ሰሜን ኮሪያ አሜሪካንን ጦርነት በማወጅ እየወነጀለች ነው

በሁለቱ አገራት ጦርነት ምን ይመስል ይሆን?
አጭር የምስል መግለጫ በሁለቱ አገራት ጦርነት ምን ይመስል ይሆን?

የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪ ዮንግ ሆ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገራቸው ላይ ጦርነት አውጃለች በማለት እየከሰሱ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ፒዮንግ ያንግ የአሜሪካን ቦምብ ጦር አውሮፕላኖችን የመምታት መብት እንዳላትም ጨምረው ተናግረዋል።

ዮንግ የጦር አውሮፕላኖቹ የሰሜን ኮሪያ ክልል ውስጥ መገኘት አይጠበቅባቸውም ብለዋል። ለዚህ ንግግር ዋይት ሀውስ የሰጠው ምላሽ "አስቂኝ" የሚል ነው። ፔንታጎንም ቀጠል በማድረግ ፒዮንግ ያንግ ጠብ አጫሪነቱን ማቆም አለባት በማለት አስጠንቅቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ይህ "ጠብ አጫሪ ንግግር" ጦርነትን ሊጋብዝ ወደሚችል አለመግባባጠት ይቀየራል ብለዋል። የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሱን ያቀረቡት ትራምፕ 'የሰሜን ኮሪያ አመራር በዚህ ጉራው ከቀጠለ ለረጅም ጊዜ እንደማይቆዩ' በትዊተር ገፃቸው ላይ ካሰፈሩ በኋላ ነው።

"ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስታወስ ያለበት መጀመሪያ አሜሪካ ናት በአገራችን ላይ ጦርነት ያወጀችው።" በማለት ሪ ዮንግ ሆ የተናገሩት ኒውዮርክ ውስጥ በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፈው ሲወጡ ከሪፖርተሮች ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው።

"ከአሜሪካ እየተቃጣብን ላለው ሥጋት የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን። ይሄም ማለት የአሜሪካ ቦምብ ጣይ የጦር አውሮፕላኖችን በአየር ቀጠናዎቻችን ላይ ባይሆኑም የማጥቃት መብት አለን" በማለትም ጨምረው ተናግረዋል።

የትራምፕ የትዊተር ፅሁፍ የመጣው ሪ ዮንግ በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትን አስመልክቶ "አእምሮው የቀወሰ፣ በስልጣን የሰከረ፣ ራስን በማጥፋት ዘመቻ ላይ ያለ" በሚል ኃይለቃል የተሞላበት ንግግር ከሰጡ በኋላ ነው።

የፔንታገን ቃልአቀባይ ኮሎኔል ሮበርት በበኩላቸው "ሰሜን ኮሪያ ይህ ጠብ አጫሪነት ፀባይ ካላቆመች ፕሬዝዳንታችን ሰሜን ኮሪያን አስመልክቶ ምን አይነት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የተሻለ አማራጭ እንሰጣለን።" በማለት ተናግረዋል።