አሳንሰር እንደ ሕዝብ ማመላለሻ!

Image copyright Getty Images

አሳንሰሮችን እንደ ሕብ ማመላለሻ ቆጥረዋቸው ያውቃሉ? አውነታው ግን ያ ነው። አሳንሰሮች የሕዝብ ማመላለሻ ናቸው። በመቶ ሚሊዮን የሚቀጠሩ ሰዎች በየቀኑ ያጓጉዛሉ። ይህን በማገናዘብ ይመስላል ቻይና በአንድ ዓመት ብቻ ወደ ስድስት መቶ ሺህ የሚሆኑ አሳንሰሮችን ለጥቅም ያዋለችው።

ቡረዠ ዱባይን ወይም የቺካጎውን ሲርስ ማማን የመሳሰሉ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች መሬት ላይ ማንጠፍ ቢቻል እና በዙሪያው የመኪና ማቆምያ ስፋራ ቢገነባ ብለን እናስብ። ለቢሮ ግልጋሎት የሚውል ትልቅ ከተማ እንደምናገኝ አያጠራጥርም። በጣም ብዙ ሰዎች በተወሰነ ስፍራ ወይም በአንድ ትልቅ ህንጻ ላይ በአንድ ጊዜ መስራት እና መንቀሳቀስ እንዲችሉ ካደረጉ ቴክኖሎጂዎች መካከል አሳንሰር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

እ.አ.አ. በ1743 የኖረው ግሪካዊው አርኪሜዴስ የመጀመሪያውን አሳንሰር እንደገነባ ይታመናል። አሳንሰሩም ሉዊ አስራምስተኛ በድብቅ የሚገናኛትን ውሽማውን ለማየት የሚጠቅመበት እንደነበር ይነገራል። በአስፈላጊው ጊዜ ገመዱን በመጎተት የሚሰራ ነበር የዛኔው የአርኪሜዴስ አሳንሰር።

እንግሊዛውያኑ የኢንዱስትሪ አብዮተኞች ማቲው ቦልተን እና ጄምስ ዋት በእንፋሎት ሃይል የሚሰራ አሳንሰር ከመፍጠራቸው በፊት በሃንጋሪ፥ በቻይና እንዲሁም ግብጽ የነበሩ አሳንሰሮች በእንስሳት እገዛ ነበር የሚንቀሳቀሱት።

ደህንነት

ነገር ግን እነዚህን አሳንሰሮች ደህንነታቸውን ተማምኖ ህንጻዎች ላይ መጠቀም ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ግልጽ ነበር። በጣም አሳሳቢ ነገር የነበረው የአሳናሰሮቹን ደህንነት በኣሳማኝ እና በሚታይ መልኩ ማስጠበቅ ነበር።

እ.አ.አ. በ1853 ዓ.ም. በኒው ዮርክ ከተማ በተደረገ ትዕይንት ኤሊሻ ኦቲስ የተባለ ግለሰብ ለታዳሚያን አንድ ነገር ማሳየት ፈለገ። በሁለት ግንቦች መሃል በሆነው አሳንሰር ላይ የቆመው ኦቲስ ከጀርባው የሞት ቅጣት ለመፈጸም የተዘጋጀ የሚመስል ሰው መጥረቢያ ይዞ ቆሟል። ከዛም ኦቲስ ቆሞበት የነበረውን አሳንሰር ገመድ በመጥረቢያው ቆረጠው። ኦቲስ ወደ ታች ሲምዘገዘግ ሚዛኑን እንዲጠብቅለት ያስቀመጠው መሳሪያ ወደ ላይ ተስፈነጠረ። ኦቲስም በድንጋጤ እያዩት ለነበሩ ታዳሚዎች ሁሉም ሰላም መሆኑን ነገራቸው። ኦቲስ የአሳንሰር ፍሬን በመስራት ቴክኖሎጂው አንድ እርመጃ እንዲገፋ አደረገው።

ከዛ በኋላ የከተሞች የእድገት ቅርጽ በጣም ለየት ያለ መልክ መያዝ ጀመረ። ዕድሜ አሳንሰርን ለፈጠረው ሳይሆን የአሳንሰር ፍሬን ለፈጠረው ኦቲስ።

Image copyright Alamy

የአሳንሰር ቴክኖሎጂ ከብረት እና ኮንክሪት ቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር አንድ ላይ መመንጠቅ ጀመረ። ምክንያቱ ደግሞ ረጃጅም ህንጻዎች በብረት እና ኮንክሪት ሀይል መስራት መጀመራቸው ሲሆን ብዛት ያላቸው ሰዎችንም በተወሰነ ስፍራ መያዝ እንዲቻል ምክንያት ሆኑ።

አሳንሰር እና ከምድር በታች ያሉ አንደርግራውንድ ቤቶች የአሜሪካዋ ማንሃታን ከተማ መገለጫዎች ናቸው። በሰማይ ጠቀሶቹ ህንጻዎች ላይ በአንድ ጊዜ ብዙ ሰው መስተናገድ መቻሉ ከተማዋን በጣም ዘመናይ ያደርጋታል። ከማንሀታን ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ ሰማንያ በመቶ የሚሆኑት ምድር ለምድር በእግራቸው ወይም በብስክሌት ነው ወደስራ ቦታቸው የሚሄዱት። ይህ አሃዝ ከጠቅላላ የአሜሪካ አሃዝ ጋር ሲነጻፀር አስር እጅ የበለጠ ነው።

ጥቃቅን ተዓምራት

ባቡር ወይም ባስ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ካለንበት ቢደርሱልን ደስተኛ ልንሆን እንችላለን። አሳንሰር ለሃያ ሴኮንድ ሲዘገይብን ግን ሊያበሳጨን ይችላል። ብዙ ሰዎች አሳንሰር ሲጠቀሙ ፍርሀት ሊውጣቸው ይችላል። ነገር ግን አሳንሰሮች ከተንቀሳቃሽ ደረጃዎች ወይም ኤስካሌተሮች አስር እጥፍ የበለጠ ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው።

አሁን አሁን ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች በቀጭን ገመድ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም በኮምፒውተር እገዛ የሚሰሩ አሳንሰሮችን መጠቀም ጀምረዋል። ከዛም ባለፈ አሳንሰሮች በተፈጥሯቸው ሀይል ቆጣቢ ናቸው። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት አጅግ ቀለል ያለ ክብደት ያላቸው እና ብዙ ሀይል የማይወስዱ መሆናቸው ነው።

የኒው ዮርከ ከተማ መለያ የሆነው ኢምፓየር ስቴት ህንጻ 550 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ የህንጻውን የካርበን ልቀት ለመቀነስ እንቅስቃሴ ጀምሯል። ከዕቅዱ አንደኛው ደግሞ አሳንሰሮቹን በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሀይል እንዲሰጡ ማድረግ ነው።

አሳንሰርን እንደ ቀልድ ብናየውም ለዓለማችን እጅግ ጥቅም በመስጠት ላይ ያለ ቴክኖሎጂ ነው። በየዓመቱ ቢሊዮኖችን የሚያስተናግዱት አሳንሰሮች ከተፈጥሮ ጋር በመስማማት ስራቸውን ቀጥለዋል።