በግንባታዎች ምክንያት እየጨመረ የመጣው የአሸዋ ፍላጎት ወንዞችን እያጠፋ ነው

አሸዋ

እርግጥ ያለ አሸዋ ኮንክሪት አይሰራም። በብዙ የአፍሪቃ ገራት የሚገኙ ወንዞች ለአሸዋቸው ሲባል እየተሟጠጡ ይገኛሉ። በዚህ በኩል በአሸዋ ሕንፃ ይገነባል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የወንዞች ህልውና አደጋ ላይ እየወደቀ ይገኛል።

አሸዋ

የወብ ወሃ ዳርቻዎች ማሳመሪያ፤ የምዕተ ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠራቸው ደቂቅ እና አንፀባራቂ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ድንጋዮች ስብስብ፤ አሸዋ። አባባሉም እንደ አሸዋ ያብዛችሁ ነውና አሸዋ ቁጥር ስፍር የሌለው ነገር ቢመስለንም አሁን ላይ አደጋ ከተጋረጠባቸው የምድራችን ሀብቶች አንዱ ሆኗል።

ቆም ብለን ብናስብበት እውነታው ሊገለጥልን ይችላል። ሁሉም የሕንፃ መሰረታዊያን ማለትም እነኮንክሪት፣ ጡቦች፣ እንዲሁም መስተዋት ከአሸዋ ነው የሚሰሩት። እጅጉን እየጨመረ የመጣው የሰው ልጅ ቁጥር እና በፍጥነት በማደግ ላይ ያለው የግንባታ ዘርፍ አሸዋን ከውሃ ቀጥሎ በምድራችን ላይ በጣም ተፈላጊው ተፈጥሯዊ ሀብት አድርጎታል። በቢሊዮን ቶን የሚቆጠር አሸዋ በየቀኑ በዓለም ዙሪያ ጥቅም ላይ ይውላል።

የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት እንደሚያሳየው እ.አ.አ. ከ2012 ጀምሮ በዓለማችን ጥቅም ላይ የዋለው አሸዋ በምድር ወገብ ዙሪያ 27 ሜትር ከፍታ እና 27 ሜትር ስፋት ያለው የኮንክሪት አጥር መስራት ይችላል። በአሸዋ ለመከበብ የባህር ዳርቻዎች ጋር መሄድ አይጠበቅብንም። ዙሪያችንን የከበቡን መኖሪያ ቤቶች እና መሰል ሕንፃዎች በኮንክሪት መልክ የቆሙ አሸዋዎች ናቸው።

ለግንባታ የሚውለው አሸዋ በዋነኛነት ከወንዞች ስር እና ከውቅያኖሶች ግርጌ የሚመጣ ነው። የበረሃ አሸዋ ከሌሎች የግንባታ ምርቶች ጋር ለመቀላቀል በጣም አመቺ የሆነ ተፈጥሯዊ ሀብት ነው። ትላልቅ የዱባይ የግንባታ ዕቅዶች በሀገሪቱ ዙሪያ የሚገኙ አሸዋዎችን ከማራቆታቸው የተነሳ በአሸዋ ላይ የተገነባችው ከተማ ዱባይ አሁን ላይ ከአውስትራሊያ አሸዋ ማስመጣት ጀምራለች።

የአሸዋ ፍላጎት በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመድረሱ የተነሳ በሥነ ምህዳር ላይ ከሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ባለፈ ለሰው ሕይወት መጥፋት መንስኤ መሆን ጀምሯል።

በህንድ በነውጠኛ ማፊያዎች እየተመራ የአሸዋ ጥቁር ገበያ ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅጉን ደርቷል። በቻይና የሀገሪቱ ትልቁ የንፁህ መጠጥ ውሃ ምንጭ የሆነው የፖያንግ ሀይቅ በአሸዋ ቁፋሮ ምክንያት መድረቅ ጀምሯል። በወንዙ አከባቢ የሚኖሩ እና በዓሳ ማጥመድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች እና በወንዙ ዙሪያ የሚኖሩ ወፎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል።

የሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በ2040 በእጥፍ እንደሚያድግ በሚጠበቅባት ኬንያ እንደ የባቡር መንገድ ዝርጋታ ያሉ ትላልቅ የግንባታ ዕቅዶች በብዙ ቶን የሚቆጠር አሸዋ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። የኬንያ የባህር ዳርቻዎች እና ወንዞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሸዋ ቁፋሮ ምክንያት እጅጉን መራቆት ጀምረዋል። ነገር ግን እንደ ማኩዌኒ ባሉ ዝቅተኛ ኑሮ በሚገፉ አከባቢዎች የአሸዋ ቁፋሮ ነዋሪዎችን ያለመጠጥ ውሃ እያስቀረ ይገኛል።

ለግማሹ አሸዋ ሕይወት ሲሆን ለግማሹ ደግሞ ገንዘብ ነው። በማኩዌኒ ፖሊስ ጣቢያ አፊሰር የነበረው ጄዎፍሪ ካስዮኪ በአካባቢው የአሸዋ ቁፋሮን በመከላከል በጣም የተመሰገነ ስራ የሰራ ግለሰብ ነበር። በየካቲት 2011 ግን በጠራራ ፀሀይ አሸዋ ቆፋሪ ወጣቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው ሬሳውን ጥለውት ሄዱ። ባለቤቱ አይሪን ስትናገር ''ወጣቶቹ ይህን ያደረጉት ሌሎች አሸዋ ቁፋሮን በማገድ ድርጊት ላይ ለተሰማሩ ሰዎች መልዕክት ለማስተላለፍ በማሰብ ነው'' ትላለች።

በማኩዌኒ በግብርና ስራ ላይ የተሰማራው አንቶኒ በአከባቢው በአሸዋ ቁፋሮ ምክንያት የጠፋውን ኪሎሜ ኢኮልያ ወንዝን በትካዜ እየቃኘ ይሄንን 'የሞተው ወንዝ' እንለዋለን ይላል። ''ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህ ወንዝ እንደልብ የሚፈስ ነበር። አሁን ግን አስር ሜትር ይህል ገብቶ ባዶውን ቀርቷል'' ባይ ነው አንቶኒ።

አንቶኒ በደረቀው ወንዝ ዙሪያ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በጠራራ ፀሀይ በቡድን በአሸዋ ቁፋሮ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ተመለከተ። ሰዎቹ የቆፈሩትን አሸዋ ወደጭነት መኪና ለመጫን ዝግጅት ላይ ነበሩ።

አሸዋ የልጅነት የወንዝ ዙሪያ ትዝታ ሆኖ ሊቀር ይሆን ብለን በምንጭነቅበት ወቅት ሌሎች ግን በጣም የሚያሳስባቸው ጉዳይ አለ። እንደተባለው አሸዋ ለግማሹ ሕይወት ሲሆን ለግማሹ ደግሞ ገንዘብ ነው። በልቶ በማደር እና በመራብ መካከል፤ የመጠጥ ውሃ በማግኘት እና ባለማግኘት መካከል ያለ፤ ባጠቃላይ አሸዋ በሕይወት እና በሞት መካከል ያለ ጉዳይ መሆን ጀምሯል።