የኡጋንዳው ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ የድግሪ ውጤት ማጭበርበር ጉዳይ እያነጋገረ ነው

ዩጋንዳ

የፎቶው ባለመብት, Andrew Moore

ከአፍሪ ቀደምት የኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው የኡጋንዳው ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ 300 የሚሆኑ ተማሪዎቹ እንዴት ተደርጎ የድግሪ ውጤታቸው እንደተቀየረ በማጣራት ላይ ይገኛል።

እ.አ.አ. በ2015 ዓ.ም. ነበር ቁጥራቸው ወደ 300 የሚጠጋ የኡጋንዳው ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዲግሪ ትምህርት ውጤታቸው ላይ ጭማሪ ተደርጎ እንዲመረቁ የተደረገው።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ባርናባስ ናዋንግዌ እንደሚናገሩት የተማሪዎችን ውጤት የሚያስተዳድሩ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ከውጤት ማጭበርበሩ ጀርባ እጃቸው አለበት።

ምርመራውን እያጣደፈ የሚገኘው የካምፓላው ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎቹን ዋና (ኦሪጂናል) ድግሪ በቁጥጥር ሥር አውሏል። ዩኒቨርሲቲው ከ2011 ጀምሮ ያሉትን የተማሪዎቹን የድግሪ ውጤት እያንዳንዱ አስተማሪ ካስገባው የፈተና ውጤት ጋር በማነፃፀር ምርመራውን እያከናወነ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የእያንዳንዱ ተማሪ መዝገብ ተገላብጦ እንደሚመረመርም አክለዋል ምክትል ፕሬዚደንቱ።

የዩኒቨርሲቲው ማህደር ክፍል (ሬጅስትራር) ዋነኛ የምርመራው ትኩረት እንደሆነ ምክትል ፕሬዚደንቱ አሳውቀዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት 600 የሰብዓዊ እና ማሕበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች መመረቂያቸው ደርሶ ነገር ግን ውጤታቸው ለምረቃ የሚያበቃ አይደለም በሚል እንዳይመረቁ መደረጉ ይታወሳል።

የማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ በአህጉረ አፍሪቃ እጅግ ታዋቂ የሆነ የከፍተኛ ትምህርት መስጫ ተቋም ሲሆን ወደ አርባ ሺህ የሚጠጉ ከኡጋንዳ እና ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ተማሪዎች የሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ነው።

የታንዛንያውን የቀድሞ ፕሬዝደንት ጁሊየስ ኔሬሬን እና ታወቂውን የኬንያ ፀሃፊ ንጉጊ ዋ ቲዮንጎን የመሳሰሉ ሰዎችን ያፈራ ተቋም ነው የኡጋንዳው ማኬሬሬ ዩኒቭርሲቲ።

ፕሮፌሰር ናዋንግዌ ለቢቢሲ 'ፎከስ ኦን አፍሪካ' ሲናገሩ "የተፈጠረው የውጤት ማጭበርበር የዩኒቨርሲቲውን ስም ከሙጉዳቱ በፊት በቁጥጥር ሥር አውለን ምርመራችንን አጠናክረናል። ማንም ቢሆን በተጭበረበረ ውጤት ከእኛ ዩኒቨርሲቲ ድግሪ አግኝቶ ማምለጥ አይችልም" ብለዋል።

በማጭበርበር ወንጀሉ የተሳተፉ የተቋሙ ሰራተኞች በቁጥጥር ሥረ ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። እንዲህ ዓይነት ነገር ዳግም ፈፅሞ እንዳይታሰብ የሚያደርግ ቅጣት አጥፊዎቹ ላይ እንደሚያስተላልፉ ምክትል ፕሬዚደንቱ አሳውቀዋል።