በኢትዮጵያ የተፈናቃዮች ቁጥር ማሻቀብ የደቀነው ፈተና

ከምሥራቅ ሐረርጌ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች
አጭር የምስል መግለጫ ከምሥራቅ ሐረርጌ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ

በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሱትን ግጭቶች ተከትሎ ከሚኖሩበት ቀዬ የተፈናቀሉ ከ50 ሺህ በላይ መሆናቸው ባለፈው ሳምንት ተዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እንደሚሉት ደግሞ በ2009 የበጀት ዓመት ከአምስት የግጭት ዞኖች የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር ከ416 ሺህ በላይ ነው።

ቢቢሲ ያነጋገረው በሶማሌ ክልል ቦምባስ ከተማ በሰው ቤት ተቀጥሮ ይሰራ የነበረው ደንሳ ለአንድ ዓመት ከሰባት ወር ያህል የኖረበትን ስፍራ ጥሎ የሄደው ያለንብረት ባዶ እጁን መሆኑን ይናገራል።

ለጥቂት ቀናት በሐረር ስቴዲየም ከቆየ በኋላ የተፈናቃዮቹ ቁጥር መብዛት በሃረማያ ከተማ በሰው ቤት ውስጥ እንዲጠለል እንዳስገደደው ያስረዳል።

ደንሳ ቀጣይ ጉዞው ወደ ትውልድ ቀዬው ምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ቢሆንም ምን እንደሚገጥመውም ሆነ ሕይወቱ ከዚህ ወዲያ ምን ዓይነት መልክ እንደሚኖረው አያውቅም።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ግጭቶች ተግ ማለታቸው ቢሰማም በተቃራኒው የሚወጡ ዘገባዎች ግጭቶች እየተከሰቱ እንደሆነ እያመለከቱ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደንሳን ለመሳሰሉ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለግ ሌላ የራስ ምታት ነው።

የተለያዩ ወገኖች ተፈናቃዮችን የማቋቋምን ተግባር ለማገዝ በማሰብ ገንዘብና ቁሳቁሶችን በማዋጣት በመረባረብ ላይ ይገኛሉ።

በግጭትና በድርቅ ተፈናቅለው ለተረጅነት የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ያለመሆን፤ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ከሳዑዲ አረቢያ ከስደት እየተመለሱ መሆኑ አገሪቱ እየተጋፈጠች ያለችውን ሸክም አመላካች ነው።

የድርቅ ተረጅዎች ቁጥር ጨምሯል

ለሶስተኛ ተከታታይ ዓመት ያጋጠመው የዝናብ እጥረት 8.5 ሚሊዮን ሰዎችን ለአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ጠባቂነት እንዳጋለጠ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

ባለፈው ጥር የተረጅዎቹ ቁጥር 5.6 ሚሊዮን እንደነበር ይታወሳል።

በዚህም ከየትኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች በባሰ የተጠቃው የሶማሌ ክልል ሲሆን፤ በክልሉ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለከፋ የምግብ እጥረት እንደተዳረጉ የደብልዩ ኤፍ ፒ ሪፖርት ያሳያል።

ከባለፈው አመት ጀምሮ በክልሉ የሚገኙ አርብቶ አደሮች ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸው የሆኑ ከብቶችን እንዳጡ ይዘገባል። ከዚህ በተጨማሪም እንደ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ያሉ በሽታዎች መከሰታቸው ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።

ለሁኔታው አሳሳቢነት አጽንዖት ለመስጠት በወርሃ ነሐሴ መገባደጃ ሶስት የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ አካባቢው ተጉዘው ነበር ።

የዓለም ምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) የበላይ የሆኑት ጆዜ ግራዚያኖ ዳ ሲልቫ፤ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም (ደብልዩ ኤፍ ፒ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴቪድ ቢስሊ እና ከዓለም አቀፉ የእርሻ ልማት ፈንድ ፕሬዚዳንት ጊልበርት ሁንግቦ በአራት ቀናት የኢትዮጵያ ቆይታቸው ወደ ሶማሌ ክልል በማቅናት በድርቁ የተጠቁ አርብቶ አደሮችን አናግረዋል።

ሶስቱ ባለስልጣናት ከአየር ንብረት መዛባት ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ድርቅን ለመቋቋም በሚያስችሉ ዘላቂ የመፍትሄ ተግባራት ላይ ብዙ መሰራት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

"ድርቅ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍን የሚጠይቅ [አደጋ] መሆን የለበትም" ሲሉ በወቅቱ ሁንግቦ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ትብብር ጽህፈት ቤት ሪፖርት እንደሚያሳየው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ከተባሉ የድርቅ ተጠቂዎች በተጨማሪ እስከ ያዝነው የፈረንጆች ዓመት መገባደጃ ድረስ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ በሴፍቲ ኔት የታቀፉ ተጠቃሚዎች ያልተቋረጠ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።

ዘንድሮ ኢትዮጵያ እነዚህን ተረጅዎቿን ለመመገብ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ እገዛ እንደሚያስፈልጋት የተገለፀ ሲሆን የሰብዐዊ እርዳታ ትብብር ጽህፈት ቤቱ እንደሚለው ከዚህ በኋላ ላሉት አራት ወራት 418 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።

የተረጅዎች ቁጥር አስደንጋጭ ወደ ሆነ ደረጃ ማደጉም አሳሳቢ እየሆነ ነው።

አጭር የምስል መግለጫ ተፈናቃዮች ያረፉባቸው ድንኳኖች

ግጭቶች የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ቁጥር ይጨምራሉ

ከሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰነው የኦሮሚያ ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከሚንቀሳቀስ አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው በዞኑ ከ116 ሺህ በላይ ሰዎች በድንበር ግጭት ምክንያት ተፈናቅለዋል።

ግጭቶቹ ለ66 የጤና እና ለ41 የትምህርት ተቋማት ሥራ መቋረጥ ምክንያት እንደሆኑም መረጃው ያሳያል።

መቀመጫውን በጄኔቫ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መቆጣጠሪያ ማዕከል (አይዲኤምሲ) እንደሚለው እ.ኤ.አ 2017 የመጀመሪያ አጋማሽ በኢትዮጵያ 213 ሺህ አዳዲስ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሉ።

ይህም ከግጭት ጋር በተያያዘ ከሚኖሩበት ወይንም ከሚሰሩበት ቀዬ የለቀቁ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ቁጥር ከ588 ሺህ በላይ ያደርሰዋል።

በተለይም በ2007 ዓ.ም እና በ2008 ዓ.ም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተነሱት ተቃውሞችና ግጭቶች ለተፈናቃዮች ቁጥር መጨመር ምክንያት ሳይሆኑ እንዳልቀረ ይቆጠራል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የወርሃ ሐምሌ ሪፖርት እንደሚያስረዳው ድርጅቱ በ544 የተፈናቃዮች ጣቢያዎች ውስጥ ባደረገው ቅኝት ከ1 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሲኖሩ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በሶማሌ ክልል ይገኛሉ።

ድርቅና ግጭት ከቀዬ ለመፈናቀል ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ይላል ሪፖርቱ።

ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ በተለይም ከደቡብ ሱዳን፣ ከኤርትራና ከሶማሊያ ለተፈናቀሉ 800 ሺህ ገደማ ስደተኞች መጠለያ ሰጥታለች።

በሌላ በኩል የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ሰነድ አልባ የሆኑ የሌላ አገር ዜጎች አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ ያስተላለፈውን መመሪያ ተክትሎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዕጣ ሲያነጋግር ቆይቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ከባለፀጋዋ ሳዑዲ ለማስወጣትና ወደ አገራቸው ከተመለሱም በኋላ በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት እያደረገ እንደሆነ ይገልፃል።

እስካሁንም 70 ሺህ ያህል ዜጎች መመለሳቸው ተዘግቧል።

በቅርቡ ሳዑዲ ለሰነድ አልባ ሰራተኞች የሰጠችውን አገሪቱን ለቆ የመውጫ የምህረት ጊዜ ለሶስተኛ ጊዜ ማራዘሟን ተከትሎ ተጨማሪ ሰዎች የሚመለሱ ከሆነ፤ እነርሱን የማቋቋሙ ኃላፊነት በአገሪቷ ጫንቃ ላይ የሚደረብ ሌላ ፈተና ይሆናል።