ካታሎንያ ከስፔን ነፃ ከወጣች ባርሴሎና በላሊጋው የሚኖረው ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

ባርሴሎን የእግር ኳስ ቡድን Image copyright Getty Images

የስፔኑ ባርሴሎና የእግር ኳስ ክለብ በካታሎንያ የነፃነት ጉዳይ ላይ ጥግ ቆሞ ተመልካች አይመስልም።

የባርሴሎና የእግር ኳስ ክለብ በፈረንጆቹ ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም. በሚካሄደውና የካታሎንያን ነፃነት በሚወስነው ሕዝበ ውሳኔ ላይ ገለልተኛ መሆን የፈለገ አይመስልም። ማዕከላዊው የስፔን መንግስት የሕዝበ-ውሳኔ ሂደቱን ሕገ-ወጥ በማለት ይኮንነዋል።

የሕዝበ-ውሳኔው ጉዳይ አሁን ላይ እየተካረረ የመጣ ሲሆን የስፔን ፖሊስ ሕዝበ-ውሳኔውን እንዲያግዙ የተዘጋጁ ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር ሲያውል የንቅናቄውን መሪዎችንም ማሰሩም ታውቋል።

ዋና ከተማዋ ባርሴሎና የሆነው የካታሎንያ ግዛት ነፃ የምትወጣ ከሆነ የስፔን ላሊጋ ሃያል ክለብን ላናየው ነው ማለት ነው? ኤል-ክላሲኮ የሚባል ነገር አይታሰብም? የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።

የባርሴሎና አቋም. . .

የባርሴሎና መሪዎች በፖሊቲካ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ ብዙ ጊዜ ሲናገሩ ይደመጣል። ክለቡ ለነፃነቱ መሳካትም ይፋዊ አዎንታዊ ድጋፉን አያሳይ እንጂ በያዝነው ወር መባቻ ላይ ነፃነቱን እንደሚደግፍ የሚያሳይ ፍንጭ ሰጥቷል።

የስፔን ፖሊስ የካታሎንያ ባለስልጣናትን ባሰሩበት ወቅት ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መግለጫ መልቀቁ ይታወሳል። ክለቡ በለቀቀው መግለጫ "ዲሞክራሲ፣ የመናገር ነፃነት እና የራስን ዕድል በራስ መወሰንን እንደግፋለን" በማለት አስረግጧል።

ምንም ይፈጠር ምንም ባርሴሎናዎች በፈለጉት ሊግ ለመጫወት የሚያስችል ምርጫ እንዳላቸው እሙን ይመስላል።

"ልክ እንደስፓኝዮል ሁሉ እኛም በሊጉ እንቆያለን" ይላሉ የክለቡ ምክትል ፕሬዝደንት ካርሌስ ቪላሩቢ። ስፓኝዮል የካታላን ሁለተኛ ከለብ ሲሆን፣ የክለቡ ደጋፊዎች ከስፔን ጋር መቆየትን እንደሚደግፉ ይነገራል።

ላሊጋውን የሚያስተዳድረው 'የስፔን ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ሊግ' ፕሬዝደንት ሃቪዬር ቴባስ እንደሚሉት ከሆነ ግን "ካታሎንያ ነፃ የምትወጣ ከሆነ ባርሴሎና በየትኛው ሊግ እንደሚጫወት ሊመርጥ አይችልም" ብለዋል።

Image copyright Getty Images
  • ባርሴሎና 24 ጊዜ የላሊጋውን ዋንጫ አንስቷል
  • ከየትኛውም የስፔን ክለብ በላይ 29 ጊዜ የኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫን አንስቷል
  • ባርሴሎና ከሪያል ማድሪድ ጋር ካደረጋቸው 232 ጨዋታዎች ማድሪድ 95ቱን ሲያሸንፍ ባርሳ 91 ጊዜ አሸንፏል፤ 46 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል

ታማኝ ምንጭ ለቢቢሲ እንደተናገረው ክለቡ ስለሁኔታው ምንም ዓይነት መግለጫ ለመስጠት ዝግጁ አይደለም። "እንደኛ እምነት ከሆነ በዓለም የታወቅን ክለብ ነን። የስፔንን ጨምሮ ማንኛውም ሊግ እኛን ለመቀበል ዝግጁ ይመስለኛል።"

"ስፔን ላሊጋን ካለባርሴሎና ማሰብ ይከብደኛል" ይላል የሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን። "እንደእግር ኳስም ሆነ እንደጠቅላላ ስፖርት ደጋፊ ሊታየኝ አይችልም።"