''ሙያችን መልክ ቢይዝ የትራፊክ አደጋን መቀነስ ይቻላል!'' የአዲስ አበባው ምርጥ ባርቴንደር።

የአዲስ አበባውን ምርጥ ባርቴንደር ይተዋወቁ !

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የትራፊክ አደጋና የባርቴንዲግ ሙያ ምን ያገናኛቸዋል?

መልከፃዲቅ ምትኩ ይባላል። በራዲሰን ብሉ ሆቴል ባር (መጠጥ ቤት) ስራ አስኪያጅ ነው። ከአራት ዓመታት በፊት ነበር በአስተናጋጅነት የሥራ ዘርፉን የተቀላቀለው። በቅርቡ በተካሄደ የባርቴንደሮች (የመጠጥ ቀማሚዎች) ውድድር መልከፃዲቅ ከብዙ ባለሙያዎች ልቆ 'የአዲስ አበባ ምርጥ ባርቴንደር' (መጠጥ ቀማሚ) ተብሎ ተሸልሟል።

ባርቴንደር ማለት የመጠጥ ድብልቆችን በመፍጠር ወይም የተለመዱ የመጠጥ ደብልቆችን፣ ለስላሳና የታሸጉ መጠጦችን ከባንኮኒው ጀርባ በመሆን የሚያሰተናግድ ባለሙያ ማለት ነው።

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምሩቅ የሆነው መልከፃዲቅ ወደዚህ ሙያ እንዴት እንደተሳበ ሲናገር ''አስተናጋጅ ሆኜ እሰራ በነበረበት ወቅት ባርቴንደሮችን የመርዳት ግዴታም ነበረብኝ። ይህም ሃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ ባርቴንደሮች ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት አስተዋልኩ። እንደማስበው ደንበኞቻችን ለሥነ-አዕምሮ ሃኪሞቻቸው የሚያካፍሉትን መረጃ ዓይነት ለባርቴንደሮች ይነግራሉ። ባርቴንደሮች ከደንበኞቻቸው ጋር እጅግ ጥሩ የሚባል ግንኙነት ነው ያላቸው ይህም ወደ ሙያው እንደሳብ አድርጎኛል'' ይላል።

አጭር የምስል መግለጫ ''ባርቴንደሮች ከደንበኞቻቸው ጋር እጅግ ጥሩ የሚባል ግንኙነት ነው ያላቸው ይህም ወደ ሙያው እንዽሳብ አድርጎኛል'' ሲል መልከፃዲቅ ይናገራል

የትራፊክ አደጋና የባርቴንዲግ ሙያ

መልከፃዲቅ የባርቴንዲንግ ሙያ የትራፊክ አደጋን ሊቀንስ እንደሚችል ያምናል።

መልከፃዲቅ እንደሚለው ስራውን የሚያከብር ባርቴንደር ሙያው የሚለውን አጣምሮ ነው የሚሰራው። ይህም በምንም አይነት ሁኔታ ደንበኞች በመጠጥ ተፅዕኖ ውስጥ ሆነው አንዳያሽከረክሩ ጥንቃቄ ያደርጋል።

ወደፊት መሠረታዊ የሆነ የባርቴንዲንግ ሙያን የሚያሰለጥን ተቋም በመክፍት በሃገራችን ጠጥቶ በማሽከርከር የሚከሰትን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እንደሚፈልግ ይናገራል።

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያን ባህላዊ መጠጦች ከውጪ ሃገር መጠጦች ጋር በመቀላቀል ተወዳጅ ጣዕምን መፍጠር ከእቅዱ አንዱ ነው።

አልፋ ሞሂቶ

''በበርካቶች የተወደደልኝ የራሴ የሆን አልፋ ሞሂቶ ብዬ የሰየምኩት የመጠጥ ድብልቅ አለኝ። ሞሂቶ በዓለም-አቀፍ ደረጃና በደንበኞቼ ዘንድ የተወደደ መጠጥ ነው። ይሁን እንጂ ይህ መጠጥ ጠንካራ አይደለም። ብዙዎቹ የእኔ ደንበኞች ደግሞ ጠንከር ያለ መጠጥን ይመርጣሉ። ሰለዚህ የእነሱን ፍላጎት ለሟሟላት ተኪላን በመጨመር የአልኮል መጠኑን ከፍ በማድረግና ሁሉም ግብዓቶች በትክክለኛ መጠን ላይ መሆናቸውን በማረጋገጥ የተወደደ ጣዕምን መፍጠር ችያለሁ'' ይላል።

''ከኔ ልምድ እንደተረዳሁት በሙያ ዘርፉ ብቁ ሆኖ ለመገኘት ዋናው ቁም-ነገር ለሙያው ጥልቅ የሆነ ፍላጎት መኖሩ ነው'' የሚለው መልከፃዲቅ፤ ከመጠጦች ጀርባ ላይ ያለውን ጽሁፍ በማንበብ ብቻ ስለ መጠጡ መሰረታዊ የሆኑ መረጃዎቹን ማግኘት ይቻላል። በተጨማሪም ከተለያዩ ድረ-ገፆች ላይ ብዙ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል" ሲል ይናገራል።