አየር ማጤዣ(ኤይር ኮንዲሽነር) እንዴት ዓለምን ሊቀይር ቻለ?

Image copyright Getty Images

የዓለምን የአየር ሁኔታ መቆጣጠር ብንችል ብለን እናስብ። አንዲት ቁልፍ በመጫን ስንፈልግ ሞቃት ስንፈልግ ቀዛቃዛ ሲያሻን እርጥብ ወይም ደረቅ ማድረግ ብንችል። ድርቅም አያጠቃን ጎርፍ አያጥለቀልቀን። በረሃ የለ በረዶ የወረው መንገድ የለ . . . ሁሉም ሰላም!

የሰው ልጅ ምንም ያህል ብልህ ቢሆን የዓለምን የአየር ሁኔታ መቆጣጠር አልቻለም ወይም አይችልም። ነገር ግን ዕድሜ ለአየር ማጤዣ ወይም 'ኤር ኮንዲሽነር' የዓለምን አየር ሁኔታ መቆጣጠር ባይቻል እንኳ ቢያንስ የቤቱን አየር ንብረት መቆጣጠር ችሏል። ነገር ግን እንዲህ በቀላሉ የተገኘ ግኝት አይደለም። ይዞት የመጣው መዘዝም ከምናስበው በላይ ነው።

የእርጥበት ችግር

በ19ኛው ክፈለ ዘመን ላይ አሜሪካዊው ሥራ ፈጣሪ ፍሬድሪክ ቱዶር አንድ ነገር አገኘ። ክረምት ላይ ወደ በረዶነት ከተቀየሩ ወንዞች በረዶን በመውሰድ በቆርቆሮ አድርጎ ሞቃት ወደሆኑ ስፍራዎች በመውሰድ ሙቀቱን ለመከላከል መፍትሄ አበጀ። ነገር ግን አሁን የምናውቀው ዓይነት የአየር ማጤዣ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው እ.አ.አ. በ1902 ዓ.ም. ሲሆን የዚህ ግኝት መነሻ ጥንስስ ሀሳብ ግን የሰው ልጅ ምቾት አልነበረም።

በኒው ዮርክ የሚገኝ አንድ ማተማያ ቤት በእርጥበት ምክንያት አንድን ወረቀት አራት ጊዜ በአራት ዓይነት ቀለማት ማተም ግድ ሲሆንበት ጊዜ 'በፋሎ ፎርጅ' ለተሰኘ ኩባንያ መፍትሄ እንዲያበጅለት አሳሰበ። በዚህ ጊዜ ወጣቱ አሜሪካዊ ኢንጂነር ዊሊስ ካርየር በሙከራው አሞኒያ ላይ የተጠመጠመ ሽቦ አየር ሲነፍስበት እርጥበቱን ቢያንስ በ55 በመቶ እንደሚቆጣጠረው መረዳት ቻለ። ማተሚያ ቤቶቹም በዚህ ግኝት እጅግ ደስተኛ ሆኑ።

ከዚያም በፋሎ ፎርጅ የተባለው ኩባንያ የዊሊስ ካርየርን ፈጠራ ተመሳሳይ ችግር ላጋጠማቸው ፋበሪካዎች መቸብቸብ ጀመረ። ፋብሪካዎቹ ለማሽኖቻቸው እንጂ ለሰራተኞቻቸው ምቾት እጅግም የተጨነቁ አልነበሩም። ነገር ግን እ.አ.አ. በ1906 ዓ.ም. ወጣቱ ካርየር ከፋብሪካዎች አልፎ ሰው በዛ በሚልባቸው እንደ ቲያትር ቤት ላሉ ስፍራዎች የሚሆን የአየር ማጤዣ መስራትን ተያያዘው። ከዚያ በፊት ግን ቲያትር ቤቶች በበጋ ወቅት በተለይ በሙቀት ሳቢያ ይዘጉ ነበር።

ቲያትር ቤቶች በፈሉበት በ1920ዎቹ በአሜሪካ የአየር ማጤዣ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ መዋል ጀመረ። በትንሽ ጊዜ ውስጥም ከቲያትር ባልተናነሰ የሰውን ቀልብ መሳብ ጀመረ። ለመገበያያ አዳራሽ ወይም ሞሎች መስፋፋትም የአየር ማጤዣ ማሽኖች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል።

Image copyright CARRIER
አጭር የምስል መግለጫ ዊሊስ ካርየር አሞኒያ ላይ ሽቦ በመጠምጠም አየር እንዲነፍስበት በማድረግ እርጥበትን መቆጣጠር ቻለ

ተለዋጭ ቴክኖሎጂ

ኮምፒውተሮች በጣም ከሞቁ ወይም በጣም ቅዝቃዜ ውስጥ ከሆኑ መስራት አይችሉም። ውስጣቸው አየር ማጤዣ ወይም ፋን ባይገጠምላቸው ምንም ዓይነት ሥራ በኮምፒውተር መስራት አይቻልም ማለት ነው። ፋብሪካዎችም በተመሳሳይ አየር ማጤዣ ካልተገጠመላቸው ዕለታዊ ተግባራቸውን መከወን እጅጉን ከባድ ይሆንባቸዋል። ከዛም አልፎ አየር ማጤዣዎች በኪነ-ሕንፃ ወይም አርክቴክቸር መስክ አብዮትን ማምጣት ችለዋል።

በህጉ መሰረት ቀዝቀዝ ያለ አየር ያለው ህንፃ ወፍራም ግድግዳ ያለው፣ ጣራው ከፍ ያለ፣ ሰፋፊ በረንዳዎች የተሰሩለት እንዲሁም መስኮቱ ፀሃይን ሸሽቶ የተተከለ መሆን አለበት። በአሜሪካ ደቡባዊ ክፍል ታዋቂ የሆኑት ዶግትሮት ቤቶች እየተባሉ የሚጠሩ መኖሪያዎች ክፍት ኮሪዶር ያላቸው ተደርገው ነበር የሚሰሩት። ከአየር ማጤዣዎች በፊት በመስታወት የታጠሩ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን መስራት የማይታሰብ ነበር። ምክንያቱም ህንፃው ከፍ ባለ ቁጥር ሙቀቱ በጣም ከፍተኛ ስለሚሆን። ዱባይ እና ሲንጋፖር የመሳሰሉ ባለሰማይ ጠቀስ ከተሞችን ያለአየር ማጤዣዎች ማሰብ ባልተቻለ ነበር። ለዚህም ነው አየር ማጤዣዎች ሥነ-ሕዝብ ላይም ላቅ ያለ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማምጣት ችለዋል የሚባለው።

ሞቃት በሆነው የአሜሪካ ደቡባዊ ክፍል የሚኖሩ አሜሪካውያን ድርሻ ከአየር ማጤዣዎች በኋላ ከ28 ወደ 40 በመቶ አደገ። የፖለቲካ ሚዛኑም ቅርፅ መለወጥ ጀመረ። አንዳንድ ተንታኞች ሮናልድ ሬገን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ለመመረጣቸው ዋነኛ ምክንያት የአየር ማጤዣ ነው በማለት ይከራከራሉ። በወቅቱ አሜሪካ ከዓለም የአየር ማጤዣ ምርት ግማሽ ያህሉን ትጠቀም ነበር።

በህንድ፣ ብራዚል፣ ቻይና እና ኢንዶኔዥያ የአየር ማጤዣዎች ፍላጎት ባለፉት አስር ዓመታት ቁጥሩ እጅግ ጨመሯል። ከሰላሳ በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት መካከል አስራ አንዱ ሞቃት ስፍራዎች ላይ መገኘታቸው ገበያው ማደጉን እንደሚቀጥል ማሳያ ነው።

የአየር ማጤዣ ገበያ መድራቱ ለብዙዎች በጣም በጎ ዜና ነው። ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በሙቀት ምክንያት የሚደርሰውን ሞት ለመቀነስ ትልቁን ሚና ከመጫወቱም በላይ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በታራሚዎች መካከል የሚፈጠረውን ፀብም ይቀንሳል። የአየር ሁኔታው ከ22 ዲግሪ ሴልሺየስ ሲልቅ ተማሪዎች በሒሳብ ትምህርት ዝቅ ያለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ጥናቶቹ ያሳያሉ። በአሜሪካ የአየር ማጤዣዎች በተገጠመላቸው የሥራ ቦታዎች የሚሰሩ ሰዎች የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑም ጥናቶች ያክላሉ።

እውነታ ወዲህ ነው!

ነገር ግን አሉታዊ ተፅዕኖዎችንም መዘንጋት የለብንም። በአሜሪካ አሪዞና ግዛት የተሰራ ጥናት እንደሚያሳየው የአየር ማጤዣ ከተገጠመላቸው ቦታዎች የሚወጣው አየር የከተማዋን የምሽት ሙቀት በሁለት ዲግሪ ሴልሺየስ ጨምሮታል። የአየር ማጤዣዎችን ለማንቀሳቀስ የምንጠቀምበት የድንጋይ ከሰል ለአየር መበከል የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል። አየር ለማቀዝቀዝ የምንጠቀምባቸው የአየር ማጤዣዎች ግሪን ሃውስ እየተባሉ ከሚጠሩት የኢንዱስትሪ ስፍራዎች ከሚለቋቸው የበለጠ አየር ይበክላሉ።

የአየር ማጤዣ ቴክኖሎጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰለጠነ እና ለአየር ንብረት ተስማሚ እየሆነ እየተመረተ ቢገኝም እ.አ.አ. በ2050 የሰው ልጅ ኃይል ፍላጎት እጅጉን ስለሚንር የአየር ንብረትን ከመበከል ወደኋላ እንደማይል ይነገራል። እስከዚያ ግን ልክ እንደውስጠኛው የውጭውንም አየር ንብረት መቆጣጠር የሚችል ግኝት ይመጣ ይሆን? የሁላችንም ጥያቄ ነው።