ለዓለማችን የምግብ ደህንነት ስጋት የሆነው ተምች ወደ ኢትዮጵያ ዘልቋል

አርሚ ወርም Image copyright CABI

የኢትዮጵያ መንግስት እንዳስታወቀው ከ8.5 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ዜጎቹ የመጠጥ ውሃ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላይ ናቸው። በተለይ ደግሞ በደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው የዝናብ እጥረት በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችን የከፋ የምግብ እጥረት ላይ ጥሏቸዋል።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ፎል አርሚ ወርም የተሰኘ ተምች በስብል፤ በተለይ ደግሞ በበቆሎ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየባሰ መጥቷል። ተምቹ ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተከስቶ የሰብል ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደርሷል።

ፎል አርሚ ወርም?

ፎል አርሚ ወርም የተሰኘው ተምች እንደ አባጨጓሬ ያለ ነብሳት ሲሆን ወደ ቢራቢሮነት ከመቀየሩ በፊት በጣም ብዙ ምግብ የሚበላ ተመች ነው። ተምቹ ከዚህ በፊት 'አፍሪካን ኣርሚ ወርም' እየተባለ ከሚጠራው ሰበል በይ ነብሳት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን ከወደ አማሪካ አካባቢ የመጣ እንደሆነ ይታመናል።

ተምቹ በተለይ በቆሎ ላይ ከፍተኛ ውድመት የሚያደርስ ሲሆን ሌሎችም እንደ ጥጥ፣ ቦሎቄ፣ ድንች፣ እና የትምባሆ ሰብሎች ላይ ውድመት ያደርሳል። ይህ ተምች ወረራ በሚያደርስበት የሰብል ማሳ ላይ ቢያንስ ሶስት አራተኛው ስፍራ ላይ ጥፋት ያደርሳል።

ፎል አርሚ ወርም አዲስ ከመሆኑ የተነሳ መንግስታት፣ ማሕበረሰቡ እና አርሶ አደሮች እንዴት አድርገው መከላከል እንዳለባቸው መላ እስኪመቱ ደረስ ተምቹ ከፋ ያለ ጉዳት አድርሷል።

ተምቹ የአየር ሁኔታው ሞቃት እና እርጥብ በሚሆንበት ወቅት የሚራባ ሲሆን በበልግ እና መኸር ወቅት በበቆሎ ምርት ላይ ትልቅ ጉዳት ያደርሳል። እንደ ተባበሩት መንግስታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት ገለፃ ተምቹ ወደ አፍሪካ ዘልቆ የገባው በፈረንጆቹ 2016 ዓ.ም. ሲሆን በስምንት ሳምንታት ብቻ ደቡባዊ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ላቅ ያለ ጉዳት አድርሷል።

በዚህ መልክ አህጉሪቱን ያካለለው ተምቹ በወርሃ የካቲት ኢትዮጵያ ገብቷል።

"ተምቹ ከአባጨጓሬነት ዘመኑ ይልቅ ወደ ቢራቢሮነት ሲቀየር ሰብል ላይ ብዙ ጥፋት ያደርሳል። ለዚህም ነው በጣም ብዙ ቦታ በአጭር ጊዜ ማዳረስ የቻለው" በማለት ማብራርያ የሚሰጡት የዘርፉ ባለሙያ ፕሮፌሰር ኬን ዊልሰን ናቸው።

ፎል አርሚ ወርም በኢትዮጵያ

ተምቹ አሁን ላይ ከ20 በላይ የአፍሪካ ሀገራትን ያደረሰ ሲሆን ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ የመጀመሪያዋ ተጠቂ ሀገር ናት። በኢትዮጵያም ተምቹ በጋምቤላ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች በመስፋፋት ጉዳት ካደረሰ በኋላ ወደ አፋር፣ አማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እየተዛመተ ነው። ነገር ግን እስካሁን ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ በእግጠኝነት መናገር አልተቻለም። ቢሆንም ግን ለተከሰተው የምግብ እጥረት የራሱን አስተዋፅኦ እንዳበረከተ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

ፎል አርሚ ወርምን በፀረ-ተባይ ኬሚካል ማስወገድ ቢቻልም ነገር ግን ተምቹ በአንዳንድ ቦታዎች ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን መላመድ መጀመሩን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ተመራማሪዎች ተምቹን የሚያጠፋ ቫይረስ ለመስራት ከመሞከር ጀምሮ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ሩጫ ላይ ናቸው።

በቀጣይ. . .

የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት እንደሚያስጠነቅቀው ተምቹ በአፍሪካ ተጨማሪ ሀገራትን ከማዳራሱም በላይ ወደ አውሮፓ እና እስያም ሊያመራ ይችላል።

የሳይንስ ተቋማትም ፎል አርሚ ወርም የተሰኘው ተምች ለዓለማችን የምግብ ደህንነት ስጋት የሆነ ሲሉ ፈርጀውታል።