የዓለምን ትራንስፖርት የቀየረው ዲዚል ሞተር

የዲዚል መኪናዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩዶልፍ ዲል ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ ፈጠራው ግቡን አሳክቶ ዓለምን ሲያጥለቀልቅ ሳይመለከት ሕይወቱ አለፈ።

እ.አ.አ. መስከረም 29/ 1913 ዓ.ም ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ሩዶልፍ ዲዚል ከቤልጄም በእንግሊዝ በኩል አድርጎ ወደቤቱ በመርከብ አየተመለሰ ነበር።

የሌሊት ልብሱ እና አልጋው ተስተካክሎ ቢቀመጥም ልብሱን መቀየር አልፈለገም። ስለተጫነው ዕዳ እና ወለዱን እንዴት አድርጎ መክፈል እንደሚችል አብዝቶ እየተጨነቀ ነበር።

ከሌላው ቀን በተለየ ሁኔታ የዕለት ውሎ መመዝገቢያው ላይ በትልቁ የኤክስ ምልክት ሰፍሯል። ዲዚል ወደ መርከቡ በረንዳ ወጣ ብሎ ንፋስ ለመቀበል ያወለቀውን ኮቱን ወለሉ ላይ ካስቀመጠ በኋላ የመርከቡን አጥር ተሻግሮ በመዝለል ወደ ውቅያኖሱ ገባ።

ይህ እንግዲህ ስለ ሩዶልፍ ዲዚል አሟሟት በግምት የሰፈረ ታሪክ ነው። ስለ አሟሟቱ ብዙ ብዙ ይባላል። በሴረኞች ምክንያት እንደሞተ የሚናገሩ ግን ያይላሉ።

ከዲዚል መሞት አርባ ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሰን በ1872 ላይ ራሳችንን ብናገኘው በሞተር የሚሰሩ ባቡሮች እና ፋብሪካዎች ባሉበት ዘመን፤ ከተማ ውስጥ ግን በፈረስ ኃይል የሚንቀሳቀሱ መጓጓዣዎችን መመልከት አዲስ አልነበረም።

በዚያ ዘመን በተከሰተ የፈረስ ጉንፋን ምክንያት የአሜሪካ ከተሞች ጭር ኩምሽሽ ብለው ነበር።

ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ያሉበት ከተማ ቢያንስ እስከ መቶ ሺህ ፈረሶችን ያስተናግዳል። የፈረሶቹ ሽንት እና ፋንድያ ለበሽታው መስፋፋት ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ግልፅ ነበር።

ይህንን የሚያስወግድ አነስተኛ ሞተር ማግኘት ከሰማይ እንደወረደ መና ነበር።

በእንፋሎት የሚሰሩ ሞተሮች አንድ አማራጭ ነበሩ። በነዳጅ፣ በጋዝ እንዲሁም በባሩድ የሚሰሩ ሞተሮች ቢሞከሩም ለሥራ አልበቁም ነበር። ይህ እንግዲህ ሩዶልፍ ዲዚል ገና ተማሪ በነበረበት ወቅት ነበር።

ዲዚል በዚህ ዘርፍ የራሱን ነገር ይዞ ለመምጣት ሩጫውን ተያያዘው። መጀመሪያ የሰራው ሞተር 25 በመቶ ብቻ ውጤታማ ሲሆን፤ እንደዛም ሆኖ ሌሎቹ ከሰሩት እጅግ የተሻለ ነበር። የዲዚልን ሞተሮች እጅግ ወጤታማ ያደረጋቸው ነገር ከከሰሉ ወይም ከነዳጁ ጋር የሚቀጣጠሉበት ሂደት ነው።

ከሰል ከአየር ጋር ሲጋጭ ሞተር እንዲነሳ ያደርጋል። ነገር ግን የሁለቱ ውህደት በደንብ ከተጨመቀ ሞተሩ በፍጥነት ይነሳል። የዲዚል ፈጠራ አየሩን ብቻ በከፍተኛ ጫና ውስጥ በመጭመቅ ከዛም ከሰሉን ወይም ነዳጁን በትክክለኛው ሰዓት በመለኮስ ሞተር እንዲነሳ ያደረገ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Shutterstock

የዲዚል ፈጠራ ሌላው ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር አነስ ያለ ነዳጅ መጠቀሙ ነው። ነገር ግን በመጀመሪያዎቹ ፈጠራዎቹ ላይ መተማመን ያጡ ሰዎች ሞተር የገዙበትን ገንዘብ እንዲመልስላቸው መጠየቅ ጀመሩ።

ይህም ሩዶልፍን ካላሰበው ዕዳ ውስጥ ዘፈቀው። ቢሆንም ግን ሩዶልፍ ምርቱን ማሻሻሉን እና ተጨማሪ ነገር ማሳየቱን ቀጠለ።

የዲዚል ሞተሮች ከሌሎቹ ሞተሮች ጋር ሲነፃፀሩ በጣም ዝቅተኛ ነዳጅ የሚጠቀሙ እና ሙቀት የሚቋቋሙ በመሆናቸው በተለይ በወታደራዊው ዓለም ተመራጭነትን ማግኘት ጀመሩ። እ.አ.አ. በ1904 ዓ.ም ዲዚል ሞተሮቹን ለፈረንሳይ የምድር ጦር ማቅረብ ጀመረ።

ይህም የሩዶልፍን አሟሟት በተመለከተ ከሚነገሩት የሴራ ንድፈ ሃሳቦች መካከል ወደ አንዱ ይወስደናል።

እ.አ.አ በ1913 አውሮፓ በጦርነት በምትታመስበት ወቅት ጀርመን እንግሊዝን ለመውረር ወደ ለንደን ጉዞ ላይ ነበረች። በወቅቱ የነበረ አንድ ጋዜጣ "የፈጠራ ባለቤቱ ሥራውን ለእንግሊዝ እንዳይሸጥ በሚል ወደ ውቅያኖስ ተወርውሮ ተገደለ" ሲል ፅፎ ነበር።

ዲዚል ሞተሩን ከነዳጅ ጀምሮ እስከ ከሰል እንዲሁም ከአትክልት የተዘጋጀ ዘይትን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮችን እንዲጠቀም አድርጎ ነው የሰራው። እ.አ.አ በ1900 በፓሪስ በተዘጋጀ የዓለም የንግድ ትርዒት ላይ በለውዝ ዘይት የሚሰራ ሞተር አስተዋውቆም ነበር።

ከመሞቱ አንድ ዓመት አስቀድሞ ዲዚል ከአትክልት የሚዘጋጁ ዘይቶች እንደ ነዳጅ ሁሉ በጣም አስፈላጊ መሆናቸው እንደማይቀር ተነበየ።

ይህ ዜና ደግሞ ለነዳጅ አምራቾች በጎ ዜና አልነበረም። ይህኛው መንገድ ወደ ሁለተኛው የዲዚል አሟሟት ሴራ ይወስደናል። አንድ የወቅቱ ጋዜጣ የዲዚልን ሞት ሲዘግብ ሕይወቱ በነዳጅ አምራች ኩባንያዎች እንደጠፋ አድርጎ ፅፏል።

ዲዚል እንዴት እንደሞተ እርግጠኛ ሆኖ መናገር እጀግ ከባድ ነው። ሰውነቱ ከአስር ቀናት በኋላ ሲገኝ ለምርመራ የሚበቃ መረጃ አልተገኘበትም ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Alamy

ል እና ከባቢ አየር

የተሻለ ነገር ይዘው ለመምጣት የሞከሩ ፈጣሪዎች ቢኖሩም ሩዶልፍ ዲዚል የፈጠረው ሞተር እስካሁን ድረስ ከነዳጅ ሞተሮች የተሻለ ውጤታማ ነው።

ነገር ግን የዲዚል ሞተር ትልቁ ችግር ከባቢ አየርን መበከሉ ነው።

የዲዚል ሞተር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ያለጊዜ የተከሰቱ ሞቶች መንስኤ እንደሆነ ይነገራል።

ይህን የተረዱ አንዳንድ የዓለማችን ከተሞች የዲዚል መኪናዎች እ.አ.አ. ከ2025 በኋላ እንዳይነዱ አግደዋል።

አንዳንዶች ደግሞ ከ2040 በኋላ ማንኛውም ዓይነት የዲዚል ምርት እንዲሁም በነዳጅ የሚሰራ መኪና በከተማቸው ዝር እንዳይል እንደሚያደርጉ ከአሁኑ አሳስበዋል።

እንግዲህ ዲዚል አሟሟቱ በዕዳ ምክንያት ካልሆነ ወይም ተገድሎ ካልሆነ ሞተሩ ባመነጨው አየር በካይ ጋዝ ምክንያት ይሆን?? ምን ይታወቃል።