ቀጣዩ ኢትዮጵያዊ የማራቶን ባለተስፋ ጉዬ አዶላ ማነው?

ጉዬ አዶላ በበርሊን ማራቶን አሸንፎ በገባበት ወቅት Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ጉዬ አዶላ በበርሊን ማራቶን አሸንፎ በገባበት ወቅት

በቅርቡ በርሊን ማራቶን በተደረገው ውድድር ላይ የጉዬ አዶላ ስም አልተጠቀሰም። ቀጣዩን የዓለም አለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር ሬከርድ የሚሰብረው ማን ይሆን የሚለው መላ ምት ውስጥ ታላላቆቹ ሯጮች እነ ቀነኒሳ በቀለ፣ ዊልሰን ኪፕሳንግና ኢሉድ ኪፕቾጌ ነበሩ ግምት የተሰጣቸው።

ጉዬ እንኳን የማሸነፍ ግምት ሊሰጠው ይቅርና የማራቶን ውድድር ላይ ተወዳድሮ አያውቅም። ውድድሩ ሲያልቅ ግን ብዙዎች ስሙን አንስተውታል። ቀነኒሳ በቀለና ዊልሰን ኪፕሳንግ ሩጫውን መጨረስ ቢሳናቸውም፤ ጉዬ አዶላ እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ እልህ በሚያስጨርስ ሁኔታ ተወዳድሮ በጥቂት ሰከንዶች ተበልጦ ሁለተኛ ወጥቷል። ያስመዘገበውም ሰዓት በዓለም የማራቶን ሩጫ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት እንዲሁም ለኢትዮጵያም ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።

ማነው?

ብዙ ያልተባለለት የ26 አመት እድሜ ያለው ጉዬ አዶላ ድንገት ከየት ተገኘ?

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ቢሉ በምትባል አካባቢ የተወለደው ጉዬ፤ እንደ ቀደሙት አትሌቶች ሩጫን የጀመረው በህፃንነቱ ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት ነው። ዕድሜው 17 ሲሞላ ለቀጣይ ስልጠናዎች አዲስ አበባን መዳረሻው አደረገ። የአምቦ አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ የሆኑት አቶ ተፈሪ መኮንን በሩጫ ህይወቱ ላይ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ አበክሮ የሚናገረው ጉዬ፤ የሩጫ ህይወቱ ግን ማንሰራራት የጀመረው በኦሮሚያ የውሃ ሥራዎች ክለብ ቆይታው ነበር።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ጉዬ ከውድድሩ በኋላ ሜዳልያውን አጥልቆ

የመጀመሪያው ትልቅ ውድድር የነበረው ከሦስት ዓመታት በፊት ማራኬሽ ከተማ በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ነው። ይህም ለቀጣይ ውድድሮቹ ፈር የቀደደለት ሲሆን፤ በዚያው ዓመትም በተመሳሳይ ርቀት እንዲሁም በ10 ኪ.ሜ ብዙ ውድድሮችን አድርጓል። ነገር ግን ብዙ የሚያስደስት ውጤት ማምጣት አልቻለም።

"የጤና እክል ደርሶብኝ ስለነበር ምግብ መመገብ ከብዶኝ ነበር" በማለት የሚናገረው ጉዬ፤ "ሰው ካልበላ ደግሞ መሮጥ ከባድ ነው፤ ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ ቀላል የማይባሉ የእግር ጉዳቶች ደርሰውብኝ ነበር" ይላል። ብዙዎች አትሌቶች ከድህነት በመውጣት የተሻለ ህይወትን ለማግኘት ሩጫን እንደ መውጫ መንገድ ያዩታል። የጉዬም ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም።

"ከገጠር የሚመጡ ሰዎች ምን አይነት ህይወት እንደሚመሩ ከዚያው የመጡ ያውቁታል። ከደሃ ቤተሰብ ነው የመጣሁት፤ ሩጫ ከጀመርኩ በኋላ ግን የቤተሰቦቼ ህይወት ላይ መሻሻል አለ" በማለት ይናገራል።

  • የትውልድ ቀን፡ ጥቅምት 27 1984
  • የትውልድ ቦታ፡ ኦሮሚያ ክልል ቢሉ በሚባል ቦታ
  • ሙሉስም፡ ጉዮ አዶላ ኢደማ
  • ቁመትና ክብደት፡ 1.8 ሜትር፣ 60 ኪ.ግ
  • ወኪል/ማኔጀር፡ ጂያኒ ዲማዶና የአትሌቲክስ ፕሮሞሽን (ጣልያን)
  • ስፖንሰር፡ አዲዳስ

ከእሱ በፊት የመጡ የሩጫ ጀግኖች የሚላቸውን የእነ ቀነኒሳ በቀለ እንዲሁም የጥሩነሽ ዲባባን ስኬት ማየቱ ትምህርቱን ዘጠነኛ ክፍል ላይ አቋርጦ ለሩጫ ሙሉ ትኩረቱን እንዲሰጥ አደረገው። የእሁድ ዕለቱ ድልም በሩጫ ዘመኑ ሁለተኛ የሚባለውን የ24 ሺህ ዶላር ሽልማትን አስገኝቶለታል። ከሦስት ዓመታት በፊት ከፍተኛ የሚባለውን ብር ያገኘው ህንድ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ሲሆን፤ ከማሸነፉ በተጨማሪ አዲስ ክብረ-ወሰንም አስመዝግቧል። በወቅቱ የተከፈለውም 35 ሺህ ዶላር ነበር። ከበርሊን ውድድር በኋላ ጣልያናዊው ማኔጀሩ ዝናውም ሆነ የሚያገኘው ብር ይቀየራል በማለትም አስተያየቱን ይሰጣል።

"በዚህ ውድድር ላይ ያሸንፋል ተብሎ ስላልተጠበቀ፤ በአዘጋጆቹ የተሰጠው ክፍያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።" በማለት የሚናገረው ጂያኒ ዲማዶና "ከዚህ በኋላ ግን ጠቀም ያለ ክፍያ ይሰጡታል" ይላል።

ተጨማሪ የማራቶን ተስፋዎች

ጉዬ የእራሱ ቤት የለውም፤ አላገባም። ነገር ግን በበርሊን ላይ ካሸነፈ በኋላ ብሩህ ተስፋ እንደሚታየው ተናግሯል። ጂያኒ ዲማዶናም የአሁኑን የጉዬን ድል እንደ ትልቅ ስኬት በማየት፤ ቀጣዩ ዝግጅታቸው በሚያዝያ ወር ላይ ለሚካሄደው ትልቁ የለንደን ማራቶን መሆኑን ይናገራል።

Image copyright ጉየ አዶላ
አጭር የምስል መግለጫ ጉዬ አዶላ

ከዚህ ቀደም ለምን በማራቶን ሩጫ አላሸነፈም?

ምንም እንኳን በአሰልጣኞቹ አስተያየት ማራቶን ላይ እንዲሳተፍ ምክር ቢሰጠውም ጉዬ እንደሚለው ለማራቶን ሩጫ ምንም ፍላጎት አልነበረውም። በእድሜው ትንሽ መሆኑና እንዲህ አይነቱን ረዥም ርቀት ለመሮጥ ከባድ ነው በሚልም ይመልስላቸው ነበር። አሁን ግን ያለምንም ጥርጣሬ የማራቶን ሯጭ ነው። በበርሊን ያሸነፈበት ሰዓት ከአለም ሬከርድ በ49 ሰከንዶች ብቻ መለየቱ፤ በኢትዮጵያ ደረጃም ምርጥ የሚባል ሰዓት ማስመዝገብ አስችሎታል።

ጂያኒ ዲማዶና እንደሚለው በስልጠናው ወቅት ጥሩ ሰዓትን ቢያስመዘግብም ይህ ግን "ታላቁ ህልማችን" ነው። "ባስመዘገብነው ሰዓት በጣም ነው የተደነቅነው። እየጠበቅን የነበረው 2፡05 ወይም ደግሞ 2፡06 ነበር። በጭራሽ 2፡03፡46 ግን አልነበረም" ይላል። የጉዬ ረዳት አሰልጣኝ የሆነው ከሊል አማን በበኩሉ፤ ጉዬ ለረዥም ርቀት ሩጫ ለየት ያለ ተሰጥኦ እንዳለው ይመሰክራል። "አሯሯጡ፤ እግሩን የሚያነሳበት መንገድ ጉልበቱን በብቃት እንደሚጠቀም የሚያሳይ ነው። ለዛም ነው የማይደክመው።" በማለት ሙያዊ አስተያየቱን ይሰጣል። ጉዬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሩጫ የህይወቱን 'ሀ' ብሎ የጀመረው ከሦስት ዓመታት በፊት ዴንማርክ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ሲሆን፤ በወቅቱም የነሐስ ሜዳሊያ ለማግኘት ችሏል።

ተያያዥ ርዕሶች