የመጀመሪያውን ፊደል በ60 ዓመቷ መቁጠር የጀመረችው ኬንያዊቷ ፍሎረንስ

ፍሎረንስ

ዕድሜ ስድሳ ከረገጠ በኋላ ማንበብ መጀመር ምን ይመስላል? ይህን ሁሉ ዕድሜ ሳናነብ ከተጓዝን በኋላ ማንበብ መጀመርስ ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል?

ማንበብ በመቻላችን ምክንያት በየሰዓቱ ምን ያህል መረጃ እንደምናጋብስ ብናስበው ሊገርመን ይችላል። ጋዜጣ አንብበን በአከባቢያችን ብሎም በዓለም ዙሪያ ምን እየተከናወነ እንዳለ ማወቅ ስንችል፤ ቢሯችን ገብተን በበይነ-መረብ 'ኢ-ሜይል' የተደረገልንን መልዕክት ስናጣራም ሆነ በተንቀሳቃሽ ስልካችን የተላከልንን መልዕክት ስናነብ ብዙ መረጃዎችን እንቃርማለን። ስራችንን ያለ እነዚህ ነገሮች መከወን እጅጉን አዳጋች ሊሆንብን ይችላል። ነገር ግን ማንበብ ባንችል ብለን ብናስብስ?

ቼሶንጎች በተባለ የኬንያ ገጠራማ አካባቢ ነዋሪ የሆነችው ፍሎረንስ ቼፕቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊደል የቆጠረችው በ60 ዓመቷ ነው። የፍሎረንስ የልጅ ልጅ ከትምህርት ቤት መፅሓፍ ይዛ ስትመጣ ነበር ሴት አያቷ ፊደል ለመጀመሪያ ጊዜ የገለጠችው።

ቡክ ኤይድ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት ነበር የፍሎረንስ የልጅ ልጅ ለምትማርበት ትምህርት ቤት ቤተ-መፃሕፍት ከእንግሊዝ አታሚዎች ያመጣቸውን መፃሕፍት የለገሰው። ነገር ግን የአብዛኛዎቹ ልጆች ወላጆች እና አያቶች እራሳቸው ማንበብም ሆነ መፃፍ የሚችሉ ባለመሆናቸው አስተማሪዎቹ እነሱንም ለማስተማር ቆረጡ።

"ፊደል መቁጠር የጀመርኩት በ60 ዓመቴ ነው" የምትለው ፍሎረንስ ስትናገር "ማንበብ ከቻልኩ ወዲህ የሰለጠነውን ዓለም የተቀላቀልኩ ሆኖ ተሰማኝ" ትላለች። "ልጅ እያለሁ ቤተሰቦቼ እኔ እንድማር ብዙ አያግዙኝም ነበር። አግብቼ፣ ለነሱም ጥሎሽ አምጥቼ ከብቶችን እየጠበኩ እንድኖር ነበር ፍላጎታቸው። ቤተሰቦቼ ትምህርት የነበረው ጥቅም ብዙ አልገባቸውም ነበር" ስትል ታክላለች ፍሎረንስ።

ፍሎረንስ ፊርማ ማሳረፍም ሆነ ማንኛውንም ሕጋዊ ወረቀት አንብባ መረዳት አትችልም ነበር። ባለፈው ሕይወቷ ተጭበርብራም እንደሆን የምታውቀው ነገር የላትም።

አሁን ግን ፍሎረንስ ማንበብ ችላለች። ማንበብ መቻሏ የሰጣትን ጥቅምም ዘርዝራ አትጨርስም።

የታዘዘላት መድሓኒት ጥቅም እና የጎንዮሽ ጉዳት ከመረጃ መስጫ ወረቀቱ ላይ አንብባ በቀላሉ መረዳትም ትችላለች። ጋዜጣ አንብባ የውጭው ዓለም ላይ ምን እየተከናወነ እንዳለ እየተገነዘበችም ትገኛለች። ከሁሉም በላይ ግን ታሪክ አዘል መፃሕፍትን፤ ከቤተዘመድ የሚላክላትን ደብዳቤ እንዲሁም መፅሐፍ-ቅዱስን ማንበብ መቻሏ እጅግ ደስታ እንደሰጣት ትናገራለች።

"በተጨማሪም የዓለም ካርታን እያየሁ ሌሎቻ ሀገራት የት እንዳሉ ማወቅ መቻሌ ትልቅ ደስታ ይሰጠኛል" ባይ ነች። "ሌላው ደግሞ ግብርና ላይ የተፃፉ መፃሕፍትን በማንበቤ እንዴት እርሻየን መንከባከብ እንዳለብኝም አውቄያለሁ" በማለት ታክላለች ፍሎረንስ። የልጅ ልጇን የትምሀርት ቤት ውጤትም ማጣራት ችላለች ፍሎረንስ። ማንበብ ከሚችሉም ሆነ ከማይችሉ ሰዎች ጋር ስትሆን ድሮ የነበረባት ዝምታ ተሽሮ አሁን በልበ ሙሉነት መጫወት ጀምራለች።

"በማሕበረሰባችን ውስጥ ያሉ ጥሩ እና ጎጂ የሆኑ ህግጋት እና ባህሎች አሁን ተለይተው ተገልጠውልኛል" ትላለች ፍሎረንስ ስታስረዳ።

ፍሎረንስ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም ዕድሜያቸው የገፋ የማሕበረሰቡ አባላት የንባብ ትምህርቱን መውሰድ ጀምረዋል። በሰማንያዎቹ ዕድሜ መባቻ ላይ የሚገኙ አዛውንትም የትምህርቱ አካል ነበሩ። እርግጥ የአዛውንቱ ዓይን ደክሞ መፃፍ እና ማንበብ ቢያግዳቸውም ለወጡበት ማሕበረሰብ መልዕክት ለማስተላለፍ ሲሉ ወደ ትምህርት ቤት እንደሚመጡ ይናገራሉ።

ቡክ ኤይድ ከተባለው ድርጅት የመጣችው ኤማ ቴይለር የነፍሎረንስን ትምህርት ቤት ቤተ-መፃሕፍት ከጎበኘች በኋላ መፃህፍቱ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ጭምር እንዲያነቡ በመገፋፋታቸው እጅግ መደሰቷን ትገልፃለች።

"በኬንያ ገጠራማ ስፍራዎች ቤተ-መፃሕፍት ለታዳጊዎች ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያ እየሆኑ ነው። እዚህ ሲመጡ ከለላ እንዳገኙ ይሰማቸዋል። መፃሕፍትን እንደ ጓደኞቻቸው መቁጠር ጀምረዋል" በማለት ኤማ ታስረዳለች።