የአለም ሙቀት መጨመር የቡና ጣዕምን ያበላሽ ይሆን?

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የቡና ለቀማ በኢንዶኔዥያ

ዓለም ላይ እየተከሰተ ያለው የሙቀት መጨመር ምቹ የሆኑትን የቡና እርሻዎችን መጠን ሊያሳንስ እንደሚችልና በዚህም ቡና ጠጪዎች ጣዕሙ ጥሩ ያልሆነና ዋጋው የናረ ቡና ሊጠጡ እንደሚችሉ ለንደን ከሚገኘው ኪው ጋርደንስ ተመራማሪዎች የተገኘ መረጃ ያሳያል።

የቡና መገኛና ከፍተኛ ጥራት ያለውን አረቢካ ተብሎ የሚታወቀውን ቡና አምራታ ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ፤ በሚቀጥለው ክፍለ-ዘመን ቡናዋ ከፍተኛ አደጋ ሊገጥመው እንደሚችል በቅርቡ የታተመው የኔቸር ፕላንትስ ዘገባ ያሳያል። ዘገባው ጨምሮ እንደሚያስረዳውም ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ነው። "በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገራት ጥንቃቄ ካላደረግን የሚኖረው የቡና ክምችት ከማነሱ በተጨማሪ ጣዕሙ ጥሩ ያልሆነና ዋጋው የማይቀመስ ይሆናል። " በማለት ለቢቢሲ የተናገረው በኪው ጋርደንስ የቡና ተመራማሪ የሆነው ዶክተር አሮን ዴቪስ ነው። በወቅቱ የሚኖረው ከፍተኛ የቡና ፍጆታም በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የሚኖረውን ምርት ባዶ ሊያስቀረው እንደሚችል ከዓለም አቀፍ የቡና ድርጅት የወጡ ቁጥሮች ያሳያሉ።

እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ምርት በተመዘገበባቸው ወቅት ያለው የቡና ክምችት የቡና እጥረት እንዳይገጥም እንዲሁም ዋጋውም እንዳይንር አድርጎታል። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ላኪዎች ካለቸው ክምችት ለመላክ በመገደዳቸው ያለው የቡና መጠን ክምችት እንዲቀንስ እንዳደረገ ከዓለም አቀፍ የቡና ድርጅት የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ደግሞ የቡና ዋጋን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያንረው እየተነገረ ሲሆን በተለይም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የቡና አይነቶች ዋጋ የማይቀመስ ይሆናል።

አጭር የምስል መግለጫ ኢትዮጵያዊቷ ቡና ስትለቅም

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ

አሁን ባለው የ4 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት መናር በክፍለ-ዘመኑ መጨረሻ ላይ ቡና የሚመረትባቸውን የኢትዮጵያ ክፍሎችን በ60 በመቶ እንደሚቀንሰው ኪው ጋርደንስና ኢትዮጵያውያን የተጣመሩበት ጥናት ይተነብያል። ነገር ግን አሁን አለም እየሄደችበት ባለው የአየር ለውጥ ሁኔታ ውስጥ ሲፈተሽ ቡና የሚመረትባቸውን የኢትዮጵያ ክፍሎች በ55 በመቶ እንደሚቀንሱ የኪው ጥናት ያስረዳል።

"እንደተለመደው ቡናን ማምረት እንዲሁም መሸጥ ለመጪው የኢትዮጵያ የቡና ኢኮኖሚ አደገኛ የሆነ አካሄድ ነው። " በማለት ሌላኛው የኪው ጥናት ፀሀፊ ጀስቲን ሞአት ይናገራል።

የኪው ተመራማሪዎች ችግሮቹን መጥቀስ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄ ከተደረገበት መፍትሄ ማምጣት እንደሚቻል በአፅንኦት ይናገራሉ። እንደ መፍትሄም ከሚያቀርቧቸውም መካከል ቡና የሚያበቅሉ አካባቢዎችን በመቀየር ጠንከር፤ ያለ የደን ጥበቃና ተከላ ለኢትዮጵያ ቡና ምርት ዘላቂ የሆነ ዕድገትን ሊያመጣ እንደሚችል ይናገራሉ። "አንዳንዶቹን አሉታዊ ችግሮች መቅረፍና ያሉትን የቡና አብቃይ አካባቢዎችን ከአራት እጥፍ በላይ ማሳደግ ያለውን ከመጠበቅ ጋር ሲወዳደር የተሻለ ነው። " በማለት ዶክተር ዴቪስ ይናገራል።

ቡና 15 ሚሊዮን ለሆኑ ኢትዮጵያውያን የመተዳደሪያ ምንጭ ሲሆን ይሄም 16 በመቶ የሚሆነውን የህዝብ ብዛት ይሸፍናል። በምሥራቁ ክፍል የሚኖሩ በግብርና የሚተዳደሩ ኢትዮጵያውያን ካለው የሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ ትግል ላይ የነበሩ ሲሆን ምርት በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰበት እንዲሁም ረዘም ላለ ወቅት አካባቢያቸው በድርቅ ተመታበት ነው።

ባለፉት አስር ዓመታት በግብርና የሚተዳደረው ጀማል ቃሲም የቡና ምርቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እንደተመለከተ ይናገራል። "በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ብዙ ፍሬ ቢያፈሩም፤ በአሁኑ ወቅት ግን መሬቱ ደርቋል እንዲሁም መክኗል።" በማለት ጀማል ይናገራል።

ቴክኖሎጂ የቡናን መፃኢ ዕድል ይታደግ ይሆን?

ቴክኖሎጂ የቡናን የወደፊት ደህንነት ከመታደግ አንፃር ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል። ከሦስት ዓመታት በፊት የአረቢካ ቡና የዘረመል አወቃቀሩ ለህዝብ የተገለፀ ሲሆን፤ ለሞቃት አካባቢዎችም የሚሆኑ ሰብሎችንም ለመምረጥ አስችሏል። የዓለም የቡና የምርምር ተቋም ሰብሎችን የማራባት እቅድ የያዘ ሲሆን አረቢካ ቡናንም እንደገና ለመፍጠር እየተሞከረ ነው። ይሄም የተሻለ ዝርያን፣ የተለያዩ የቡና አይነቶችን ለማግኘት እንዲሁም የአየር ፀባይን ለውጥን መቋቋም እንዲችሉ የሚያደርጋቸው ነው። ይህ የማራባት እቅድ በአንድ ምሽት የሚሆን አይደለም ምናልባትም እውን የሚሆነው የቡና ወዳጆች የዋጋ መናርንና የጥራት ማሽቆልቆል በሚያጋጥማቸው ወቅት ይሆናል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ