የሮቦት ነገር. . . ወዴት ወዴት?

Image copyright Getty Images

የአንድ ፎቶ ኮፒ ማሽን ያህል ክብደት እና ቅርፅ ቢኖራት ነው። እደብዙዎቹ አዳዲስ ሮቦቶች የጃፓን ሪት ናት። እንደ አዲስ መኪና ዓይነት ድምፅ እያወጣች በመጋዘኑ ወዲያ ወዲህ በመንጎራደድ የምታዘውን ነገር በዓቱ ታከናውናለች። በግራ እጇ የወረቀት ሳጥኑን በመጎተት ከሳጥኑ ውስጥ በቀኝ አጇ ጠርሙስ መሳብ እዲችል ታመቻቻለች።

እርግጥ ከወረቀት ሳጥን ጠርሙስ ለመሳብ የመጀመሪያዋ ሮቦት ላትሆን ትችላለች ነገር ግን በሮቦት ቴክኖሎጂ ዘርፍ ነገሮችን እንዲህ በቀላሉ እና በፍጥነት ልክ እንደ ሰው ልጅ በመከወን አንድ እርምጃ የተራመደች ነች።

አሁን ላይ የሰው ልጅ እና ማሽን በመተባበር ነገሮችን እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ወደፊት ደግሞ ሮቦቶች ሰዎችን ተክተው በመጋዘን ውስጥ ወዲያ ወዲህ ማለት መጀመራቸው የማይቀር እንደሆነ ይነገራል።

ሰዎች እና ሮቦቶች አብረው የሚሰሩባቸው ፋብሪካወችም ነበሩ። እ.አ.አ. በ1961 ጄኔራል ሞተርስ የተሰኘው ፋብሪካ ዩኒሜት የተባለ ባለአንድ እጅ ሮቦት በመግጠም በዋነኛነት የብየዳ ሥራውን እንዲያቀላጥፍለት አደረገ።

ነገር ግን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሮቦቶች በሰው ልጅ ሥራ ውስጥ ሰርገው መግባት አልቻሉም። አንድም ለሰው ልጅ ህልውና ሲባል ሌላም ሮቦቶች በጣም ቁጥጥር የሚያሻቸው ስለሆኑ ያንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። የረቀቁ ሮቦቶች በሚመረቱበት በአሁኑ ዘመን ግን ሮቦቶቹን ስለመቆጣጠር ብዙ መጨነቅ አስፈላጊ አይደለም።

በዕድሳት ላይ

ሪቲንክ ሮቦቲክስ በተባለው ፋብሪካ የተሰራው 'ባክስተር' የተሰኘው ሮቦት ሰዎች ላይ አይወድቅም ሰውም ቢወድቅበት እንኳ ፍንክች የአባ ቢላዋዱ ልጅ. . አይንቀሳቀስም። ከአያቶቹ በተለየ ሁኔታ 'ባክስተር' ከሥራ ባልደረቦቹ ልምድ ይቀስማል።

የዓለም ሮቦቶች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው። በኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሰሩ ሮቦቶች ሽያጭ ቁጥር በዓመት በ13 በመቶ እያደገ ነው። በሌላ አገላለፅ የሮቦቶች የውልደት መጠን በየአምስት ዓመቱ እጥፍ እያደገ ነው። የዚያኑ ያህል ተግባራቸውም እየረቀቀ መጥቷል።

ሮቦቶች ከመጠጥ ቤት እስከ ሆስፒታል እንደየሁኔታው እያገለገሉ ነው። ነገር ግን አሁንም የምንፈልገውን ያክል እያገለገሉን እንዳልሆነ ይታመናል።

ተሻሽለው ለመጡ የሮቦት ሀርድዌሮች ምስጋና ይግባቸውና ሚዛን መጠበቅ፣ የተሻለ እይታ እና ዳሳሽ እጆችን የተገጠመላቸው ሮቦቶችን ማየት እየተዘወተረ መጥቷል።

ከዚህ ባሻገርም ሮቦቶች ሰው-መሰል ችሎታን ተላብሰው የተሻለ አእምሮ ይዘው መፈጠር ጀምረዋል። እጅግ በጣም የተሻለ ችሎታ ያላቸው ሮቦቶችን ለመፍጠር ሙከራው አሁንም ቀጥሏል።

Image copyright Rethink Robotics

የሰው ልጅ ዕጣ

ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን የሥራ ዕድሎች እያጠበበ በሌሎች መተካቱ አዲስ ነገር አይደለም። ነገር ግን ከሮቦቶች መበራከት በኋላ ለሰው ልጆች የሚተርፈው ሥራ እጅግ የከፋ እና የወረደ እንደሚሆን ይገመታል።

ለዚህም ምክንያት የሚሆነው ቴክኖሎጂ ከሥራው የይልቅ ማሰቡ ላይ እየበረታ መመጣቱ ነው። የሮቦቶች አእምሮ ከሰውናታቸው በፈጠነ መልኩ እያደገ መጥቷል።

ራይዝ ኦፍ ዘ ሮቦትስ በተሰኘው መፅሃፉ የሚታወቀው ማርቲን ፎርድ ''ሮቦቶች አውሮፕላን ማሳረፍ ይችሉ ይሆናል ዎል ስትሪትም ሄደው አክስዮን መገበያየታቸውም አይቀርም። ነገር ግን ሽንት ቤት ማፅዳት አይችሉም'' ሲል ይሞግታል።

በተጨማሪም ሮቦቶች የቤት ሥራዎቻችንን እንዲሰሩልን ባንጠብቅ ጥሩ ነው ባይ ነው።

ሮቦቶች የሰው ልጅን በማሰብ የሚበልጡት ከሆነ፤ ሰዎች ደግሞ ሮቦቶችን በፍጥነት የሚበልጧቸው ከሆነ እና ለምን የሰውን ልጅ በሮቦት ጭንቅላት መቆጣጠር አይቻልም?

እርግጥ የማይዋጥ ሀሳብ ሊመስል ይችላል ግን ሊሆን የሚችል ነገር ነው።