ሰሜን ኮሪያን በምን መመከት ይቻላል?

የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል

የፎቶው ባለመብት, KCNA

ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ወደ ጃፓን የውቅያኖስ ክፍል ሚሳኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል። ሀገሪቱ ሙከራው በጠላቶቿ ላይ ልታደርግ ላሰበችው ጥቃት የመጀመሪያው እርምጃ እነደሆነ ተናግራለች። የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ሰሜን ኮሪያ ላይ ቅጣት ጥለውባታልም።

እርግጥ አሜሪካ በጦር መሳሪያ አቅም ከሰሜን ኮሪያ እጅግ የላቀች ሀገር ብትሆንም ሰሜን ኮሪያ ከምትፈፅማቸው ድርጊቶች እንድትታቀብ ለማድረግ ያላት አማራጭ ውሱን ነው። እና አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን ለመግታት ምን ዓይነት አማራጭ መጠቀም ትችላለች?

1. ስልታዊ ከበባ

ይህ አማራጭ በጣም ዝቅ ያለ ጉዳት ያለው አንደሆነ ቢነገርም ውጤታማነቱም ዝቅ ያለ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል። አሜሪካ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ያላትን የእግረኛ ጦር ቁጥር በመጨመር እንዲሁም የየብስ ላይ የሚሳኤል አቅሟን ማጠናከር ትችላለች።

ነገር ግን ደቡብ ኮሪያ ይህን የአሜሪካ ሀሳብ ለመቀበል እያንገራገረች ትገኛለች። ምክንያቱም ሰሜን ኮሪያን ለጦርነት ይገፋፋታል በሚል። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለውም ሰሜን ኮሪያ ይህንን የአሜሪካ እንቅስቃሴ ለየብስ ወረራ ዝግጅት እንደሆነ መጠራጠሯ አይቀርም።

ቻይና እና ራሺያም በዚህ ጉዳይ አሜሪካን ይደግፋሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። እንዲያም ሆኖ የአሜሪካ የባህር ሀይል በኮሪያ ባሀረ ሰላጤ ሁሪያ በመርከብ እና አውሮፕላኖች በማንዣበብ በማንኛውም ሰዓት የሚተኮስ ሚሳኤልን መከላከል ትችላለች።

ሰሜን ኮሪያ የበጣም በርካታ ባለስቲክ ሚሳኤል ባለቤት መሆኗ እና አሜሪካ ያሏት አቅጣጫ አስቀያሪ ሚሳኤሎች ውድ መሆን እና እንደልብ አለመገኘት ነገሮችን ለአሜሪካ የከበዱ እንዲሆኑ ሊያደርጉ ይችላሉ።

2. ቀጥታ ጥቃት

በምድራችን እንደ አሜሪካ ያለ ቀጥተኛ ጥቃት የማድረስ ከፍተኛ አቅም ያለው ሀገር የለም። አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ የባህር ዳርቻዎች በመነሳት በቦምብ የሀገሪቱን የሚሳኤል ክምችት በማጋየት ሰሜን ኮሪያን ማሽመድመድ ትችላለች። ነገር ግን በጥቃቱ ሂደት አሜሪካ የጦር አውሮፕላን ልታጣ ትችላለች። በዚህ በኩል አሜሪካ ምን ያህል ጉዳት ሊደርስባት እንደሚችል መገመት አዳጋች ነው። ምክንያቱም የሰሜን ኮሪያ አየር ሀይል ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ መገመት ስለማይቻል።

የአሜሪካ፥ ራሺያ እና አሜሪካ የጦር አቅም ባለፉት ሀምሳ ዓመታት በጣም የጠነከረ ቢሆንም ሀገራቱ ሰሜን ኮሪያን ለማጥቃት ያላቸው ዝግጁነት እንደ ወንዝ ድንጋይ ሙልጭልጭ ነው። ሰሜን ኮሪያ ጥቃት ቢደርስባትም በቀረ ሀይሏ ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ልታደርስ እንደምትችል እሙን ነው።

እንደሚገመተው ከሆነ ሰሜን ኮሪያ አንድ ሚሊዮን መደበኛ እና ስድስት ሚሊዮን ተጠባባቂ ጦር እንዲሁም የፓርላማ ወታደሮች እንዳሏት ይገመታል። የሮኬት መሳሪያዎች ክምችት ደግሞ የሚገኘው አስር ሚሊዮን ህዘብ ገደማ ላላት በደቡብ ኮሪያዋ ዋና ከተማ ሴኡል አቅራቢያ ነው። ለዚህም ነው የደቡብ ኮሪያ መንግስት ሰሜን ኮሪያን ወደ ጠብ የሚመራ እርምጃ እንዳይወሰድ አብዝቶ የምትጠነቀቀው።

3. ሙሉ በሙሉ ወረራ

ከላይ የተጠቀሱትን አማራጮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ አማራጭ ትክክለኛው ነው ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው። ሰሜን ኮሪያን ለመውረር መሞከር የአሜሪካን የወራት የጦር ዕቅድ፥ የደቡብ ኮሪያን የነቃ ተሳትፎ እንዲሁም የሰሜን ኮሪያን የሚሳኤል ክምችት ባለበት ዶግ አመድ ማድረጊያ ተኣምር ይጠይቃል። በሁለቱም ወገን የብዙ ሰዎች ሕይወት ሊያጠፋ የሚችል ነው።

አሜሪካ ለመጨረሻ ጊዜ ሰሜን ኮሪያን የወረረችው በ1950 በኮሪያ ጦርነት ወቅት ሲሆን ቻይና ሰሜን ኮሪያን ወግና ጠንካራ የተባበረች ኮሪያ እንዳትመሰረት የራሷን አስተዋፅኦ አበርክታለች። አሁንም ቻይና ወደ ሰሜን ኮሪያ ግድም ወግና የምትታየው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። ከዛን ግዜ ጀምሮ ሰሜን ኮሪያ ከዓለም ተነጥላ በከፋ ምጣኔ ሀብታዊ ሁነት ውስጥ ቆይታለች።

እውነታው ወዲህ ነው። የትኛውም አሜሪካ ያላት አማራጭ ያለ ጉዳት ወይም ኪሳራ የሚተገበር አይደለም። ጣጣው ከሁለቱ ሀገራት አልፎ ለዓለም የሚተርፍ እንደሆነም ልብ ይሏል።