ቴዲ አፍሮን ለምን?

Image copyright Teddy Afro/Facebook

ከስንት ውጣ ውረድ ወጪና ድካም በኋላ ዛሬ ይቀርባል ተብሎ የተጠበቀው የቴዲ አፍሮ የአልበም ምረቃ ዝግጅት እስካሁን ባልታወቀ ምክንያት ተከልክሏል። 1,000 ለሚሆኑ ለቴዲ አፍሮ ቤተሰቦች፣ አድናቂዎችና የስራ ባልደረቦች ቅዳሜ እለት የመግቢያው ካርድ ከተበተነ በኋላ ነው አዘጋጅ ቡድኑ ለፕሮግራሙ ወደ ሂልተን ሲያቀኑ መስሪያቸውን እንዳያስገቡ የተከለከሉት።

ሰኞ ነሀሴ 26፥ 2009 ዓ.ም. ረፋድ ላይ 'ኢትዮጵያ' ከተሰኘው ከቴዲ አፍሮ አምስተኛ የስቱድዮ አልበም አሳታሚ እና አከፋፋይ ጆይስ ኤቨንትስ ሄኖክ ተፈራ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው የስልክ ቆይታ ለዝግጅቱ አንድ ሚሊዮን ብር ለሆቴሉ እንዲሁም ተጨማሪ ገንዘብ ለሽልማት፥ ለተጋባዥ ድምፃዊያን እና ለመሳሰሉ ዝግጅቶች ወጪ መሆናቸውን ተናግሯል።

የአልበም ምረቃውን ድጋሚ ለማዘጋጀት መወሰን አለወሰናቸውን ከድምፃዊው ጋር ተመካክረው በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚያሳውቁ ሄኖክ ተናግሯል።

በማህበራዊ ሚድያ ላይ የድምፃዊው አድናቂዎች እና ወዳጆች በአልበም ምረቃው መሰረዝ የተሰማቸውን ሀዘን እየገለፁ ይገኛሉ። ብዙዎች ለምን ቴዲ አፍሮ በማለትም ጥያቄያቸውን እየሰነዘሩ ነው። የአልበም ምረቃ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ጆርካ ኤቨንትስ ለኮንሰርት ካልሆነ መሰል ዝግጅቶችን ለማዘጋጀት ፈቃድ ተጠይቀው እንደማያውቁ አስታውቋል።

ድምፃዊው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መባቻን ምክንያት በማድረግ ‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘውን አልበም ካወጣ በኋላ የመጀመርያውን የሙዚቃ ድግስ በሚሊኒየም አዳራሽ ሊያካሂድ አቅዶ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሰላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ፈቃድ ማሳወቂያ ክፍል ፈቃድ ባለማግኘቱ መሰረዙም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

እና ለምን ቴዲ አፍሮ ላይ ብቻ? የሚለው ጥያቄ ቢነሳ የሚገርም አይሆንም። እርግጥ ቴዲ አፍሮ አወዛጋቢነቱ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ በፊት እ.አ.አ. 2008 ላይ ሰው ገጭቶ በመጥፋት ወንጅል ተፈርዶበት መታሰሩ ይታወሳል። ምንም እንኳ ድምፃዊው ጉዳዩ ፖለቲካዊ ተፀዕኖ አለበት ቢልም።

ቢቢሲ የቴዲ አፍሮን ማናጀር ጌታቸው ማንጉዳይን አናግሮ ባገኘው መረጃ አስካሁን ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ለድምፃዊው እና ለአዘጋጆቹ መግለጫ አልሰጠም። በተጨማሪም ቢቢሲ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ስልክም እየሰራ ባለመሆኑ ሰው ማግኘት አልተቻለም።

በጉዳዩ ላይ ፖሊስ እና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መግለጫ ሊሰጥ እንደሚችል ይጠበቃል።