የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ ድረ-ገፁ አድልዎ ይፈፅማል የሚለውን ክስ አጣጣለው

የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ

የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ፤ ዶናልድ ትራምፕ ፌስቡክ ሁል ጊዜ እነደሚቃናቸው የሰጡትን አስተያየት እንደማይቀበለው ተናግሯል። ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገፃቸው ላይ ፌስቡክ 'ፀረ-ትራምፕ' ዘመቻን በማስፋፋት አብሯል ሲሉ ወንጅለዋል።

ሩሲያ ባለፈው የአሜሪካ ምርጫ ላይ ጣልቃ ገብታለች ለሚለው ውንጀላ ፌስቡክ በቅርቡ ሶስት ሺ የሚደርሱ ድረ-ገፁ ላይ የወጡ የፖለቲካ ማስተዋወቂያዎችን ለኮንግረስ መርማሪዎች ያቀርባል።

ድረ-ገፁ እንደሚለው እነዚህ ማስተዋወቂያዎች በምርጫው ወቅትና በኋላ በሩሲያውን የተገዙ ናቸው።

ፌስቡክ፣ ትዊተርና ጉግል በምርጫው ላይ ሩሲያ ምርጫውን ላይ ነበራት ስለተባለው ጣልቃ ገብነት ለሚደረገው ምርምራ ቃላቸውን እንዲሰጡ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በአሜሪካ ሴኔት የደህንንት ኮሚቴ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ማርክ ዙከርበርግ በፌስቡክ ገፁ ለዶናልድ ትራምፕ ትችት በሰጠው ምላሽ "ለሁሉም ሀሳቦች የሚሆን መድረክ ለመፍጠር እየጣርን ነው" በማለት ነው። ነገር ግን "ችግር ያለባቸው ማስተዋወቂያዎች" ፌስቡክ ላይ እንደነበሩ የማይክደው ማርክ፤ ከዚህ ጋር ሲወዳደር ግን የፌስቡክ አዎንታዊ አስተዋፅኦ የጎላ ነው ይላል።

"የፌስቡክ ሚና ለሰዎች ድምፅ ከመሆን ጀምሮ፣ ተወዳዳሪዎች ከህዘቡ ጋር በቀጥታ የሚገናኙበትን መድረክ ማመቻቸት እንዲሁም ሚሊየኖች መምረጥ እንዲችሉ አስችሏቸዋል። " ይላል።

እንደ ማርክ ዙከርበርግ አስተያየት ተወዳዳሪዎች በምረጡኝ ዘመቻቸው በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር መዋዕለ-ንዋይ ያፈሰሱ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ "ችግር ካለባቸው ማስተዋወቂያዎች ጋር ሲወዳደር አንድ ሺ እጥፍ በልጦ ይገኛል።"

የ33 ዓመቱ ማርክ ዙከርበርግ ትራምፕ በተመረጡበት ወቅት በፌስቡክ ላይ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎች የምርጫውን ውጤት ቀይረውታል የሚለውን አባባል ማጣጣሉን አሁን ተፀፅቶበታል።

"ሁሉንም የሚያሳትፍ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጠንክረን እንሰራለን" በማለትም ቃል ገብቷል። ከዚህም በተጨማሪ "ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመንዛት እንዲሁም ምርጫን ለመቀልበስ የሚሞክሩትን እንከላከላለን። "ብሏል።

ከክሬምሊን የወጡ መረጃዎች ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች የሚለውን ውንጀላ የካዱ ሲሆን፤ ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸውም ከሩሲያ ጋር አላስፈላጊ ግነኙነት ነበራቸው የሚለውንም አጣጥለዋል።

ነገር ግን የአሜሪካ የደህንነት መረብ ካገኘው መረጃ ተነስተው እንዳጠቃለሉት ሩሲያ በምርጫው ትራምፕ እንዲያሸንፉ ሞክራለች። ይህ ጉዳይ መቋጫ ያላገኘ ሲሆን የኮንግረሱ ኮሚቴ እንዲሁም የኤፍቢአይ የምርመራ ክፍልም ጉዳዩን በጥልቅ እየመረመሩት ይገኛሉ።