ታዬ የህግ ድግሪውን አጠናቆ ለመመረቅ አስራስድስት ዓመታት ፈጅቶበታል።

ታዬ Image copyright Taye Dendea

ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ዲግሪ ሊጭን የተዘጋጀው ልጃቸውን ወግ ማዕረግ ለማየት የታዬ ደንደኣ ቤተሰቦች ጓጉተዋል። ባደገበት በሰሜን ሸዋ ኩዩ ከተማ የሚኖሩት ቤተሰቦቹ ለምረቃው ድግስ ዕቅድ ማውጣት ሁሉ ጀምረው ነበር።

ነገር ግን ብዙ የታሰበለት የታዬ ምረቃ ጉዳይ ድንገት የማለዳ ጤዛ ሆነ።

በ1996 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት የህግ ድግሪ ተማሪ የነበረው ታዬ በሽርተኝነት ወንጀል ተጠርጥሮ ለእስር ተዳረገ። አራት አስርት ዓመታትን በዚች ምድር የኖረው ታዬ በእስር ቤት የነበረውን ቆይታ እያስታወሰ በየመሃሉ ይተክዛል። "ማረሚያ ቤት ብዙ ነገር አስተምሮኛል። ብዙ እንዳነብ እና ከታላላቆቼ እና ከተማሩ ሰዎች ብዙ እንዳውቅ አግዞኛል" ይላል ታዬ።

ለሦስት ዓመታት ያህል በእስር ከቆየ በኋላ ክሱ እንዲታይ ወደ ፍርድ ቤት ተላከ። ክሱን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ከተጠረጠረበት የሽርተኝነት ወንጀል ነፃ በመሆኑ እንዲለቀቅ ወሰነ።

የጀመረውን ትምህርት ለመጨረስ ወደ የኒቨርሲቲ ተመለሰ። በሕይወቱ ካጋጠመው በመነሳት የመመረቂያ ወረቀቱን 'በሀሰት ለተወነጀሉ የሚሰጥ ካሳ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ልምድ ምን ያሳያል' በሚል ርዕስ መስራት ጀመረ። ታዬ እንደሚለው "በሀሰት የተወነጀሉ ሰዎች ካሳ ሊሰጣቸው ወይም ሊከፈላቸው ይገባል።"

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ታዬ የህግ ድግሪውን አጠናቆ ለመመረቅ አስራስድስት ዓመታት ፈጅቶበታል።

የእስር አዙሪት

ከእስር ቆይታ በኋላ ታዬ በ2001 ዓ.ም ሊመረቅ አራት ቀን ቀርቶታል። ቤተሰቦቹ እና ወዳጅ ዘመዶቹ እንዳለፈው ጊዜ ለድግሱ ሩጫቸውን እያጣደፉት ነው። ነገር ግን ታዬ እንደገና ለእስር ተዳረገ። አሁንም በሽርተኝነት ወንጀል ተጠርጥሮ ነው ወደ ወህኒ የወረደው። የኢትዮጵያ መንግስት በሽብር ቡድንነት ከፈረጀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጋር ግንኙነት እንዳለው እና ሰዎችን ሰብስቦ በኬንያ በማሰልጠን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጥቃት እንዲያደርሱ ልኳል በሚል ነበር የተከሰሰው።

ታዬ ሁለቱንም ወንጀል አልፈፀምኩም ሲል ያስተባብላል። "ሁለቱም ክሶች አደናጋሪና ብዙም ግልፅ ያልሆኑ ናቸው። ፍርድ ቤቱም በፍርዱ ወቅት ትክክለኛውን መንገድ አልተከተለም" ሲል ይወቅሳል።

ሆነም ቀረም ታዬ ለአስር ዓመታት እስር ወደ ማረማያ ቤት ተላከ። መጀመሪያም በቁጥጥር ስር ሲውል አስር ዓመት እንደሚያስፈርድበት የያዘው የፖሊስ መኮንን ዝቶበት ነበር። ይግባኝ ቢጠይቅም ተሰሚነት አላገኘም።

'ፀፀት የሚባል የለም'

"ማረሚያ ቤት ማለት በቀን ለ24 ሰዓታት የፈለከውን ነገር ማድረግ የምትችልበት ቦታ ማለት ነው። እኔም መናደዴን ትቼ ሦስት ነገሮችን ለማሳካት ወስኜ ተነሳሁ" ይላል ታዬ። እነዚህም አንድ ከመፃህፍት እንዲሁም በእውቀት እና በዕድሜ ከሚበልጡት መማር፤ ሁለት መፃህፍትን ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ መተርጎም እንዲሁም ሦስተኛው የማረሚያ ቤት ጓደኞቹን የኦሮምኛ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር ነበሩ።

በማረሚያ ቤት ቆይታው ወቅት 'ገላ ደሎታ' ወይም 'ስንቅ ለመጪው ትውልድ' በሚል ርዕስ ተረት እና ምሳሌ አዘል መፅሃፍ አዘጋጀ። "በማረሚያ ቤት ባሳለፍኩት ጊዜ ፀፀት የሚባል ነገር አይሰማኝም" ባይ ነው ታዬ።

ሰባት ዓመታት በማረሚያ ቤት ከቆየ በኋላ በ2008 ዓ.ም. ተፈታ። ከዛም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በበመለስ ከ16 ዓመታት በፊት ጀምሮት የነበረውን ትምህርት በስተመጨረሻም አጠናቀቀ። በዚህ ጊዜ ግን ለቤተሰቦቹም ሆነ ለወዳጅ ዘመዶቹ ስለ ምረቃው የተናገረው ነገር የለም። ይህን ያደረገበት ምክንያት ደግሞ ልክ እንዳለፈው ጊዜ የእሱን ደስታ ለማየት የጓጉ ቤተሰቦቹ ዳግም የሆነ ነገር ተፈጥሮ ሀዘን ውስት እንዳይወድቁ በማሰብ ነበር።

ህግ እና የተፈፃሚነቱ ነገር

ታዬ በአሁኑ ጊዜ በፍትህ ዙሪያ እየሰራ ሲሆን፤ "ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሩ ህጉ አይደለም። ተፈፃሚነቱ እንጂ" በማለት ይናገራል። ታዬ ሲያክል "ከእውነታው ይልቅ ገንዘብ በፍርድ ላይ የጎላ ሚና ይጫወታል።"

ታዬ አሁን ላይ በህግ ነክ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ፅሁፎችን እያዘጋጀ ይገኛልዷል። (መሃይምነት?) እና ግለሰባዊነት ደግሞ በጣም አተኩሮ የሚፅፍባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።