በሰሜን ጎንደር 4 ወረዳዎች በቅማንት አስተዳደር ስር ለመጠቃለል ወይንም በነበረው አስተዳደር ስር ለመቀጠል ሕዝበ ውሳኔ ተካሄደ

ድምጽ ሰጪዎች

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በ4 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ የ8 ቀበሌ ነዋሪዎች በትናንትናው ዕለት ከማለዳ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ሕዝበ ውሳኔ ሲያካሄዱ ውለዋል።

በሕዝበ ውሳኔው መሰረት የቀበሌዎቹ ኗሪዎች በቅማንት የራስ አስተዳደር ሥር ለመጠቃለል ወይንም እስካሁን በነበረው አስተዳደር ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ውሳኔ አስተላልፈዋል።

ከቅማንት ሕዝብ የማንነት እንዲሁም የራስ አስተዳደር ጥያቄ ጋር በተያያዘ በ2008 ዓ.ም በአካባቢው በተቀሰቀሱ ግጭቶች የፀጥታ አስከባሪ አካላትን ጨምሮ 95 ሰዎች መገደላቸውን መንግስታዊ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት ይገልጻል። ሪፖርቱ አክሎም የክልሉ የጸጥታ አስከባሪ አካላት "ከመጠን ያለፈ ኃይል" ተጠቅመዋል ሲል ወንጅሏል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከተነሱ ተመሳሳይ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች በተለየ የቅማንትን ሕዝብ ጥያቄ የአማራ ክልል መንግሥት ተመልክቶ በመጋቢት 2007 ባደረገው ጉባኤ ዕውቅና ሰጥቶታል።

የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች በደቡብ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የኮንሶና የቁጫ እንዲሁም የወልቃይት አካባቢ ኗሪዎች ማንሳታቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት የቅማንት ተወላጆች በብዛት ይኖሩባቸዋል የተባሉ በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ 42 ቀበሌዎች በቅማንት የራስ አስተዳደኣር እንዲካተቱ ሲደረግ የአማራና የቅማንት ተወላጆች ተቀላቅለው የሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ደግሞ በሕዝበ ውሳኔ ምርጫቸውን እንዲያሳውቁ ተወስኗል።

በቅማንት ሕዝበ ውሳኔ 25000 ያህል ኗሪዎች በ34 የምርጫ ጣብያዎች ላይ ድምፃቸውን ያሰማሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም በሕዝበ ውሳኔው ላይ ለመሳተፍ ካርድ የወሰዱት በ8 ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ21 000 በላይ ሰዎች መሆናቸውን የክልሉ የብዙሃን መገናኛ ድርጅት ገልጿል።

የምርጫ ጣብያዎቹም ቁጥር ቀድሞ ከታሰበው በአስር ያነሰ ነው።

ጭልጋ ወረዳ ነጋዴ ባህር ቀበሌ አካባቢ ሲዘዋወር የነበረ ጋዜጠኛ በአንዳንድ የምርጫ ጣብያዎች የሕዝበ ውሳኔ ሒደቱ ዘግይቶ ከመጀመሩ በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ችግር አለማየቱን ለቢቢሲ ገልጿል።

በአካባቢው ያነጋገራቸው አንድ አዛውንት ብዙዎቹ የአካባቢው ኗሪዎች እርስ በእርስ ተጋብተው ለረጅም ጊዜ መኖራቸውን ካስረዱት በኋላ የሕዝበ ውሳኔው መቃቃርን እንዳይፈጥር ስጋት የገባቸው መሆኑን እንደገለጹለትም ይናገራል።

ከመራጮች መካከል በዛ ያሉ ዕድሜያቸው ያልደረሰ የሚመስሉ ድምጽ ሰጪዎችን መመልከቱንና ዕድሜያቸውን ሲጠይቅ ሁሉም "አስራ ስምንት" ሲሉ እንደመለሱለት ጋዜጠኛው ጨምሮ አስረድቷል።

የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ተቆጥሮ ከዛሬ መስከረም 8 ማለዳ አንድ ሰዓት ጀምሮ በየምርጫ ጣብያው እንደሚለጠፍ ይጠበቃል።

ሂደቱን በበላይነት የሚቆጣጠረውና የሚያስፈፅመው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያሳየው የድምፁ ውጤት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መስከረም 15 ቀን ይላካል።