ዓለማችንን በግኝቱ ወደፊት ያራመደው አይንስታይን ወጣ ባሉ ባህሪያቱም ይታወቅ ነበር።

አይንስታይን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዓለማችን ካፈራቻቸው ታላቅ ጠቢባን መካከል አልበርት አይንስታይን አንዱ ነው። አይንስታይን ከምጡቅነቱ ባለፈ ወጣ ባሉ ባህርያቱ ይታወቃል። ከኤነርጂ አቶም ማምረት እንደሚቻል ያሳየን አይንስታይን ምን ይታወቃል ለየት ካሉ ባህርያቱ አንድ ወይም ሁለት ነገር ያስተምረን ይሆናል። እነሆ አምስቱ።

1. የአስር ሰዓታት መኝታ እና የአንድ ሴኮንድ እረፍት

እንቅልፍ ለጤናችን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። አይንስታይንም ይህንን ምክር ችላ አላለውም። አሁን ላይ የአንድ አሜሪካዊ አማካይ የእንቅልፍ ጊዜ 6.8 ሰዓት ነው። አይንስታይን ግን በቀን ቢያንስ ለአስር ሰዓታት ይተኛ ነበር። ግን በቀን ለአስር ሰዓታት እየተኛ እንዴት ባለምጡቅ አእምሮ መሆን ይቻላል?

ዓለማችንን ከለወጡ ግኝቶች መካከል እንደ አርኬያዊ ሰንጠረዥ ወይም ፔሪየዲክ ቴብል፥ የዘር ቅንጣት ወይም የዲኤንኤ መዋቅር እንዲሁም የአይንስታይን የአንፃራዊነት ፅንሰ ሀሳብ ወይም ሪላቲቪቲ ቲየሪ ፈጣሪዎቹ በእንቅልፍ ውስጥ ሳሉ የመጡላቸው ኃሳቦች ናቸው። አይንስታይን የአንፃራዊነትን ፅንሰ ሀሳብ ወይም ሪላቲቪቲ ቲየሪን ሊያስበው የቻለው በህልሙ ላሞች በኤሌክትሪክ ሲያዙ በማየቱ ነበር። እውነት ግን ይህ ነገር ተዓማኒ ነው?

እ.አ.አ. በ2004 ዓ.ም. በጀርመን የሉቤክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ያደረጉት ጥናት ጥሩ እንቅልፍ የሚያገኙ ሰዎች ጥሩ እንቅልፍ ካላገኙ ሰዎች ሁለት እጥፍ በተሻለ ሁኔታ በፍጥነት የማሰብና የማስታወስ ችሎታ እንዳላቸው ያሳያል። እንቅልፍ ላይ ስንሆን ተመራማሪዎቹ ስፒንድል ኤቨንትስ እያሉ የሚጠሯቸው በአዕምሯችን ውስጥ ያሉ ፍንጣቂዎች እንደ ጆሮ ሆነው በማገልገል መረጃ ከውጭ ወደውስጥ ያስገባሉ።

የኦቶዋ ዩኒቨርሲቲው ኒውሮሳይንቲስት ስቱዋርት ፉገል እንደሚያምኑት "የአይንስታይን ምጡቅነት ከልህቀት ወይም ነገሮችን ከማስታወስ ጋር ብዙ ተያያዥነት የለውም። ለዚህም ነው አይንስታይን መደበኛ ትምህርት እና ቀላል ነገሮችን ማስታወስ ላይ ጥላቻ የሚያሳየው።"

ከዚህም በተጨማሪ አይንስታይን አጠር ያለ እረፍት ማድረግ ያዘወትር እንደነበር ይነገራል። ከልክ ያለፈ እረፍት እንዳይወስድ በማሰብም በተቀመጠበት ወይም ጋደም ባለበት ቦታ በእጁ ማንኪያ ይይዛል። ከማንኪያው ትይዩ ከስር የብረት ሳህን ያስቀምጣል። እንቅልፍ ሲወስደው ልክ ማንኪያው ከእጁ ወድቆ ብረት ላይ በማረፍ በሚያሰማው ድምፅ ይነቃል። በዚህ ሁኔታ ለአንድ ሴኮንድም ቢሆን እረፍት ያደርግ እንደነበር ይነገራል።

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

2. የእግር መንገድ

አይንስታይን የእግር መንገድን እንደተቀደሰ ተግባር ነበር የሚያየው። በኒው ጀርሲ ፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ በሚያስተምርበት ወቅት በቀን እስከ 1.6 ኪሎ ሜትር ድረስ በእግሩ ይራመድ ነበር። ቻርልስ ዳርዊንም በቀን ሶስት ጊዜ ለ45 ደቂቃዎች ይራመድ እንደነበረ ልብ ይሏል። አይንስታይን ይህንን ያደርግ የነበረው የሰውነቱን ቅርፅ ለመጠበቅ አልነበረም፤ እርግጥም የእግር እርምጃ ማድረግ ለማስታወስ፥ ለፈጠራ ችሎታ እንዲሁም ችግር ፈቺነትን ለማዳበር ጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች አሉ።

3. ፓስታ መመገብ

የምጡቅ አዕምሮ ባለቤቶች ምን ይሆን የሚመገቡት? የአይንስታይን አዕምሮ በምን ኃይል እንደተሞላ ባይታወቅም በይነመረብ ወይም ኢንተርኔት ላይ አይንስታይን ፓስታ መመገብ አብዝቶ እንደሚወድ ተፅፏል። እንደውም በአንድ ወቅት " ከጣልያኖች ምን እንደሚመቸኝ ታውቃላችሁ. . .ፓስታቸው እና ሌዊ ሲቪታ (ጣልያናዊው የሒሳብ ሊቅ) ነው" ሲል ቀልዷል።

ከሰውነታችን ሁለት በመቶ ብቻ ክብደት የሚይዘው አዕምሯችን ከምንበላው ሃያ በመቶውን ይጠቀማል። የአይንስታይን አዕምሮ ክብደት ከተለመደው የሰው ልጅ አዕምሮ በክብደት ያነሰ ነበር። ኃይል ሰጪ ምግብ ለአዕምሯችን ጥቅም ቢኖረውም ፓስታን አብዝቶ መመገብ ግን ሁሌም ጠቃሚ ላይሆን ይችላል ይላሉ የሮይሀምፕተን ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የሆኑት ሌይ ጊብሰን።

4. ፒፓ

ትምባሆ እና መሰል ነገሮችን የማጨስ ጉዳቶች አሁን ላይ በሰፊው የሚታወቁ ነገሮች ናቸው። ይህም የሚያስረግጥልን ከአይንስታይን መሰል ልምድ መውሰድ የብልህ ተግባር እንዳልሆነ ነው። አይንስታይን በህይወት ዘመኑ ፒፓ ያጨስ ነበር። ፒፓ ማጨስ ሰዎች ፍርድ እናዳያጓድሉና ሚዛናዊነት እንዳይጎድላቸው ያግዛል ብሎም ያምናል። የሲጋራ ቁሩ መንገድ ላይ ካገኘም ወስዶ ወደ ፒፓው ይጨምራት ነበር።

አይንስታይን ትምባሆ ማጨስ ለሳንባ በሽታ እንደሚያጋልጥ ጥናቶች ከማረጋገጣቸው ሰባት ዓመታት በፊት እ.አ.አ. በ1955 ዓ.ም. ነበር ሕይወቱ ያለፈው። ነገር ግን ስለትምባሆ ሲነሳ አንድ አስገራሚ ጥናት ሁሌም አብሮ ይነሳል። በአሜሪካ በ20 ሺህ ወጣቶች ላይ ለ15 ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው ይህ ጥናት እንደሚጠቁመው የላቀ አስታሳሰብ ያላቸው ሕፃናት ሲያድጉ ትምባሆ አጫሾች እንደሚሆኑ ነው። እርግጥ ሁሉም ቦታ ይህ ፅንሰ ኃሳብ ተግባራዊ አይደለም። ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም ትምባሆ የሚያጨሱ ስዎች ንቃተ-ህሊናቸው ዝቅ ያለ ነው የሚል ጥናት አለ።

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

5. ካልሲ ምን ያደርጋል?

የአይንስታይን ለየት ያሉ ባህርያት አሁን ከምንነግራችሁውጭ ብዙም ወዝ አይኖራቸውም ነበር። አይንስታይን ካልሲ አይወድም። አዎ ካልሲ አይወድም። ኋላ ላይ ሚስቱ ለሆነችው የአጎቱ ልጅ ኤልሳ በፃፈው ደብዳቤ አይንስታይን ሲናገር "ሁሌም አውራ ጣቴ የካልሲዬን ጫፍ ይቀደዋል፤ ከዛ በኋላ ካልሲ ማድረግ ተውኩኝ።" አንዳንዴ ሰንደል ጫማዎቹን ማግኘት ካልቻለ የሚስቱ ኤልሳን ታኮ ጫማ አድርጎ ይወጣ ነበር።

እርግጥ ካልሲ አለመጠቀም ጥቅም እንዳለው የሚያሳይ ጥናት የለም። ነገር ግን ሁሌም አዲስ ነገር ከመሞከር ወደኋላ የማይለው አይንስታይን ከካልሲ ጋር ዓይን እና ናጫ እንደሆነ እ.አ.አ. ሚያዝያ 18 ቀን 1955 ዓ.ም. አለፈ።