ሰው ሰራሽ ልህቀት፦ ከመፃኢ የዓለም ፈተናዎች አንዱ! ሌሎቹስ?

Image copyright Joe Raedle
አጭር የምስል መግለጫ የአየር ንብረት ለውጥ የዛሬ አረባ ዓመት የዓለማችን አበይት የራስ ምታት አንደሚሆን ይገመታል።

እ.አ.አ በ2050 እጅጉን የሚያሳስቡን ነገሮች ምን ይሆኑ? እርግጥ እቅጩን መናገር ይከብዳል። ቢሆንም አሁን እየሄድንበት ካለው መንገድ በመነሳት የዓለማችን ሳይንቲስቶች አስርቱ አበይት ፈተናዎችን አስቀምጠዋል።

1. የሰው ልጅን ዘረ-መል ማሻሻል

በሳይንሳዊ አጠራሩ 'ክሪስፐር' እየተባለ የሚጠራው መላ የሰው ልጅን ዘረ-መል ወይም ዲኤንኤ በማሻሻል ካንሰርን የመሳሰሉ በሽታዎች የሚከላከል ትውልድ ለመፍጠር የሚተጋ ዘዴ ነው። ሀሳቡ ባልከፋ። ነገር ግን ዘዴውን ያሰበውን ሳያሳካ ቀርቶ በዚህ ንድፍ መሰረት የተወለዱ ልጆች ልቀት ወይም ኢንተለጀንሳቸው እንዲሁም የሰውነት ቅርጻቸው ከተለመደው ወጣ ያለ እንዳይሆን ያሰጋል። ነገሩ ትልቅ አደጋ ነው ብሎ ለማሰብ ጊዜው ገና ቢሆንም መዘዙ የከፋ ሊሆን ስለሚችል መጠንቀቅ አለብን ባዮች ናቸው ሳይንቲስቶቹ።

''ቴክኖሎጂው በፍጥነት እያደገ ባለበት በዚህ ዘመን ስለመዘዙ የምናስብበት ጊዜ ዘሁን አይደለም የሚባለው ነገር እርባና ቢስ።" ነው ይላሉ በኒውዚላንድ ዌሊንግተን ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግባር ፕሮፌሰር የሆኑት ኒኮላስ አጋር።

2. ዕድሜው የገፋ ትውልድ

ከጊዜ ወደጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው የዓለማችን ሕዝብ እዚች ምደር ላይ የሚኖርበት የዕድሜ ገደብም እያሻቀበ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ። "ኧረ ዕድሜ ጨምሮ ጨማምሮ ይስጠን" ሊሉ ይችላሉ። አሳሳቢው ጉዳይ ወዲህ ነው። ወደ እርጅና ዘመን የሚሻገሩ ሰዎች እንክብካቤ እንደሚያሻቸው የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። አንድ ጥናት እንደሚያሳው መቶ ዓመትን የሚሻገሩ ሰዎች ቁጥር አሁን ካለበት አምስት መቶ ሺህ ሀምሳ እጥፍ በማደግ እ.አ.አ. በ2100 ሃያ ስድስት ሚሊዮን ይደርሳል። ይህም ለኣዛውንቶች የሚሆን ከባቢ አየር እንድንፈጥር ግድ ይለናል። እንደውም ጃፓን ሮቦቶችን በዚህ መስክ ለማሰማራት ዕቅድ ላይ ነች።

3. የሚዋጡ ከተሞች

ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ብዙ ለውጦችን ያየንበት ዘመን ነው። የጎርፍ አደጋ የዕለተ ዕለት ክስተት እየሆነ ወደ መምታት ደርሷል። የአየሩ ሁኔታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀያየረ መጥቷል። በዚህ ምክንያትም የአሜሪካዋ ማያሚ ከተማ ሕንጻዎች ሲገነቡ ምድር ቤቱን ከፍ አድርገው እንዲገነቡ ትዕዛዝ አውጥታለች። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ እንደባለሙያዎች ትንበያ ውቅያኖስ እና ሀይቅ አካባቢ የሚኖሩ ከተሞች፥ ደሴቶች እንዲሁም ባንገላዲሽን የመሳሰሉ ዝቅ ባለ ስፍራ የሚገኙ ከተሞች መጥፍያቸው ሩቅ አይደለም።

የሚሆነው ባይታወቅም ወደፊት የስደት አንዱ መንስኤ ይሄ ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል።

4. የማህበራዊ ሚድያ ዝግመተ ለውጥ

ማህበራዊ ሚድያ የእርስ በርስ መገናኛ መንገዳችንን መቀየር ከጀመረ እነሆ አስር ዓመት ሞላው። ከዛም አልፎ ዋነኛ የዜና ምንጭም ሆኖ መቆጠር ከጀመረም ሰንበትበት ብሏል። ይሄም ሰዎችን ለውሸት ዜና እንዲጋለጡ አርጓዋቸዋል። ሰዎች የዜና ምንጫቸውን ማሕበራዊ ሚዲያ ካደረጉ በጊዜ ሂደት ዕውቀታቸውም ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚያመጣም ይተነበያል። ማህበራዊ ሚድያው ካመጣቸው አሉታዊ ተጽዕኖዎች ሳይበር ቡሊይንግ ወይም በማሕበራዊ ሚድያ የሚደርስ ጥቃት ደግሞ ሌላኛው ነው።

ከተፈጠረ ገና አስራ ሶስት ዓመት የሆነው ፌስቡክን ጨምሮ ማህበራዊ ሚድያዎች በሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት ምን ሊያጋጥማቸው እንሚችል መተነቤይ ቢያዳግትም ቀላል ፈተና እንደማይጠብቅን ግን እሙን ነው።

Image copyright AJ PHOTO/SCIENCE PHOTO LIBRARY
አጭር የምስል መግለጫ ሳይበር ቡሊይንግ ወይም በማሕበራዊ ሚድያ የሚደርስ ጥቃት አንዱ የማህበራዊ ሚድያ አሉታዊ ተጽዕኖ።

5. ጄኦፖለቲካዊ ውጥረት

የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ጥቃት፥ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች፥ በሰው ሀገር ምርጫ የሚገቡ የቤይነመረብ ጠላፊዎች ወይም ሀከሮች ጉዳይ፥ የታላቋ ብሪታንያ ከአውሮፓ ሕብረት ራሷን ማግለል፥ እያደገ የመጣው የብሔርተኝነት አስተሳሰብ. . . እኚህ ሁሉ እ.አ.አ. 2016ን ጨምሮ በያዝነው 2017 ዓ.ም አጀንዳ የነበሩ ኹነቶች ናቸው። ታዲያ በዚህ ከቀጠለ የኣለማችን ጄኦፖለቲካዊ ውጥረት መርገቢያው ምን እና መቼ እንደሆነ ለማሰብ ይከብዳል።

6. የተሽከርካሪ ነገር

እያደገ በመጣው የከተሜነት ዑደት ውስጥ እንደ ጥይት የፈጠኑ ባቡሮች እንዲሁም ሃይፐርሉፕ እየተባሉ የሚጠሩ በጣም ፈጣን መጓጓዣዎችን ማየት እየተለመደ መጥቷል። ነገር ግን መኪና ቦታውን የሚለቅ አይመስልም። እንደውም በሚቀጥሉት ጥቂት አስርት ዓመታት የመኪኖች ቀጥር እየጨመረ እንደሚመጣ ይታሰባል።

አሽከርካሪ አልባ መኪኖችም ቁጥር እጀጉን በፍጥነት እያደገ ነው። መካከለኛ ደረጃ ያለው ማሕበረሰብ እየሰፋ በመታባት ቻይና እና መሰል ሀገራት አሽከርካሪ የመጠቀም ፍለጎት እጅጉን አሻቅቧል። አደጋ የማይበዛበት፥ እንዲሁም በካይ ያልሆነ የመንገድ ስርዓት እንዴት ይዘርጋ የሚለው ደግሞ ሌላው የዓለማችን መጻኢ ራስ ምታት ነው። የአሽከርካሪ አልባ መኪኖች ነገር እንዳለ ሀኖ።

Image copyright VCG

7. የተፈጥሮ ሀብታችን

የ21ኛው ክፍለ ዘመን መለያ የሆኑት የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንዳቻው እንኳ ያለ ተፈጥሮ ሀብት እገዛ እውን መሆን ባልቻሉ ነበር። አንድ ዘመናዊ ስልክ በውስጡ እስከ ስልሳ የሚሆኑ ከተፍጥሮ ሀብት የተሰሩ ክፍሎች እንዳሉት ልብ ይሏል። እየተመናመኑ ከመጡ የዓለማችን ተፈጥሯዊ ሀብቶች ዘጠና በመቶውን የያዘችው ቻይና ያሏት ምዕድኖች በሚቀጥሉት ሁለት አስርት ዓመታት ሊጠፋ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። በምን ሊተኩ እንደሚችሉ ግን እስከ አሁን አልታወቀም።

8. ሌላ ዓለም ማመቻቸት

ታዋቂው የፊዚክስ ምሁር ስቴፈን ሀውኪንግ ሰዎች ሌላ ዓለም በቶሎ ካላመቻቹ ነገሮች እንዳልሆኑ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃል። የውጭኛው ዓለም ሙሉ በመሉ የምንተማመንበት ባይመስልም ፊት የምንነሳው ጉዳይ እንዳልሆነም ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። አሁን ላይ የሕዋ ኩባንያዎች እና ቢሊየነሮች ብቻ የሚረግጡት የሚመስለን ሌላኛው ዓለም ወይም ሕዋ ወደፊት ለሁሉም ተደራሽ እንደሚሆን ይገመታል። ያን ጊዜ የመጓጓዥ ነገር፥ ደህንነታችን እንዲሁም ዲፕሎማሲ አሳሳቢ ጉዳዮች እንደሚሆን ኑ ግልጽ ነው።

9. የሰው ልጅ ጭንቅላት አቅም

ቡናም ሆነ ጠንከር እንደ ሞዳፊኒል ያሉ ነገሮች በመውሰድ ጭንቅላትን ማገዝ የተለመደ ነገር። ከዛም በዘለለ ያደጉ የሚባሉ ሀገራት ዘመናዊ ስልኮችን እንደ ውጫዊ መረጃ ማስቀመጫ በመጠቀም ጭንቅላታቸውን ያግዛሉ። ቤተ-ሙከራዎች አሁን ላይ በፍጥነት እንድናስብ የሚያግዙን እንዲሁም ትኩርታችንን እንድንቆጣጠር የሚረዱ መድሃኒቶችን በማምረት ላይ ናቸው። ጥያቄው እነኚህን መድሃኒቶች የመግዛት አቅም የሌላቸው ሰዎች ምን ያደርጋሉ የሚለው ነው። ከዛም አልፎ የስነ-ምግባር ጥያቄውም ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

10. ሰው ሰራሽ ልቀት

መጪውን ዓላሚው ሬይ ኩርዝዌል እንደሚያምነው ሰው ሰራሽ ልህቀት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወደፊት ከተፈጥሯዊው ልህቀት በብዙ እጥፍ በመብለጥ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይደርሳል። እርግጥ አሁን ጊዜው ለጋ ቢሆንም ስለወደፎቱ ማሰብ እንደማይጎዳ ግን ብዙዎች ይስማሙበታል። ሰው ሰራሽ ልህ

ቀት ለብዙ ነገሮች እንዲጠቅም ሆኖ ከመሰራቱ ባለፈ ባልሆነ መንገድ ተጉዞ የሰው ልጅ አደጋ ላይ እንዳይጥል ማስጋቱ ግን አልቀረም።