ኡበር የተሰኘው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ በለንደን የሥራ ፈቃድ መከልከሉን ተከትሎ ሹፌሮች ዕጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

ኡበር Image copyright Reuters

ኡበር የተሰኘው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ በለንደን ከተማ የሥራ ፈቃድ መከልከሉን ተከትሎ በሺዎች ሚቆጠሩ ሹፌሮች ዕጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

አሜሪካዊው ኩባንያ 'ኡበር' በመላው ዓለም በሚገኙ በ633 ከተሞች የትራንስፖረት አገልግሎትን ይሰጣል። ተጠቃሚዎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ በሚጭኑት መተግበሪያ አማካኝነት በአቅራቢያቸው የሚገኘውን ታክሲ በመጥራት ወደ መዳረሻቸውን መሄድ ይችላሉ። የክፍያው መጠን የሚሰላው የትራፊክ እንቅስቃሴን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተጓዙበትን የርቀት መጠንና ጉዞው የወሰደውን ጊዜ በማመዛዘን ነው።

አሽከርካሪዎች የራሳቸውን መኪና ተጠቅመው አገልግሎት በሚሰጡበት በዚህ ኩባንያ ውስጥ በለንደን ብቻ 40ሺ የሚሆኑ ሹፌሮች እየሰሩ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ይገኙበታል።

ኤርትራዊው ሰሚር አማን ከ3 ዓመት በላይ የኡበር ሹፌር በመሆን እየሰራኝ ይገኛል። ሰሚር እንደሚለው ኡበር በማንኛውም ስዓት የሚሰራው ሥራ ስለሆነ ለሱ ሁነኛ ምርጫ ነው።

የለንደንን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚቆጣጠረው ትራንስፖርት ፎር ለንደን የኡበርን የሥራ ፈቃድ አለማደሱን ዓርብ ዕለት ይፋ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ሰሚርን የመሳሰሉ በርካታ ሹፌሮች እጣፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

እንደ ትራንስፖርት ፎር ለንደን ከሆነ ኡበር አስፈላጊውን መመዘኛ ባለሟሟላቱ ነው ፈቃዱን የተከለከለው።

ከህዝብ ከደህንነትና ከጸጥታ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ውሳኔውን ማሳተላለፉንም አስታውቋል። ኡበር የአሽከርካሪዎችን የኋላ ማንነት የሚያጠናበትና በተደጋጋሚ የወንጀል ሥራ ውስጥ የሚገቡትን የሚያሳወቅበት ሂደት አንዱ ስጋት ሆኗል።

ኡበር በለንደን ያለው የስራ ፈቃድ መስከረም 30 ይጠናቀቃል።

ውሳኔው ላይ ያለውን ይግባኝ በ21 ቀናት ውስት ማስገባት የሚችል ሲሆን በዚህ ወቅትም በስራ ላይ መቆየት ይችላል።

በለንደን የኡበር ሥራ አስኪያጅ ቶም ኤለቪጅ "እኛን ከለንደን ከተማዎች ላይ በማራቅ ትራንስፖርት ፎር ለንደን እና ከንቲባው የተጠቃሚዎችን አማራጭ ማሳነስ ለሚፈልጉ ጥቂቶች መሸነፋቸውን አሳዩ" ብለዋል።

"ውሳኔው ከጸና ከ40 ሺ ሹፌሮች በላይ ከስራ ውጭ የሚሆኑ ሲሆን የለንደን ነዋሪዎችም ከምቹና በቀላሉ ከሚገኝ የትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ሊቆራረጡ ነው።" ያሉት ቶም ኤለቪጅ "በሚሊዮን በሚቆጠሩ ደንበኞቻችንን ተመራጭ የሆነውን እና የአሽከርካሪዎችን ህይወት ለመታደግ ውሳኔውን በመቃወም ፍርድ ቤት እንሄዳለን።" ስሉ ጨምረው ተናግረዋል።