በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት ተጣርቶ ግልጽና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ አሜሪካ ጠየቀች

የአሜሪካ እምባሲ በኢትዮጵያ

የፎቶው ባለመብት, US Embassy

ዛሬ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያና ሶማሌ አዋሳኝ ድንበር አካባቢ በተለይም በሐረርጌ በተከሰተው ግጭት ''ተረብሸናል'' ብሏል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱን ግልጽ በሆነ አካሄድ እንዲያጣራና ተጠያቂዎቹን ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው እየተፈጠረ ስላለው ሁኔታ ''ግልጽ መረጃ የለም' ይላል የአሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲሹ መበረታታት ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡

ባለፈው አርብ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኦሮሚያንና የሶማሌ ክልሎች ሃላፊዎችን ማስጠንቀቃቸውንና አስፈላጊውን ማጣራት ተደርጎ ጥፍተኞቹን ለህግ እንደሚቀርቡ መግለጻቸው ይታወሳል።

''ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ የበለጸገችና ዴሞክራሲያዊት ሀገር መሆን የምትችለው፤ ግልጽና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይትና ግልጽ የመንግሥት አሰራር ሲኖራት፣ እንዲሁም የዴሞክራሲና የፍትህ ተቋማትን ማጠናከር ስትችል እንደሆነ እናምናለን፡፡ የሰሞኑ ሁነቶች በተጠቀሱት ዘርፎች ላይ ይበልጥ ፈጣንና ተጨባጭ ለውጥ አስፈላጊ እንደሆነ አመላካች ናቸው'' ይላል መግለጫው።