ኪም ጆንግ ኡን ፍላጎታቸው ምን ይሆን?

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ እልፍ አህጉራትን የሚያካልል ሚሳኤል ሙከራ ካደረጉ በኋላ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ደስተኛውን እንዲህ ገልፀዋል።

ወርሃ ሐምሌ ላይ ሰሜን ኮሪያ ሁለት ባህር ተሻጋሪ ባለስቲክ ሚሳኤሎች ሙከራ ካደረገች በኋላ ነገሮች መክረር ጀምረዋል። በዚህም ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቅጣት አስተላልፏል። ሰሜን ኮሪያ እና አሜሪካም የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። ግን ግን ይህን ሁሉ ውዝግብ የምትፈጥረው ሀገረ ሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ንግ ኡን ፍላጎታቸው ምን ይሆን?

አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መሳሪያ ማምረቷን እንድታቆም ምን ልታደርግ ትችላለች? ማለትም በሰላማዊ መንገድ።

በሰሜን ኮሪያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው የቃላት ጦርነት በተለይ ከትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆኖ መሾም በኋላ እየከረረ መጥቷል። ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካዋ ጉዋም ግዛት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ብትሞክር እሳት ይዘንብባታል ማለታቸውን ተከትሎ ሰላማዊው መንገድ ምን ያህል ሊያራምድ እንደሚችል ግራ አጋቢ ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሬክስ ታይለርሰንን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት ሰላማዊ መንገድ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው ሲሉ መደመጣቸው ይታወሳል። ትራምፕ ባለፈው ጊዜ የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ ኡንን አግኝተው ለማናገር እንደሚፈልጉ መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ሰሜን ኮሪያ ግን ሰላማዊው መንገድን መምረጥ የፈለገች አትመስልም።

በቅርቡ በተካሄደው የአህጉረ እስያ ጉባዔ ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ታይለርሰን እና የሰሜን ኮሪያ አቻቸው ሪ ዮንግ ሆ ሊያደርጉት ታስቦ የነበረው ውይይት ሳይሳካ ቀርቷል። እንዲሁም በደቡብ ኮሪያ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል የታቀደው ንግግርም መክኗል። ለውይይቶቹ አለመሳካት ሰሜን ኮሪያ ድርሻውን እንደምትወስድ ነው የተዘገበው።

Image copyright Reuters

በመርህ ደረጃ አሜሪካ ለሰሜን ኮሪያ ልታቀርብ የምትችላቸው ሰላማዊ መንገዶች አሉ። የጦር መሳሪያን ከማውደም ጀምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግባባት መድረስ አሜሪካ እንደ አማራጭ ልትጠቀማቸው የምትችላቸው ሰላማዊ መንገዶች ናቸው። ነገር ግን መሰል ሂደቶች እንዲሳኩ በሁለቱም ወገን ቀናነት እና ጊዜ ወስዶ ስምምነት ላይ መድረስ ይጠይቃል። ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ የምታቀርብላትን ሰላማዉ አማራጭ ጥሳ በተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራ መፈፀሟ ደግሞ መሰል መንገዶች አዋጭነታቸው ምን ያህል እነደሆነ እንድንጠራጠር አድርጎናል።

አሁን ላይ እንደተሻለ እና ብቸኛ ምርጫ እየተወሰደ ያለው አማራጭ በተባበሩት መንግስታት በኩል ሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ምጣኔ ሀብታዊ ቅጣቶችን መጣል ነው። በተለይ የማዕድን እና ምግብ ወጪ ንግድ ላይ እገዳ በመጣል የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ማሽመድመድ እንደዋነኛ ምርጫ እየተወሰደ ይገኛል።

• ሰሜን ኮሪያን በምን መመከት ይቻላል?

እና ለምን?

ኪም ጁንግ ኡን እ.አ.አ. በ2011 ወደስልጣን ከመጡ ጀምሮ ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ። እኒህ ሁለት አበይት ግቦችም የጦር ሀይላቸውን ማዘመን እና የሀገራቸውን ምጣኔ ሀብት ማበልፀግ ናቸው።

የሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር ማብላላት ጉዳይ ከ1960ወዎቹ ጀምሮ የነበረ ሲሆን በታሪካዊ ተቀናቃኞቿ አሜሪካ፥ ጃፓን እንዲሁም ደቡብ ኮሪያ ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት ያለመ አንደሆነም ይተነተናል። እንዲሁም ከታሪካዊ አጋሮቿ ቻይና እና ሩስያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደሚያጠነክረውም ይነገራል።

በሊቢያ እና ኢራቅ ላይ የደረሰው ውድመት ትምህርት የሆናት ሰሜን ኮሪያ ጦር መሳሪያ መታጠቅን እንደዋነኛ መከላከያ ወስዳዋለች። አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ጦር የመግጠም ምንም ፍላጎት የለኝም ብላ በተደጋጋሚ ብታስረግጥም ሰሜን ኮሪያ ግን ወደ 28 ሺህ የሚሆን ጦረኛ በደቡብ ኮሪያ ያሰለፈችውን አሜሪካ ማመን አልቻለችም። ከዛም በላይ በ1953 ዓ.ም በተካሄደው የኮሪያ ጦርነት አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ተቃራኒ በመሆን የነበራት ቀጥተኛ ተሳትፎ ሰሜን ኮሪያውያን አሜሪካንን እንደ ዘላለማዊ ጠላት እንዲያይዋት ምክንያት ሆኗል።

በተለይ ደግሞ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ላይ ዓለም ባላየው መልኩ 'እሳት እናዘንባለን' ማለታቸውን ተከትሎ ኪም ጆንግ ኡን አቅማቸውን ለማሳየት የሚሳኤል ሙከራዋች ማካሄዳቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

Image copyright EPA

ውክሌር የታጠቀች ሰሜን ኮሪያ እና አሜሪካ እንዴት ይዘልቁ ይሆን?

የቅርብ ጊዜ የአሜሪካ ስለላ ውጤት እንደሚያሳየው ሰሜን ኮሪያ በትንሹ ስድሳ የሚሆኑ የኒውክሌር ቦምቦች ባለቤት ናት። እርግጥ ቁጥሩን የተሳሳተ ነው ሲሉ አንዳንድ ተንታኞች ይሞግታሉ። ቢሆንም ግን በወርሃ ሀምሌ በቀን 2 እና 28 ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች ሀገሪቱ አሜሪካን ለማጥቃት የሚያስችል አቅም ማጎልበቷን ማሳያ ነው።

አሁን ላይ ሰሜን ኮሪያ ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር ቢኖር የሚሳኤል ሙከራዎቿን በማጣደፍ እና አቅሟን ለአሜሪካ እና አጋሯቿ ማሳየት ነው። ይህ ለኪም ጉልበት መበርታት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። እርግጥ አሁን አሁን ለውጥ ማሳየት ብትጀምርም የሰሜን ኮሪያ አጋር የሆነችው ቻይናም ለተባበሩት መንግስታት የቅጣት ሀሳብ ብዙም ስትጨነቅ አይስተዋልም።

አሁን ላይ መጫወቻ ካርዱ በአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እጅ ላይ እንዳለ ተንታኞች ያስረዳሉ። ትራምፕ የሚሰንዝሯት እያንድንዷ ቃል ለሰሜን ኮሪያ ቀጣይ እርምጃ ትልፅ አስተዋፅኦ አላት። ባሳለፍነው ሀምሌ ወር መጨረሻ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ላይ 'እሳት እናዘንባለን' ማለታቸውን ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካዋ ጉዋም ግዛት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መጋጀቷን መግለጿ የሚታወስ ነው።

እርግጥ በአሜሪካ ታሪክ ማንኛውም ፕሬዝደንት አሜሪካ ላይ የሚቃጣ ቀጥተኛ ጥቃት ታግሶ አያውቅም። ቢሆንም ከሰሜን ኮሪያ ጋር ባለው ጉዳይ በአሜሪካ ግዛት አቅራቢያ ያለ ውቅያኖስ ላይ ሊወድቅ የሚችል ሚሳኤል ወደ ጦርነት ሊመራ መቻሉ እሙን ነው።

የቃላት ጦርነት፥ የሚሳኤል እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ሙከራ እነዲሁም የሀያላን መንግስታት መሪዎች የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በክልላዊ ብሎም በዓለም መፃኢ ዕጣ ላይ ጉልህ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ግን ሳይታለም የተፈታ ነው።