። ይህንን ያስተዋሉት ፔጅ እና ብሪን ሁሉንም ጽሁፎች የሚያስተሳስር መረብ መዘርጋት ቢችሉ የጽሁፎቹን ታማኝነት በደረጃ ለማስቀመጥ እንደሚችሉ ተረዱ።

ነገር ግን ስልተ ቀመሩን ወይም አልጎሪዝሙን ሲያጤኑት በጣም ሰፊ የሆነ የመፈለጊያ መረብ መፍጠራቸውን አስተዋሉ። ወዲያውኑ ኢነቨስተሮች አይኖቻቸውን ወደ ጉግል ፈጣሪዎች ላይ መጣል ጀመሩ። እናም ጉግል ከተማሪ ፕሮጀክትነት ወደ ግል ኩባንያነት ተሸጋገረ።

ነገር ግን በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ፔጅ እና ብሪን ብዙ ገንዘብ ፕሮጀክታቸው ላይ አፍስሰው ነበር። መልሰው ያግኙት ወይም አያግኙት ግን እርግጠኛ አልነበሩም።

ፍጥነት እና ግልጽነት

እ.አ.አ በ2001 ዓ.ም ጉግል 'ፔይ ፐር ክሊክ' የተባለ ሥርዓት በመዘርጋት ገንዘብ ማግኛ መላ ዘየደ። ማስታወቂያ አስነጋሪዎች አንድ ግለሰብ ማስታወቂያቸውን በከፈተ ቁጥር ለጉግል ገንዘብ ይከፍላሉ። ለማስታወቂያ አስነጋሪዎች መላው በጣም ጠቃሚ ሆኖ ተገኘ። ምን ያህል ሰው ማስታወቂያቸውን እየተመለከተ እንደሆነም ማወቅ አስቻላቸው።

ይህንን ተከትሎም መገናኛ ብዙሃን አዲስ የቢዝነስ መላ ይዞ መምጣት ላይ ትኩረታቸውን አደረጉ። ይህም ጉግል ካመጣቸው ምጣኔ ሀብታዊ ተጽዕኖዎች እንደ አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል።

የጠቃሚ የፍለጋ መላ ወይም 'ፋንክሽናል ሰርች ቴክኖሎጂ' መፈጠር ደግሞ የራሱን እሴት ይዞ መጣ፤ የሰዎችንም ሕይወት መቀየር ጀመረ።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ጉግል ፍለጋ አንድ ሰው ቤተ-መጻሕፍት ሄዶ የሚፈልገውን ለማግኘት ከሚያጠፋው ጊዜ ሦስት እጥፍ ያነሰ ነው። ወደ ቤተ-መጻሕፍት ለመሄድ የሚፈጀው ጊዜ ሳይቆጠር ማለት ነው። በተመሳሳይ መልኩ ስራን በታተመ ወረቀት ከመፈለግ ሦስት እጥፍ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ጉግል ላይ መፈለግ ይቻላል።

ተፈጥሯዊ የበላይነት

ማንኛውንም ነገር መፈለግን እውን ያደረገው ጉግል የበይነ-መረብ ገበያው እንዲጧጧፍ ትልቅ በር ከፍቷል። በተለይ ደግሞ ውሱን እና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ፈላጊዎች የሚፈልጉትን ነገር እንደልብ እንዲያገኙ አስችሏል። ሥራ ፈጣሪዎችም ደንበኞቻቸውን በቀላሉ ማግኘት እዲችሉ አግዟል።

ጉግል የበይነመረብ ፍለጋውን ዘጠና በመቶ የተቆጣጠረው ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ንግዶች በጉግል አስተማማኝ ፍለጋ ላይ ሀሳባቸውን ጥለዋል። (ዕድሜ ለጉግል) ሰው ርቆ መጓዝ ትቶ ፍለጋውን ከቤቱ እያጧጧፈው ነው።

ነገር ግን በጉግል ፍለጋ አንደኛ ደረጃ ላይ ያለ ኩባንያ ለቀጣዩ ወይም ለመጭው ኩባንያ ነገሮችን እንዲከብዱ አድርጓል። ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ፈላጊ ያላቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች ሁሌም የፍለጋውን 'ተፈጥሯዊ የበላይነት' ስለሚይዙት ነው።

ጉግል በዓለማችን ካሉ የመረጃ ቋቶች ከፍተኛ ድርሻ በመያዝ ገበያውን ይመራል። ይህም የኩባንያው መጻኢ ዕጣ ፈንታ ብሩህ እንደሆነ እና ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ዕውቀት እንዳከማቸ ጠቋሚ ነው።