የ21ኛው ክፍለ ዘመን ነዳጅ. . . ውሃ!

Image copyright Getty Images

የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ነዳጅ እየተባለ ይጠራል. . . ውሃ። የውሃ አቅርቦት የዓለማችንን መፃኢ ዕጣ ፈንታ እንደሚገለባብጠው ይነገራል። በሰላማዊ ወይም ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ የዓለም ህዝቦች ለውሃ አቅርቦት ይፋለማሉ።

ለመኖር ወሃ ያስፈልገናል። እሱ ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ውሃ ከዛ አልፎ የአንድን ሀገር ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ሊገታው ወይም ደግሞ ሊያስመነድገው ይችላል። ከግብፅ እስከ ብራዚል ብንሄድ ታሪክ የሚነግረን ይሄንን ነው።

አንዳንድ የውሃ አካላት የሀገራትን ድንበር ገደብ ሲወስኑ ሌሎች እንደ ወንዝ እና ሀይቅ የመሳሰሉ የውሃ አካላት ሁለት እና ከዚያ በላይ ሀገራት ይጋሯቸዋል። የናይል ወንዝ ብቻውን ደርዘን የአፍሪቃ ሀገራትን ያካልላል።

ባለሙያዎች እንደሚስማሙት ከሆነ ሰዎች ለውሃ አቅርቦት መንገድ አበጅተው ባይሆን ኖሮ ዓለማችን ሰላም አልባ ትሆን ነበር። ለዚህም ነው በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ዓለማችን ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ ካልተጠቀመች ነገሮች ባልታሰበ መልኩ ሊጓዙ ይችላሉ የሚሉት የዘርፉ ባለሙያች። በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ከሌላው ጊዜ በበለጠ የንፁህ ውሃ ምንጮች እየደረቁ መጥተዋል። የአየር ንብረት ለውጥ፥ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፥ እንዲሁም እያደገ ያለው ብሔርተኝነት የሰዎችን እርስ በርስ ሰላማዊ ግንኙነት አየፈተነው ይገኛል። በዚህ በኩል ደግሞ የዓለማችን የውሃ ፍላጎት እ.አ.አ. ከ2000 እስከ 2050 ባሉት ዓመታት በ55 በመቶ እንደሚያድግ ይገመታል።

የውሃ ነገር

ውሃ በዓለም ፖለቲካ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የቅርብ ጊዜ ጉዳይ አይደለም። ከጥንት ጀምሮ የነበረ እንጂ። ብዙ ጊዜ የወንዝ መነሻ እና ከፍታ ቦታ ላይ የሚገኙ ሀገራት በታችኞቹ ሀገራት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። እነዚህ የዓለማችን ክፍሎች ደግሞ ብዙ ጊዜ ውጥረት የነገሰባቸው ናቸው። በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኘው የዮርዳንስ ወንዝ ፍልስጤም፥ ዮርዳኖስ እና እስራኤልን ጨምሮ በአካባቢው ለሚገኙ በርካታ ሀገራት የውሃ ምንጭ ነው።

ኢትዮጵያ እና ግብፅ ደግሞ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ማብቂያውን በግብፅ በኩል ሜዲትራንያን ውቅያኖስ ላይ ባደረገው ኣባይ ወይም በናይል ወንዝ ጉዳይ ለዘመናት ሲጎነታተሉ ኖረዋል። እ.አ.አ. በ2015 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እና ግብፅ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ትልቁ እንደሚሆን በሚጠበቀው 'በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ' ዙሪያ እሰጥ እገባ ውስጥ ገብተው ነበር። ሀገራቱ ፍትሀዊ የውሃ ክፍፍል የሚያረጋግጥላቸውን ስምምነትም እስከመፈረም ደርሰዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ማሌዢያ እና ሲነንጋፖር ከዘጠና ዘጠኝ ዓመታት በፊት የፈረሙት ስምምነት ጆን ወንዝን በፍትሃዊ መልኩ ለመጠቀም የተስማሙበት ሰነድ ነው። የሃይድሮ ፖለቲካ ምሁር የሆኑት ዜንያ ታታ እንደሚናገሩት "ዕድሜ ለጆን ወንዝ ሲንጋፖር ዛሬ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ሀገራት አንዷ ለመሆን በቅታለች።"

• ኢትዮጵያ እና ግብፅ በአባይ ጉዳይ

በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኝ ፓሲፊክ የተባለ ተቋም የለቀቀው መረጃ እንደሚጠቁመው ከውሃ ጋር በተያያዘ ከክርስቶስ ልደት በፊት 2000 ዓ.ዓ. አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለማችን በርካታ ግጭቶች ተነስተዋል። እና እንዴት አድርገን ነው ባለንበት ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ፍትሃዊ የውሃ ሀብት ክፍፍልን ማረጋገጥ የምንችለው? የዚህ ጥያቄ መልስ የውሃ ሀብት ካላቸው ሀገራት ይልቅ ውሃ እና ምግብ አምርተው ወደሌሎች ክፍለ ዓለማት የሚልኩ ሀገራት ጫንቃ ላይ ይወድቃል።

የውሃ ሀብት ክፍፍል

"ስለ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ውሃ ስናወራ ሶስት ነገሮችን ከግምት ማስገባት ይኖርብናል" ይላሉ የኦሬጎን ዩኒቨርሲቲ የመልክኣ ምድር ፕሮፌሰሩ አሮን ዎልፍ።

"የመጀመሪያው ጉዳይ የውሃ እጥረት ነው። የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት ልክ እንደ ኤች አይ ቪ እና ወባ በርካቶችን ሊቀጥፍ ይችላል። ሁለተኛው ደግሞ አሱን ተከትሎ የሚመጣው ፖለቲካዊ ቀውስ ነው። ለምሳሌ በሶሪያ ድርቅ ባስከተለው ጉዳት በርካቶች ፈልሰዋል፥ የምግብ ዋጋ ከተገቢው በላይ ንሯል እንዲሁም ሀገሪቱ ከገባችበት ቀውስ እንዳትወጣ ምክንያት ሆኗታል።. . .

. . . ሶስተኛው ጉዳይ ግን ከሁለቱ የተለየ እና ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው ጉዳይ ነው" ይላሉ አሮን። እሱም የድንብር አቋራጭ የውሃ አካላት ጉዳይ። ማለትም ሁለት እና ከዚያ በላይ ሀገራትን የሚያዋስኑ የውሃ አካላት በላይኛው እና በታችኛው ሀገራት መካከል የውሃ አጠቃቀም መብትን በተመለከተ ሊፈጠር የሚችለው አምባጓሮ አስጊ ነው።

ትልቅ ፈተና

'የውሃ ጦርነት' የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መለያ ይሆናል እየተባለ ቢነገርም እርግጥ አስካሁን ፈታኝ የሆነ ነገር አላስተዋልንም። ነገር ግን በእስያ እና በአፍሪቃ እየተስተዋለ ያለው የሕዝብ ዕድገት ተፈጥሯዊ ሀብታችን ላይ አደጋ እየጣለ ይገኛል። የዓለማችን ሙቀት መጨመርም አንዳንድ የውሃ ምንጮች እንዲደርቁ ምክንያት እየሆነ ነው። ውሃ ለግጭት መነሻ ነጥብ ሊሆን እንደሚችለው ሁሉ በአግባቡ ትቅም ላይ ከዋለ ለዓለማቀፋዊ ዕድገት ትልቅ መሰረት ሊሆንም ይችላል።

ለምሳሌ አፍጋኒስታን በቀጣናዋ ካሉ ሀገራት በላይኛው ተፋሰስ የምትገኝ ሀገር ነች። በጦርነት ስትታመስ የነበረችው አፍጋኒስታን አሁን ላይ የካቡል ወንዝን በፍትሃዊ መልኩ በመጠቀም በማደግ ላይ ትገኛለች። ለዚህም ነው የዘርፉ ተመራማሪዎች ከሀይድሮ ፖለቲካ ይልቅ ሀይድሮ ዲፕሎማሲ አዋጭ ነው እያሉ የሚገኙት።

Image copyright Getty Images

የተሻለ ክፍያ ለገበሬው

የዘርፉ በላሙያዎች አንድ ነገር ጠንቅቀን እንድንረዳ ይፈልጋሉ። ውሃ የሚገኘው በወንዞች፥ ሀይቆች ወይም ውቅያኖሶች ብቻ አይደለም። በመሬት ውስጥም አንጂ። ገበሬው እህል ለማምረት በሚጠቀምበት ለም አፈር ውስጥ። ገበሬው ከብቶቹን ለግጦሽ በሚያሰማራበት መስክ ውስጥ። ቨርችዋል ዋተር ወይም 'ምናባዊ ውሃ' እየተባለ የሚጠራው ይህ ሀብት በስንዴ ወይም በበሬ ስጋ መልክ ከላኪ ሀገራት ወደ ተቀባዮቹ ይላካል።

በኣውሮፓ ብቻ አርባ በመቶ የሚሆን 'ምናባዊ ውሃ' ከተቀረው ዓለም አህጉሪቱን ይቀላቀላል። ነገር ግን በዚህ ሂደት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው አርሶ አደሮች የሚያገኙት ገቢ እጅግ ያነሰ ነው። በዓለማችን መቶ ስድሳ የሚሆኑ ሀገራት ከውጭ በሚገቡ የምግብ ምርቶች ላይ ጥገኛ ናቸው። የውሃ ሀብት ባለቤት የሆኑት እንደ አሜሪካ እና ካናዳ ያሉ ሀገራት ምግብ አምርተው ለሌሎች ሀገራት በቅናሽ ዋጋ ይሸጣሉ።

ጆን አንተኒ አለን በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የግብርና ምሁር ናቸው። "ዓለማችን ሰላም ልትሆን የቻለችው በቨርችዋል ዋተር ወይም 'ምናባዊ ውሃ' ምክንያት ነው" ይላሉ አለን። "ወደ ሃገራት የሚገባው ውሃ በምግብ መልክ ከሌላ ሀገር የተገዛ ነው" በማለት ያክላሉ ። "ሃይድሮ ዲፕሎማሲ የክፍለ ዘመናችን ያለተዘመረልት ጀግና ነው ምክንያቱም የዓለማችንን አንፃራዊ ሰላም እያስጠበቀልን ነው" ሲሉ ያስረግጣሉ ምሁሩ።

አንድ ብርጭቆ ውሃ ጨልጠን ጥማችንን ስንቆርጥም ሆነ እህል ስናበቅልበት ውሃ የዓለም ፖሊተካ ሚዛን ጠባቂ መሆኑን ልናስብ ግድ ይላል። ውሃ ለዘመናት የነበረ፥ ያለ እና የሚኖር ሀብታችን ነውና።