ሰሜን ኮሪያ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሁለተኛውን የባለስቲክ ሚሳኤል ወደ ጃፓን አስወነጨፈች

የሰሜን ኮሪያን ሚሳኤል ሙከራ ጃፓኖች በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሲከታተሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የመጀመሪያውን ሙከራ ካደረግች ጥቂት ሳምንታት የሆናት ሰሜን ኮሪያ ሁለተኛውን የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ወደ ጃፓን ውቅያኖስ አቅጣጫ አስወንጭፋለች።

የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ሀይል እንዳስታወቀው ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈችው የባለስቲክ ሚሳኤል 3700 ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ ሆካይዶ በተባለችው የጃፓን ደሴት አቅራቢያ አርፏል።

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤ ሀገራቸው የሰሜን ኮሪያን ትንኮሳ እና አደገኛ እንቅስቃሴ እንደማትታገስ አስታውቀዋል። አቤ በሰጡት መግለጫ "ሰሜን ኮሪያ መሰል ድርጊቷን የምትቀጥል ከሆነ የወደፊት ተስፋ የሚባል ነገር የላትም" ብለዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቴይለርሰንም እንዲሁ የሚሳኤል ሙከራውን ወቅሰው ሰሜን ኮሪያ በተባበሩት መንግስታት የተጣለባትን ማዕቀብ እየጣሰች ትገኛለች ብለዋል። በተጨማሪም ቴይለርሰን ለዚህ ተጠያቂው የሰሜን ኮሪያ አጋር የሆኑት ቻይና እና ሩስያ ናቸው በማለት ይወቅሳሉ። አክለውም "ቻይና ለሰሜን ኮሪያ ነዳጅ ትሸጣለች ሩስያ ደግሞ ሰሜን ኮሪያውያንን በጉልበት ሰራተኛነት እያሰራች ነው" ይላሉ። "ቻይና እና ሩስያ የራሳቸውን ቀጥተኛ እርምጃ በመውሰድ ለሰሜን ኮሪያ ምላሽ መስጠት አለባቸው" ብለዋል።

ሰሜን ኮሪያ ሙከራውን ባካሄደች በደቂቃዎች ልዩነት ደቡብ ኮሪያም ሁለት የባለስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ውቅያኖስ እንዳስወነጨፈች ዮንሃፕ የተሰኘው የደቡብ ኮሪያው ዜና ወኪል ዘግቧል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ደቡብ ኮሪያም በምላሹ የሚሳኤል ሙከራ አድርጋለች

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚደንት ጃየ-ኢን ከሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ጋር የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባ አድርገዋል። ፕሬዚደንቱ "የሰሜን ኮሪያ መሰል የሚሳኤል ሙከራዎች በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት ላይ ትልቅ አደጋ የሚጥሉ ናቸው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በሆካይዶ ደሴት ለሚኖሩ ጃፓናውያን በፅሁፍ መልዕክት ማስጠንቀቂያ ሲደርሳቸው፤ በአካባቢው የተሰቀሉ የማስጠንቀቂያ ደወሎችም ሚሳኤሉ በተተኮሰበት ጊዜ ጩኸታቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ታውቋል።

የአሁኑ ሙከራ ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ጊዜ ከሞከረችው የባለስቲክ ሚሳኤል ከፍተኛ አቅም ያለው እንደሆነም ተገምቷል። የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዎች ዋነኛ ትኩረት አሜሪካን መምታት የሚችል ረጅም ርቀት ተጓዥ ሚሳኤል መስራት እንደሆነ እየተዘገበ ይገኛል።