የወጣቶች ዘመቻ በእምቦጭ አረም ላይ

አጭር የምስል መግለጫ ወጣቶች ውደ በጎ ፈቃድ ዘመቻው ሲሰማሩ

በኢትዮጵያ ትልቁ የሆነው የጣና ሃይቅ በእምቦጭ አረም ሳቢያ በገጠመው ሥጋት ምክንያት የተሰባሰቡ ወጣቶች በጋራ አረሙ ላይ መዝመት ከጀመሩ እነሆ አምስተኛ ቀን አስቆጠሩ።

የሃይቁ ብክለትና በዙሪያው ያለውን የተፈጥሮ ይዞታ መጎዳት ሌላኛው ሥጋት እንደሆነና እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ይናገራሉ።

እምቦጭ በተሰኘው አረም እየተወረረ ያለውን የጣና ሃይቅን ለማፅዳት በበጎ ፈቃድ የተሰባሰቡ ወጣቶች ለሦስተኛ ጊዜ በሃይቁ ላይ ተሰማርተው አረሙን በማስወገድ ላይ ይገኛሉ።

Image copyright FB: Kalkidan Tsna

ችግሩ አሳስቧቸው የጣና ሃይቅና አካባቢው እንክብካቤና ጥበቃ በጎ አድራጎት በተሰኘ ማህበር ስር የተሰባሰቡ ወጣቶች የጀመሩት ይህ እንቅስቃሴ፤ ከባህር ዳርና አካባቢዋ ባሻገር ራቅ ካሉ ቦታዎችም የሚመጡ የበጎ ፈቃድ ተሳታፊዎችን በማሰማራት አረሙን የማስወገድ ሥራ እየሰሩ መሆኑን የማህበሩ ሰብሳቢ ቃልኪዳን ፀና ይናገራል።

ቃልኪዳን እንደሚለው አረሙን ለማንሳሳት ከተለያዩ ተቋማት ካገኙት ውስን ድጋፍ ባሻገር የበጎ ፈቃድ ተሳታፊዎቹ ባገኙት መሳሪያ እየተጠቀሙ ነው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ወጣቶቹ በበጎ ፈቃድ የበኩላቸውን ለማበርከት መነሳታቸው መልካም ነገር ቢሆንም፤ ከዘመቻው በፊት ግን ስለ እንቦጭ አወጋገድ እና ሌሎች የጤና ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ መስጠት ያስፈልጋል። ለምሳሌ አረሙን የሚነቅሉ ሰዎች ጓንት፣ ውሃ የማያስገባ ልብስና ጫማ በመልበስ ራሳቸውን ከቢላርዚያ መከላከል ይኖርባቸዋል ይላሉ።

በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ የተሰማሩት ወጣቶች በዋነኝነት ትኩረታቸውን በእምቦጭ አረም ላይ ያድርጉ እንጂ ሃይቁን ከብክለትና በዙሪያው ያለው አካባቢ መልሶ ወደቀድሞ ይዞታው እንዲመለስ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ገልፀዋል።

ተያያዥ ርዕሶች