የበርማ ሙስሊሞች ጩኸት!

Image copyright AFP

ከምያንማር ወይም በቀድሞ አጠራሯ በርማ ተሰደው ወደ ባንግላዲሽ የሚገቡ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው። እንደ ተባባሩት መንግስታት መግለጫ ከሆነ በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ወደ 35 ሺህ የሚሆኑ በርማውያን ሙስሊሞች ወደ ባንግላዲሽ ገብተዋል።

እ.አ.አ. ከነሃሴ 25 ጀምሮ ባለው ጊሴ ውስጥ ብቻ ወደ 123 ሺህ የሚሆኑ የሮሂንጃ ምሰሊሞች በርማ ሸሽተው መሰደዳቸው ተነግሯል። የሮሂንጃ ታጣቂዎች በምያንማር ፖሊሶች ላይ በከፈቱት ተኩስ ምክንያት የተቀሰቀሰው ግጭት የሮሂንጃ ሙስሊሞች ቀየአዘውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል።

የሮሂንጃ ሙስሊሞች ሀገር አልባ አናሳ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሲሆኑ ከምያንማር ቡድሂስቶች ጭፍጨፋ እና ግድያ እየደረሰባቸው ነው። ሮሂንጃዎችን ከሀገራቸው ጠራርገው ለማስወጣት በሚል የምወያንማር ጦር የሮሂንጃ ምሰሊሞችን ቤት እያቃጠለ እና ሰውም እየገደለ እንደሚገኝ ተዘግቧል። የምያንማር ጦር እየተዋጋሁ ያለሁት የሮሂንጃ ነፃ አውጪዎችን ነው በማለት ጉዳዩን መፈፀሙን ይክዳል።

ጉዳዩን በገለልተኛነት ለማጣራት ወደ ቦታው መግባት ከሚያመጣው አደጋ አንፃር እጅጉን ከባድ ነው። ነገር ግን ወደ ባንግላዲሽ ዕቃቸውን ጠቅልለው ወደባንግላዲሽ የሚገቡ የሮሂንጃ ሞስሊሞች ቁጥር እጅጉን አሻቅቧል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምግብ እና መጠለያ የሚያሻቸው የሮሂንጃ ምሰሊሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ጉዳዩ ኣሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል።

ድርጅቱ ስደተኞቹን ለመቀበል ያዘጋጃቸው ሁለት መጠለያዎች መሙላታቸውን አስውቋል። የተቀሩት ሰዎች ውጭ ላይ እነዲሁም መንገድ ዳር እየተኙ ይገኛሉ።

"ግድያው ሲጀመር ወደ ተራራው ሮጠን ወጣን። ከዛም ጦሩ ቤታቸንን አቃጠለብን" ሲል ለሬውተርስ ዜና ወኪል የተናገረው በግብርና ስራ ይተዳደር የነበረው የሮሂንጃ ሙስሊሙ ሳሊህ ኡላህ ነው። "እናቴን፥ ሚስቴን እና ሁለት ልጆቼን ይዤ ከሌሎች አራባ ሰዎች ጋር በጀልባ ተሳፍሬ ወደዚህ ተሰደድኩ። ጀልባው ውስጥ 25 ሴቶች እንደነበሩ ትዝ ይለኛል' በማለት ያክላል ሳሊህ።

የተባበሩት መንግስታት መረጃ እንደሚጠቁመው አሁንም ግጭቱ ረካይን በተሰኘችውና የሮሂንጃ ሙስሊሞች በሚበዙባት ቦታ ቀጥሏል። በባንግላዲሽ ወደብ አካባቢ እንኳን 15 የሚሆኑ የቃጠሎ ጭሶች እንደታዩ ዘገባው ይጠቁማል።

Image copyright Reuters

በሌላ በኩል ደግሞ በመልሱ ማጥቃት ድርጊት የተሰማሩት የሮሂንጃ ነፃ አውጪዎች የበርማ ቡዲሂስቶችእ እየገደሉ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል። ለቢቢሲ በርማ አገልግሎት ድምጿን የሰጠች አንዲት ግለሰብ እንደተናገረችው ነፃ አውጪዎቹ በጎራዴ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ናቸው።

በጉዳዩ ላይ እስላማዊ ሀገራት ያሳዩት ቸልተኝት ለትችት ዳርጓቸዋል። እርግጥ ዘግይቶም ቢሆን ኢንዶኔዢያ በጉዳዩ ላይ ድምጿን በማሰማት ቀዳሚ ሆናለች። ፓኪስታን እና ማሌዢያም ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው አሳውቀዋል። ማልዲቭ ደግሞ ከምያንማር ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ማቋረጧን አስታውቃለች። የቱርክ ፕሬዝደንት ጣይብ ኤርዶዋን በበኩላቸው የበርማዋ መሪ ኣውንግ ሳን ሱ ኪ ለግጭቱ መፍትሄ እንዲያበጁ አሳስበዋል።

ሰኞ ዕለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ባለስልጣን የሮሂንጃ ሙስሊሞች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዲሞክራሲ በመታገል የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆኑት የበርማ መሪ ኣውንግ ሳን ሱ ኪ ስለጉዳዩ አስተያየት እንደሚሰጡም ይጠበቃል። መሪዋ የምያንማር ጦር እየፈፀመ ያለው ግፍን ማስቆም እንዳለባቸው እየተነገረ ቢሆንም የሮሂንጃ ሙስሊሞች ከሀገራቸው እንዲወጡ ከሚፈልጉት በርማውያን እና ከጦሩ ከፍተኛ ተቃውሞ ሊገጥማቸው እንደሚችልም እየተነገረ ነው።

ባለፈው ወር የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ 43 ሺህ የሚሆኑ የሮሂንጃ ሙስሊም ስደተኞችን ህገ-ወጥ በመሆናቸው ምክንያት ከሀገራቸው ለማስወጣት ማቀዳቸውን ይታወሳል።

ምያንማር የሮሂንጃ ሙስሊሞችን እንደዜጋ አትቀበላቸውም። በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ስደተኞቸው መጠለያ የሰጠችው ባንግላዲሽም ተመሳሳይ አቋም ይዛለች። በዚህ ሁኔታ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ሀገር አልባ ሆነው በስደት እና ስቃይ ላይ ይገኛሉ።