በህንድ ጥቅም ላይ የዋሉ የንፅህና መጠበቂያ ጨርቆች ለምን ተፈለጉ?

  • በሲቫ ፓራሜስዋራን
  • ከቢቢሲ የታሚል ቋንቋ አገልግሎት
የንፅህና መጠበቂያ ጨርቆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የወር አበባ በህንድ ሀገር በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች እንደ ነውር የሚቆጠር ነገር ነው። ስለ ወር አበባ መናገርም እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ተደርጎ ይቆጠራል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ከህንድ ሴቶች ጥቅም ላይ የዋሉ የንፅህና መጠበቂያ ጨርቆች መሰብሰብ ምን ያህል ሊከብድ እንደሚችል አስቡት።

ነገር ግን በህንድ ማሃራሽትራ ግዛት የተሰማሩ ተመራማሪዎች ይህንን ከመፈፀም ያገዳቸው ነገር አልነበረም። ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት ደግሞ የሚሰበስቡት ጥቅም ላይ የዋለ የንፅህና መጠበቂያ ጨርቅ የማህፀን በር ካንሰርን ለመመርመር እንዲያስችላቸው ነበር።

በዓለማችን ካሉ የማህፀን በር ካንሰር ታማሚዎች ሩብ ያህሉ የሚገኙት በህንድ ሃገር ነው። እንዲያም ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው ህንዳውያን ሴቶች አሁንም የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ አያደርጉም። የጤና ማዕከላት በአስፈላጊው መጠን አለመኖር እና ህክምናውን ለማግኘት የሚጠየቀው ከበድ ያለ ወጪ ሰዎች ምርመራውን እንዳያደርጉ ከሚያግዱ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ህንዳውያን ሴቶች ከዘመናዊዎቹ የንፅህና መጠበቂያ ጨርቆች በተቃራኒ ቤት አፈራሽ ጨርቅን በወር አበባ ጊዜ ለንፅህና መጠበቂያነት ይጠቀማሉ። ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ከሆነ እነዚህን ጥቅም ላይ የዋሉ የንፅህና መጠበቂያ ጨርቆች በመጠቀም የማህፀን በር ካንሰር አምጪ ቫይረስ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል።

''በጣም ቀላል እና አመቺ መንገድ ነው" ይላሉ የምርምር ቡድኑ መሪ ዶክተር አቱል ባዱክ። ጨምረው ሲናገሩም "ምርምራችንን በድንብ እንዳናካሂድ ያገደን ነገር ቢኖር የሴቶች ፈቃደኛ አለመሆን ነው።'' ተመራማሪዎቹ እንደሚናገሩት የህንድ ሴቶች የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ የሚደርግላቸው በሌላ የጤና እክል ምክንያት ወደ ጤና ተቋም ሲመጡ ነው።

ቀዘቃዛ ዘረ-መል

ሁለት ዓመት ለሚፈጀው ምርምር ዕድሜያቸው ከ30-50 ዓመት የሆነ እና የካንሰር በሽታ የሌለባቸው 500 የሚሆኑ ሴቶች ተመርጠዋል። ተሳታፊዎቹ ሴቶች የወር አበባ ማየት በጀመሩ የመጀመሪያ ቀን የተጠቀሙበትን የንፅህና መጠበቂያ ጨርቅ በተሰጣቸው ባለዚፕ ቦርሳ ውስጥ እንዲያስቀምጡ እና በአካባቢው ላሉ የጤና ጥበቃ ሰራተኞች እንዲያቀብሉ ተነገራቸው።

የተሰበሰቡት የንፅህና መጠበቂያ ጨርቆች ከ20 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ባነሰ ሙቀት ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርጎ ወደ ምርምር ማዕከሉ ተላኩ። ዘረመሎቹ ከደረቁት የንፅህና መጠበቂያ ጨርቆች ላይ ከተወሰዱ በኋላ ምርመራው ተደረገ። በተገኘው ውጤትም ሃያ አራት ሴቶች የማህፀን በር ካንሰር አምጪ ቫይረስ እንዳለባቸው ታውቆ ለተጨማሪ የሕክምና እርዳታም ወደተሻለ የጤና ማዕከል ተላኩ።

የፎቶው ባለመብት, Dr Atul Budukh/TMC hospital

የመራቢያ አካላት ንፅህና

የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው የመራቢያ አካላትን ንፅህና አለመጠበቅ ለማህፀን በር ካንሰር አምጪ ቫይረሶች መፈጠር እና መራባት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል። በ2011 የተደረገው የህንድ ህዝብ ቆጠራ እንደሚያሳየው 41 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች መፀዳጃ ቤት የሌላቸው ሲሆን መፀዳጃ ቤት ካላቸው 16 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጣራ የሌላቸው መፀዳጃ ቤቶች ናቸው።

ዶክተር ባዱክ እንደሚያምኑት "በገጠር አካባቢዎች የመፀዳጃ ቤቶች እጥረት ስላለ ሴቶች የመራቢያ አካላቸውን ለማፅዳት ምቹ ቦታ የላቸውም።" ከዛም በላይ ጥቅም ላይ የዋሉ ጨርቆችን መልሶ መጠቀም ቫይረሱን እንደሚያባብሰው ዶክተር ባዱክ ያሳስባሉ።

ከወር አበባ ጋር በተያያዘ ህንድ ውስጥ ያሉት ባህል እና እምነቶች ለተመራማሪዎቹ ሥራቸውን እጅግ ከባድ እንዲሆን አድርጎታል። የወር አበባ የሚያዩ ሴቶች ማዕድቤት ውስጥ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም። ከዛም አልፎ በፀሎት ሥፍራዎች ላይ እንዳይኙና ሀይማኖታዊ ስርዓቶችን እንዳይካፈሉ ይደረጋሉ።

ወደ መፍትሄው

የማህፀን በር ካንሰርን መከላከያ መንገዶችን የሚያሳዩ የጤና ትምህርቶች በተለይ ደግሞ ለጎሳ መሪዎች፣ ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት ለሚሰሩ ሰራቶኞች እንዲሁም ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ማስተማር ሴቶች ከማህፀን በር ካንሰር ራሳቸውን እንዲጠብቁ ያደርጋቸዋል። ላቅ ሲልም የወር አበባን የተመለከቱ በጎ ያልሆኑ አመለካከቶችን ማስወገድ መቻል ለበሽታው አለመከሰት የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጥናቱ ጠቁሟል።

የጥናቱ አንድ ክፍተት ሆኖ የተመዘገበው የወር አበባ ማየት ያቆሙ እና ማየት ያልጀመሩ ሴቶችን አለማካተቱ ነበር። ዶክተር ባዱክ እንደሚጠቁሙት ግን ቢያንስ የወር አበባ የሚያዩ ሴቶችን በዚህ መንገድ የማህፀን በር ካንሰር እንዳለባቸው ከመለየት አልፎ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ማድረግ ተችሏል። እንደ አዲስ የማህፀን በር ካንሰር መመርመሪያ መሳሪያ ልትቆጥሩት ትችላላችሁ ይላሉ ዶክተሩ ሲያጠቃልሉ።