አሜሪካ አወዛጋቢ የሆነውን የጉዞ ዕገዳ በሰሜን ኮሪያ፣ በቬንዝዌላና በቻድ ዜጎች ላይ ጥላለች

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ዋይት ሃውስ እንዳሳወቀው ይህ የጉዞ ዕገዳ የመጣው የተለያዩ የውጭ መንግሥታት የሰጡት መረጃ ከታየ በኋላ ነው። ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንታዊዉን አዋጅ ያወጡት እሁድ ረፋዱ ላይ ነው። "ዋነኛ ቀዳሚ ሥራዬ የአሜሪካንን ደህንነት ማስጠበቅ ነው። ስለእኛ ደኅንነት አፋችንን ሞልተን የማንናገርላቸውን ሰዎች አገራችን ውስጥ አናስገባም። " በማለት ትራምፕ ተናግረዋል።

ቬንዙዌላን በተመለከተ ክልከላው ለሁሉም ዜጎች ሳይሆን ለመንግሥት ባለስልጣናትና ለቤተሰቦቻቸው ነው። እነዚህ ሦስት ሃገራት ቀድሞ ክልከላ የተደረገባቸውን እንደነ ኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመንና ሶማሊያን ተቀላቅለዋል። ነገር ግን ይህ አዲስ አዋጅ ሱዳን ላይ ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ አንስቷል። የመጀመሪያው የትራምፕ የጉዞ ዕገዳ ስድስት በአብዛኛው ሙስሊም የሚኖርባቸው አገሮች ላይ በማተኮሩ አወዛጋቢ የነበረ ሲሆን፤ ሙስሊሞችን የማገድ ዘመቻ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እንደነበር የሚታወስ ነው።

የመጀመሪያው የጉዞ ዕገዳ ከፍተኛ ተቃውሞ ከማስነሳቱም በተጨማሪ ጉዳዩ ህጋዊ መፍትሄም እንዲሰጠው ጥያቄ ተነስቶበታል። የአሜሪካውም ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐምሌ ወር ላይ በከፊል ያፀደቀው ሲሆን አጠቃላይ ውሳኔውም በጥቅምት ወር ላይ ይታወቃል። የአሜሪካ የሲቪል መብቶች ማህበር አዳዲሶቹ አገራት መጨመራቸው ምንም እንደማይቀይር አሳውቋል። "አሁን የተጨመሩት አገራት የአሜሪካ አስተዳደር ዋነኛ አላማው የሆነውን የሙስሊም አገራት ማዕቀብን አይቀይረውም።" በማለትም ተናግረዋል።

አዲሱ የፕሬዚዳንቱ አዋጅ ቁልፍ የሚባሉ ጉዳዮችን የሚቀይር ቢሆንም የተደቀነበትን ህጋዊ ፈተና እንዴት እንደሚያልፈው ግን ግልፅ አይደለም።

የሰሜን ኮሪያና የቬንዙዌላ በዝርዝሩ ውስጥ መካተት ሁለም ዕገዳ የተጣለባቸውን አገራት ሙስሊም አይደሉም የሚለውን ያሳያል። አዲሶቹን አገራት ላይ ማዕቀብ ለመጣል መስፈርቶቹ አገራት ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ትብብር በመመልከትና ጥልቅ ምርመራ በማድረግ ሲሆን፤ እገዳውም እያንዳንዱን አገር ነጥሎ በማየት ነው።

1.ሰሜን ኮሪያን በተመለከተ ዋይት ሀውስ እንዳሳወቀው ሃገሪቷ ከአሜሪካ መንግስት ጋር በምንም መንገድ መተባበርን ባለማሳየቷና መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች ልታሟላ ባለመቻሏ ሁሉም ዜጎቿ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እገዳ ተደርጎባቸዋል።

2.አሜሪካ በምታደርገው ሽብርተኝነትን መዋጋት ዘመቻ ምንም እንኳን ቻድ አጋር ብትሆንም ሽብርተኝነትንና ሌሎች መረጃዎችን በተመለከተ አሜሪካ በምትፈልገው መንገድ ባለመስጠቷ የንግድና የቱሪስት ቪዛ ለሁሉም ዜጎቿ ተከልክላለች።

3.በቅርቡ ከአሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የተጣለባት ቬንዙዌላ ዜጎቿ ለደህንነት ስጋት መሆን አለመሆናቸውን መረጃ ባለመስጠት፤ እንዲሁም ከአሜሪካ ተባረው የሚመለሱ ዜጎቿን በፈቃደኝነት ባለመቀበል የተወሰኑ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ላይ ማዕቀቡ ተጥሏል።

የትራምፕ አዋጅን የያዘውን ሰነድ የጠቀሰው ዋይት ሀውስ እንደሚለው ምንም እንኳን ኢራቅ መስፈርቶቹን ባታሟላም አይ ኤስን ለመዋጋት ከአሜሪካ ጋር ባላት የጠበቀ ግንኙነት ይህ ገደብ አልተጣለባትም። ይህ ክልከላ ከሶስት ሳምንታት በኋላ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ህጋዊ ቪዛ ላላቸው ክልከላው ተግባራዊ አይሆንም።