የፀረ ሙስና ዘመቻው አንድምታዎች

የግንባታ ሥራዎች

የፎቶው ባለመብት, CARL DE SOUZA

የምስሉ መግለጫ,

የግንባታ ሥራዎች ለሙስና ከተጋለጡ ዘርፎች መካከል ይጠቀሳሉ

በቢሊዮን ብር የሚቆጠር የህዝብ ሐብትን በማጉደል ወንጀል ተጠርጥረዋል የተባሉ 34 ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ደላሎች እና ነጋዴዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ፤ ከሙስና ጋር በተያያዘ የሚታሰሩ ባለስልጣናት እና የንግድ ሰዎች ጉዳይ ከባለፈው ዓመት መገባደጃ ጀምሮ ከዐብይ የመነጋገሪያ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ሆኖ አሁን ድረስ ዘልቋል።

ባለፈው ዓመት ማብቂያ ገደማ የተጀመረው የመንግሥት በሙስና የተጠረጠሩ ባለሥላጣናትና ነጋዴዎችን የመያዙ ዘመቻ አሁንም ያበቃ አይመስልም። በተለያዩ ጊዜያት ከመንግሥት ተቋማትና ከሌሎችም ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች እየተያዙ ከምርመራ ባሻገር ወደ ፍርድ ቤት እቀረቡ ነው።

ከነዚህም መካከል በከፍተኛ የመንግሥት የሥልጣን እርከን ላይ ከሚገኙ ሃላፊዎች መካከል የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ዓለማየሁ ጉጆ አንዱ ናቸው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ አለማየሁ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

አሁንም በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ከዚያም ለፍርድ የሚቀርቡ ተጠርጣሪዎች ቁጥር እየጨመረ የሄደ ሲሆን፤ መንግሥት ቃል ስገባ የቆየሁትን የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻ በከፍተኛ ደረጃ መጀመሬን የሚያሳይ ሰፊ ጥናት እና በቂ ዝግጅት አድርጌ የወሰድኩት እርምጃ ነው ይላል።

ከስልጣን ጋር በተያዘዘ የተሳሳተ አመለካከት መኖሩን የሚያምነው የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በወቅቱ ያወጣው መግለጫ፤ ተጠያቂነትን ለማስፈን ብሎም አጥፊዎቹን ከህግ ፊት ለማቅረብ በመስራት ላይ መሆኑን ይናገራል።

ይሁንና ተችዎች በፌደራል ፖሊስ ምርምራ ቢሮ እና በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ትብብር እየተወሰደ ነው በተባለው እርምጃ ላይ ያላቸውን ጥርጥሬ ይገልፃሉ። የዘመቻው ውጤታማነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ እንዳሉ ሁሉ፤ ገፊ ምክንያቱን ከአገሪቱ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር የሚያይዙት አልጠፉም።

የፎቶው ባለመብት, CARL DE SOUZA

የምስሉ መግለጫ,

ግንባታ

የሙስና ፈተና

ከሰባ በላይ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ኦዲት በማድረግ ልምድ ያካበቱት የሒሳብ አያያዝና የፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን መሃመድ በሥራ ላይ በቆዩባቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት ሙስና እየተንሰራፋ ሲሄድ አስተውያለሁ ይላሉ። ይህም አነስተኛ ጉቦን ጨምሮ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ድረስ ያለውን እንደሚያካትት ይናገራሉ።

በከፍተኛ ደረጃ ምዝበራ ከሚፈፀምባቸው ዘርፎች መካከልም የሥራ ውል አሰጣጥ እና አስተዳደር፣ የመሬት አስተዳደርና ግብር ይገኙበታል ብለዋል።

ዋነኛ ዓላማውን ሙስናን እና ተያያዥ ወንጀሎችን መታገል ያደረገው ዓለም አቀፉ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ በአዲስ አበባ የሚገነቡ ጥራታቸው የወረደ የመንገድ ሥራ ፕሮጄክቶችን ነቅሶ ዓይነተኛ የብልሹ አሰራር ማሳያዎች መሆናቸውን ያስረዳል። መንግሥት በዘመቻው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንን በር ማንኳኳቱንም "የሚያበረታታ" ነው ብሏል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የቤቶች ልማት አስተዳደር እንዲሁም የስኳር ኮርፖሬሽን ሌሎች በርከት ያሉ የሥራ ኃላፊዎቻችው ሞስነዋል ተብለው የታሰሩባቸው ናቸው። የተጠርጣሪ ባለሃብቶች ንብረቶች የታገዱ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ ክልሎችም በመቶዎች የሥራ ኃላፊዎች በጥርጣሬ እንዲታሰሩ ሆነዋል።

ጽህፈት ቤቱ ጨምሮም ኢትዮጵያ በሙስና እየተፈተነች ያለች አገር ለመሆኗ እ.ኤ.አ የ2016ቱን የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሕዝብ የሙስና እይታ መለኪያን በማስረጃነት ያቀርባል። በመለኪያው መሰረት ኢትዮጵያ ከ176 አገራት መካከል 108ኛ ደረጃን በመያዝ "በሙስና የተዘፈቁ" አገራት ተርታ ውስጥ ትገኛለች። በሙስና ንፅህና ከመቶ ነጥብ ማስመዝገብ የቻለችውም 34 ብቻ ነው። በመለኪያው መሰረት ያለፉት አስራ አምስት ዓመታት የአገሪቱ አማካይ ደረጃ 109ኛ አካባቢ ነው።

አብዱልመናን እንደሚሉት ለሙስና ከዕለት ወደ ዕለት መንሰራፋት አንደኛው ምክንያት መንግሥት በምጣኔ ሐብት ውስጥ በሰፊው እጁን ማስገባቱ ሲሆን የሕዝብን ሃብት የማስተዳደርና የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት እጅጉን ደካማ መሆናቸውም እንዲሁ ትልቅ ሚና አለው። "በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ውስጥ ያለው ተገቢ ያልሆነ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትም" ለሙስና መንገድ ጠራጊ ነው ይላሉ።

"ፉከራ ብቻ"

አዲስ አበባ ውስጥ በግል የንግድ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ብሩክ ዘላለም መንግስት ሙስናን የመቅረፍ ልባዊ ፍላጎት አለው ብሎ እንደማያምን ይገልፃል። "ሁሌም ችግራችን እንደሆነ ለይተነዋል ሲባል እንሰማለን፤ አንድ ሰሞን ሆይ ሆይ ይባልና ከዚያ ደግሞ ይረሳል" ይላል። ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ ሲጋጋል የነበረው ሙስናን የመመንጠር ዘመቻ ከአንድ ወር በኋላ መቀዛቀዙ ጉዳዩን "ፉከራ ብቻ" እንዳስመስለውም ይናገራል።

አብዱልመናን ሥር የሰደደውን የአገሪቱን የሙስና ችግር በዘመቻ መቅረፍ መቻሉ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ አትኩሮቱን ሙሰኞችን መመንጠርን ያደረገ የምርምራ ቡድን መቋቋሙን ባሳውቁበት ወቅት፤ መንግሥታቸው ሥልጣናቸውን ያላግባብ ለግል ጥቅም ባዋሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተው ነበር። በወቅቱም እንዲሁ ወደ 130 የሚጠጉ ግለሰቦች በሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸው ይታወሳል።

እነዚህ እርምጃዎች ከወትሮው በተለየ ውጫዊ ገፊ ምክንያቶች እንዳላቸው የሚከራከሩት አብዱልመናን፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ልዩ ልዩ ቦታዎች ተቀስቅሰው የነበሩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መንግሥት ላይ ጫና እንዳሳደሩ ያምናሉ።

ሙስና የስራ ፈጠራን፣ ታታሪነትን እና ሃቀኛ ፉክክርን በማቀጨጭ በአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ላይ ትልቅ አደጋ መደንቀር ይዟል የሚሉት ባለሞያው፤ ተቋማዊ ድክመት እና ፖለቲካዊ ወገንተኛነት መገለጫቸው የሆኑ ፍርድ ቤቶችን፣ የመንግሥትና የፓርቲ ወሰን መምታታትን በመፍጠር ፖለቲካውን ማወኩም እየተስተዋለ ነው ባይ ናቸው።