በዩጋንዳ ሕይወትን ከዜሮ የሚጀምሩት ስደተኞች

የደቡብ ሱዳን ስደተኞች
አጭር የምስል መግለጫ ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች መሬታቸውን ለመውሰድ ሰልፍ ላይ

ሶስት፣ አራት፣ አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት. . . ሰማያዊ ጃኬት ሰልፉን የሚመራው ሰው በእጁ ከያዘው መዝገብ ላይ ቁጥሮች ይቆጥራል። ጅምላ የሚሆኑ ሴቶች ኮረብታ የሚወጣውን ባለሰማያዊ ጃኬት ሰው ይከተሉታል። ሰውየው ኮረብታውን እንዳጋመሰ ቆመ።

ዞር ብሎ ሰልፉ መጀመሪያ ላይ የቆመችውን ሴት "ይህ ያንቺ ቦታ ነው" አላት። ሀምሳ ሜትር ያህል ከሴትየዋ ከራቀ በኋላ ድንበሯን አመላከታት።

የዩጋንዳ ስደተኞችን የመቀበል ፖሊሲ በተግባር ሲገለፅ ይህን ይመስላል። በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ መጠለያዎች ኡጋንዳ ከደቡብ ሱዳን ብቻ የሚመጡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን አስጠልላለች።

ስደተኞቹ የተሳጣቸው መሬት ላይ የሞቀ የስደት ኑሮ መምራት ጀምረዋል። አልፎም ከእርዳታ ድርጅቶች የተሰጣቸውን ዘር በመጠቀም በእርሻ ዘርፍም የተሰማሩ አሉ። አንዳንዶቹም ፍየል ማርባት ጀምረዋል።

ዩጋንዳ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብዛት ያለው ስደተኛ በመቀበል ቁጥር አንድ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች።

ከተለያየ የአለም ክፍል ሀገራቸውን ጥለው የሚመጡ ስደተኞችን እጆቿን ዘርግታ በመቀበል ዩጋንዳ ግንባር ቀደም ሆናለች። አዲስ ለሚመጡ ስደተኞችም በመስጠት አቀባበላቸውን አሳይተዋል ። ነገር ግን ዋናው ጥያቄ ከመመንጠርያ (ገጀራ) በቀር እጃቸው ላይ ምንም የሌላቸው ስደተኞች በምን ተአምር ይህንን መሬት ወደ ቤትነት ይቀይሩታል የሚለው ነው።

ለስደተኞቹ ቤት መስሪያ ከላስቲክ፣ ቋሚ እንጨቶች፣ ገመድ እና መመንጠሪያ የዘለለ ነገር አይሰጣቸውም። ምንም ነገር ከመስራታቸው በፊት መሬቱን በመመንጠሪያው ማስተካከል ግድ ይላቸዋል።

ጨቅላ በጀርባዋ ያዘለችው ደቡብ ሱዳናዊቷ ስደተኛ ጆሴፊን ፎኒ አይኗ ሩቅ የማየት ችግር ስላለበት አገሯ ቀዶ ጥገና አካሂዳለች። ጆሴፊን ለእርዳታው ብቁ ትሁን አትሁን ግልፅ አይደለም እንጂ አንዳንድ እርዳታ የሚያሻቸው ስደተኞችም ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። ለጊዘው ግን ዞር ዞር ብላ የተሰጣት መሬት ላይ ያለውን ሳር ከተመለከተች በኋላ "ለዛሬ እዚህ እንተኛለን" አለች።

በዩጋንዳም ሆነ በዓለም ትልቁ የስደተኞች መጠለያ በዩምቤ ግዛት የሚገኘው 'ቢዲ ቢዲ' መጠለያ በውስጡ 275 ሺህ ስደኞችን አቅፏል። የጆሴፊን መፃኢ ዕጣ ፈንታም ወደዚህ ግዙፍ የስደተኞች መጠለያ ነው።

ከተከፈተ ዓመት ያስቆጠረው ይህ ጣቢያ በጭቃ ቤቶች የተሞላ ነው። ስፍራው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከጥቅጥቅ ጫቃነት ወደ የጭቃ ቤቶች መናኸሪያ መለወጡ ብዙዎችን ያሰደመመ ነው።

ሌላኛዋ ስደተኛ ክርስቲን አይሻ ባሏን ትታ ወደ 'ቢዲ ቢዲ' ስደተኞች መጠለያ ከመጣች እነሆ ዓመት ደፈነች። በተሰጣት መሬት ላይ የጭቃ ቤት የሰራችው የማንንም እርዳታ ሳትፈልግ ነበር። የቤት ጣሪያዋን የተሻለ እንዲሆን ሜርሲ የተባለች ልዩ ፍላጎት የሚያሻት ታዳጊን በመንከባከብ ገቢ ታገኛለች። ከዛም በተጨማሪ የራሷን ስድስት ልጆችም ማሳደግም አለባት። ከክርስቲን ጋር አብራ ከደቡብ ሱዳን የተሰሰደችው ሮዝ አቡዋም እዚህ ስደተኞች ጣቢያ ብቻዋን ኑሮዋን ለመግፋት ተገዳለች። "ምርጫ የለኝም። ባለቤቴ ተገድሏል። እዚህ ብቻዬን ነኝ።" በማለት በሀዘኔታ ትናገራለች