የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተራዘመ

የኬንያ ምርጫ ተቀናቃኞች Image copyright AFP/Getty Images

የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ለጥቅምት 07/2010 ዓ.ም ሊያካሂድ አቅዶት የነበረውን የድጋሚ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በዘጠኝ ቀናት አራዘመ።

ቦርዱ ባወጣው መግለጫ የድጋሚ ምርጫው ጥቅምት አስራ ስድስት እንዲካሄድ ወስኗል።

የኬንያ ምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ዋፉላ ቼቡካቲ እንዳሉት የምርጫውን ዕለት መለወጥ ያስፈለገው የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ታአማኒ ምርጫ እንዲካሄድ የሰጠውን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ኮሚሽኑ ሙሉ ዝግጅት እንዲያደርግ ለማስቻል ነው ብለዋል።

የሃገሪቱ መሪ ኡሁሩ ኬንያታ ግን ድጋሚ የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቀድሞ በተያዘለት ዕለት መካሄድ አለበት ብለዋል።

ኬንያታ ጨምረው ፍርድ ቤቱ በቀዳሚው ምርጫ ወቅት የነበሩትን የምርጫ ሰነዶች በአግባቡ ሳይመረመር ውሳኔ ላይ ደርሷል በማለት ወቀሳያቀረቡ ሲሆን፤ ይህም ሀገሪቱን የፍትህ ሥርዓት ወደ ቀውስ ውስጥ ሊከት ይችላል ብለዋል።

የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን የድጋሚ ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን ሊያራዝም የቻለው፤ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን የሚያቀርበው የፈረንሳይ ተቋም ቀድሞ በተያዘው ቀን አስፈላጊውን አቅርቦት ማድረስ እንደማይችል ካሳወቀ በኋላ ነው።