ሰሜን ኮሪያ 'አሜሪካ ታላቅ ስቃይ ይጠብቃታል' በማለት እየዛተች ትገኛለች።

ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ ላይ ቦምብ ለማዝነብ መዛቷን ቀጥላለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ተከትሎ የኪም ጆንግ ኡን መንግት አሜሪካ ለማዕቀቡ ተግባራዊነት የጎላ አስተዋፅኦ በማድረጓ ቅጣት ይጠብቃታል በማለት ዝቷል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰሜን ኮሪያ አምባሳደር ሀን ታይ ሶንግ የዋሽንግተን መንግሥት በሁለቱ ሀገራት መካከል ፖሊቲካዊ እና ወታደራዊ ግጭት ለማነሳሳት እየጣረ ነው ብለዋል። አምባሳደሩ መሰል ማዕቀቦች ህገ-ወጥ እና መፍትሄ አልባ ናቸው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማዕቀብ አሜሪካ ካሰበችው ጋር ሲነፃፀር ኢምንት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ድርጅቱ የጣለው ማዕቀብ ሀገሪቱ ነዳጅ እንዳታስገባ እና የጨርቃ ጨርቅ ምርቷንም ወደ ውጪ እንዳትልክ የሚያግድ ነው። የመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀቡን ሊያስተላልፍ የቻለበት ምክንያት ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ለስድስተኛ ጊዜ የሞከረችው ከባድ የኒውክሌር ሚሳኤል ሙከራ ነው።

በማዕቀቡ ላይ የመንግስታቱ ድርጅት አባላት ከተወያዩበት በኋላ ሩስያ እና ቻይና አሜሪካ ካቀረበችው ጠንከር ያለ ማዕቀብ በአንፃራዊነት ቀለል ያለ መሆን እንዳለበት ሀሳብ አቅርበው ማዕቀቡ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

አዲሱ የተ.መ.ድ ማዕቀብ

  • ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚገባ የነዳጅ መጠን እንዲቀንስ፤ በተለይ ደግሞ የሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የምጣኔ ሀብት አጋር ከሆነችው ቻይና የሚገባው ነዳጅ የተወሰነ እንዲሆን፤
  • 700 ሚሊዮን ዶላር በዓመት እንደሚያስገባ የሚገመተው የሰሜን ኮሪያ የጨርቃ ጨርቅ ንግድ ላይ እገዳ ማስተላለፍ፤
  • በዓመት 500 ሚሊዮን ዶላር ለሀገራቸው እንደሚያስገቡ በሚነገርላቸው በሌላ ሀገራት የሚሰሩ ሰሜን ኮሪያውያን ቪዛቸው እንዳይታደስ ማገድ፤

የሚሉትን ያካተተ ነው።

በሌላ በኩል አሜሪካ አቅርባው የነበር የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ንብረት እንዲሁም ራሳቸው መሪው ከሀገራቸው ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ የሚያግደው ማዕቀብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

በዕለተ-ማክሰኞ በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን ያንፀባረቁት ትራምፕ "ይህ በጣም ኢምንት የሆነ ማዕቀብ ነው። ይህን ያህል ትርጉም ያለው ነገር አይደለም'' ሲሉ፤ አክለውም "ማዕቀቡ በሙሉ ድምፅ ማለፉ አንድ ነገር ነው። ምንም እንኳ ያሰብነውን ማዕቀብ ማሳካት ባንችልም" ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጀት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ ለፀጥታው ምክር ቤት እንደተናገሩት "በተላለፈው ማዕቀብ በደስታ ልንጨፍር አንፈልግም። እኛ ጦርነት እያሰብን አይደለም" ብለዋል። "ሰሜን ኮሪያ በአደገኛው መንገድ መጓዟን ከቀጠለች እኛም ጫና ማሳደራችንን እንቀጥላለን። ምርጫው የራሳቸው ነው" በማለት አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰኞ ዕለት የተላለፈው ማዕቀብ ከ2006 ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያ ላይ ከተላለፉ ማዕቀቦች በሙሉ ድምፅ በመፅደቅ ዘጠነኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

ቀደምት ማዕቀቦች

• ህዳር 30. 2016፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያ ከቻይና ጋር ያላት የከሰል ንግድ በ60 በመቶ እንዲቀንስ እንዲሁም ሰሜን ኮሪያ የማዕድን ውጪ ንግድ ላይ የተወሰነ ቅጣት የሚያስተላልፍ ማዕቀብ፤

• ሰኔ 2. 2017፡ የመንግስታቱ ድርጅት በ14 የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ላይ ንብረታቸውን ጨምሮ ከሀገር ሀገር የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲታገድ የሚያዝ ማዕቀብ፤

• ነሀሴ 6. 2017፡ ድርጅቱ በሰሜን ኮሪያ ጠቅላላ የከሰል ንግድ ላይ እግድ ጣለ። የሰሜን ኮሪያ የከሰል ንግድ ለሀገሪቱ በዓመት 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስገባ ይታመናል።

የሰሜን ኮሪያ ዋነኛ ወዳጅ ቻይናም በማዕቀቡ መስማማቷን ገልፃ፤ ሰሜን ኮሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ህግጋት በመጠሷ ማዕቀብ ይገባታል ስትል በአምባሳደሯ አማካይነት ተናግራለች። አክላም ቻይና በአካባቢዋ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ፈፅሞ እንደማትፈቅድ ገልፃለች።

ሩስያ እና ቻይና ሁለቱ የቃላት ጦርነት ተሳታፊ ሀገራት ማለትም አሜሪካ እና ሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያቸውን እንዳያንቀሳቅሱ እና ሰላማዊ መንገድ እንዲምርጡ ማሳሳባቸውን አላቋረጡም።