ከአንድ ወር በኋላ ለሚካሄደው የኬንያ ምርጫ ''የኮምፒዩተር ሲስተም ዝግጁ አይሆንም''

የናሳ ፓርቲ መሪዎች ምስል በፖስተር ላይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ራይላ ኦዲንጋ (በስተግራ) ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባሰሙት አቤቱታ የምርጫውን ውጤት ባሳለፍነው ውር ማሰረዛቸው ይታወሳል።

የኬንያን ድጋሚ ምርጫ የኮምፒዩተር ስርዓት የሚዘረጋው ድርጅት ጥቅምት 7 ለሚካሄደው ምርጫ የድምጽ መስጫው ስርዓት ዝግጁ ሊሆኑ እንደማይች አስታወቀ። ይህም ምርጫው በታቀደለት ጊዜ ሊካሄድ አይችልም የሚል ስጋትን ፍጥሯል።

ነሐሴ 2 ተካሂዶ በነበርውና ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ያሸነፉበትን ምርጫ የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምርጫው ''የተዛባ እና የተጓደለ'' ነው ሲል ውጤቱን መሰረዙ ይታወሳል።

የድምጽ መስጫ የኮምፒዩተር ስርዓቱን የሚዘረጋው ኦቲ-ሞርፎ የተባለው የፈረንሳይ ድርጅት ጥቅምት 7 ለሚካሄደው ምርጫ ውስብስብ የሆነውን የኮምፒዩተር ስርዓት እንደ አዲስ መዘርጋት ይኖርብኛል ብሏል።

ድርጅቱ እንደሚለው ከሆነ ''ይህ እጅግ ከባድ ስራን ይጠይቃል'' ስለዚህም ምርጫው በታቀደለት ጊዜ የድምጽ መስጫ ስርዓቱ ሊደርስ አይችልም ብሏል።

ኦቲ-ሞርፎ ለምርጫው የሚያሰፈልገው የኮምፒዩተር ስርዓት ሊዘገይ እንደሚችል ለኬንያ ምርጫ ኮሚሸን በጻፈው ድብዳቤ ላይ አሳውቋል። የምርጫ ኃላፊም ይህንኑ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን አባላት ካልተቀየሩ በምርጫው እንደማይሳተፉ አስጠንቅቀዋል።

የምርጫ ኮሚሽኑ የሁለቱን እጩዎችና ተወካዮቻቸውን ወደፊት በሚካሄደው ድጋሚ ምርጫ ላይ ስለተጋረጡ ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ ለመስከረም 10 ቀጠሮ ይዞዋል።