ከመስታወት የተሰራ አጥንት?? አጀብ ነው

Image copyright Uros Zunic / Alamy Stock Photo

እ.አ.አ. 2002 ዓ.ም. በሎንዶን ኪንግስ ኮሌጅ የፊት መልሶ ጠጋኙ አያን ቶምፕሰን የስልክ ጥሪ ይደረስዋል። በሃኣዎቹ መባቻ ላይ ያለ አንድ ወጣት በመኪና አደጋ ምክንያት ጉዳት ይደርስበታል።

"የደረሰበት የመኪና አደጋ ዐይኑን ደግፎ የሚይዘው የፊቱ አጥንት ላይ ስለሆነ የብዥታ እና ትኩረት የማጣት ችግር አስከትሎበታል። ከዛም አልፎ ተጎጂው ቀለም መለየት አይችልም። ሰውየው በአውሮፕላን ጥገና ላይ ስለተሰማራ ከአደጋው መዳን ካልቻለ ወደ ስራው አይመለስም ማለት ነው" ሲል ያብራራል ቶመፕሰን።

አደጋው ከተከሰተ በኋላ የቀዶ ጥገና ባለሙያዎች አንድ ሚሊ ሜትር የሚሆነውን የተሰበረውን በጣም ደቂቅ አጥንት ለመተካት ሙከራቸውን ተያያዙት። ለሙከራቸው መሳካት ምትክ አጥንት ከህመምተኛው ከመውሰድ ጎን ጀምሮ ብዙ ጥረቶች አካሄዱ። ሁሉም ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀሩ። ሕመምተኛው ላይም ከፍተኛ ስቃይ ማስከተል ጀመሩ። ዶክተሮቹ መላው አጠራቸው።

ቶምፕሰን ያመጣው ሀሳብ ግን ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር። ከመስታወት በተሰራ ምትክ አጥንት ሕመምተኛውን ማከም። ከመስታወት ሰው ሰራሽ አጥንት የመስራት ሀሳብ የማይታሰብ ቢመስልም መስታወቱን ቅርጽ በማስያዝ ሙከራውን እውን ለማደረግ እንቅስቃሴ ተጀመረ።

"ባዮግላስ እየተባለ የሚጠራው መስታወት እንደማንኛውም ዓይነት መስታወት ሳይሆን ሰውነት ውስጥ ሲገባ ከሌሎች ሕዋሳት ጋር በመጣጣም መስራት የሚችል ነው። ስለሆነም ሰውነታችን እንደ ባዕድ ሳይሆን እንደ ሰውነት አካላችን ይቀጥረዋል።" በማለት ሁኔታውን የሚያብራሩት ደግሞ በሎንዶን ኢምፔሪያል ኮሌጅ የባዮግላስ ባለሙያው ጁሊያን ጆንስ ናቸው። "ከአጥንት ጋር ከተዋሃደ በኋላ ደግሞ እንደ ለስላሳ አጥንት መሆን ይጀምራል።" በማለት ያክላሉ ባለሙያው።

ለቶምፕሰን ውጤቱ እጅግ ፈጣን እና ድነገተኛ ነበር። ሕመምተኛውም በአጭር ጊዜ ውስጥ አገገመ። እነሆ አደጋው ከደረሰ አስራ አምስት ሆነው። ተጎጂውም አደጋው ያልተፈጠረ ያክል ወደ ሙሉ ጤንነቱ ተመለሰ።

ቶምፕሰን በዚህ ሂደት ከመቶ በላይ በመኪና እና በሞተር ብስክሌት አደጋ የተጎዱ ሰዎችን ለማከም ቻለ። "ባዮግላስ ከሕመምተኛው አጥንት በላይ የተሻለ ምላሽ ይሰጣል። ከዛም አልፎ ባክቴሪያ በመግደል ኢንፌክሽንን ማጥፋት ይችላል።"

ባዮግላስ

ባዮግላስ እ.አ.አ. በ1969 ዓ.ም. በአሜሪካዊው ሳይንቲስት ላሪ ሄንች ነው የተፈበረከው። ሄንች ባዮግላስን ለመፍጠር የተነሳሳው በቪየትናም ጦርነት ወቅት የተጎዱ ሰዎችን እጅ ከሰውነት ጋር በሚጣጣም አካል ለመተካት በማሰብ ነበር።

ላለፉት አስርት ዓመታት የቀዶ ጥገና ባለሙያዎች ባዮግላስን በክሬም መልክ ነር የሚጠቀሙት። እ.አ.አ. ከ2010 በኋላ ግን ክሬም መሰሉ ባዮግላስ ሴንሶዳይን የተባለ የጥርስ ሳሙና ውስጥ ተካቶ ገበያ ላይ መዋል ጀመረ። ጥርሳችንን በምንቦርሽበት ወቅት ባዮግላሱ በፍሳሽ መልክ በመግባት ካልሲየም ፎስፌት የተሰኘውን ንጥረ ነገር ይለቃል። በጊዜ ሂደትም ከጥርሳችን ጋር ይዋሃዳል።

በሌላ በኩል ደግሞ የአጥንት እና መገጣጠሚያ ቀዶ ጥገናን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሽግሩ ግኝቶች ዕድገት ላይ መሆናቸውም ይሰማል። የሚነጥር ባዮግላስ እያሉ ስለሚጠሩት መሳሪያ የሚናገሩት በኢምፔሪያል ኮሌጅ የቁሳቁስ ክፍል ሰራተኛ ጆንስ "ከባዮግላስ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ነገር ግን በኬሚካላዊ ውህደቱ ላይ ለውጥ ተደርጎበታል" ይላሉ።

Image copyright Edward Olive / Alamy Stock Photo

የዚህ መሳሪያ ዋና ዓላማ የአጥንት ስብራት ያጋጠማቸው ሰዎች አጥንት ውስጥ ገብቶ በመደገፍ ሰዎቹ ያለ ክራንች እንዲሁም ሌላ ነገር እርዳታ እንዲራመዱ ማድረግ ሲሆን በጊዜ ሂደትም ነጣሪው ባዮግላስ ከሰውነት ጋር እጅጉን ተላምዶ ተግባሩን ያከናውናል። "ለምሳሌ ከፍተኛ ስብራት የደረሰበት ሰው አጥንቱ መልሶ እንዲበቅል ተጎጂው/ዋ አጥንታቸው ላይ ክብደት ማሳረፍ ይኖርባቸዋል" ይላል ጆንስ።

ባዮግላስ ላይ የሚደረግ ኬሚካላዊ ለውጥ መሳሪያው የተለየ ቅርጽ እንዲይዝና እንደ ጎማ ታዛዣ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህ ባዮግላስ በተለይ ለኦርታፔዲክ ወይም ለመገጣጠሚያ አጥንት ስብራት ቀዶ ጥገና የተሰራ ነው። ከዚም ባለፈ ጆንስ በሶስታዊ ልኬት ወይም 3ዲ መልክ ተሰርቶ አጥንት ውስጥ የሚሰርጽ ባዯግላስ ለመስራት ጥረት ላይ ነው። የሙከራውን ስኬታማነት ለማረጋግጥም ጆንስ ለሕክምና ጥናት የተበረከተለትን አስከሬን ይጠቀማል። "መሳሪያው እንደ ትክክለኛ የመገጣጠሚያ አጥንት መስራቱን ካረጋገጥን በኋላ በእንስሳት ላይ ሙከራችንን እንቀጥላለን" ሲል ጆንስ ይናገራል።

ይህ መሳሪያ ውጤታማነቱ ከተረጋገጠ የዲስክ መንሸራተት በሽታ ላጋጠማቸው ሰዎችም መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ ይገመታል። ቀድሞ የዲስክ መንሸራተት በሽተኞች በእንቅስቃሴ ወቅት ከሚያጋጥማቸው ስቃይም ሙሉ በሙሉ እንደሚገላግላቸው ይታመናል። እንደ ጆንስ እምነት መሳሪያው በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ውጤታማ ሆኖ ለገበያ ይቀርባል።

ከሰው ሰራሽ መሳሪያዎች ተሰርተው ሰውነታችን ውስጥ በመግባት የሚላመዱ ንጥረ ነገሮችን ማግኘት የማይታሰብ የሚመስል ነገር ሊመስል ይችላል። ነገር ግን በሕክምናው ዘርፍ ያሉ ተመራማሪዎች ይህንን ህልም የሚመስል ነገር እውን ለማድረግ ደፋ ቀና ማለት ኣለቆሙም። ከመስታወት የተሰራ ለስላሳ አጥንት አሁን ላይ ሚሊዮኖች ጋር በጥርስ ብሩሽ መለክ ደርሷል። ነገ የሚያሳያነን ደግሞ ማን ያውቃል?