ዩኒቨርስቲዎ በስህተት 25 ሚሊዮን ብር ቢያበድሮት ምን ያደርጋሉ?

Image copyright Alamy

የደቡብ አፍሪው ዋልተር ሲሲሉ ዩኒቨርሲቲ እንዴት በስህተት ለአንድ ተማሪ አንድ ሚሊዮን ዶላር ሊበደር እንደቻለ ለማረጋገጥ ምርመራ ላይ መሆኑን ታወቀ።

ስህተት እንደተሰራ የታወቀው የተማሪዋ የባንክ ሂሳብን የሚያሳይ የታተመ ደረሰኝ ኮፒ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከተሰራጨ በኋላ ነበር። የዩኒቨርሲቲው ቃል-አቀባይ ተማሪዋ ከተበደረችው ገንዘብ የተወሰነውን የቅንጦት ልብሶችን በመግዛት በማባከኗ ተወቃሽ ነች ብለዋል።

ስሟ ያልተጠቀሰው ተማሪ ስህተት እንደተፈጠረ ማሳወቋን ተናግራለች። የተቀረውንም ገንዘብ እንደመለሰች መናገሯም ተዘግቧል።

የዩኒቨርሲቲውን ቃል-አቀባይ ዮኔላ ቱክዋዮን ጠቅሶ ኒውስ24 እንደዘገበው ተማሪዋ ላባከነችው እያንዳንዱ ሳንቲም ተጠያቂ ትሆናለች ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ ተማሪዎች ለመፃህፍት፥ ለመኖሪያ እንዲሁም ለምግብ የሚሆን ብድር በብሔራዊ የተማሪዎች ገንዘብ እርዳታ እቅድ በኩል ይሰጣቸዋል። ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ የተበደሩትን ገንዘብ መመለስ ግዴታቸው እንደሆነም ታውቋል።

በተለምዶ የደቡብ አፍሪካ ተማሪዎች ለዚህ ብድር የሚሆን የተለየ ካርድ የሚሰጣቸው ሲሆን ካርዶቹን በተወሰኑ ሱቆች ብቻ ነው መጠቀም የሚችሉት።

የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ የተማሪዎች ገንዘብ እርዳታ እቅድ በትዊተር ገፁ ለጥፋቱ ዋነኛ ተጠያቂ ዋልተር ሲሲሉ ዩኒቨርሲቲ ነው በማለት ፅፏል።