የአይ ኤስ መሪ ባግዳዲ ድምፁ ተሰማ

የአይ ኤስ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የአይ ኤስ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ

የአይ ኤስ ታጣቂዎች የመሪያቸው የአቡበከር አል ባግዳዲ ነው ያሉትን የተቀዳ ድምፅ በድረ-ገፅ ለቀቁ።

በዚህ በተቀዳው ድምፅ ላይ ተናጋሪው የአይ ኤስ መሪን በሚመስል ድምፅ፤ የሰሞኑን ሰሜን ኮሪያ ጃፓንን እንዲሁም አሜሪካንን እንዳስፈራራች ይጠቅሳል።

ከዚህም በተጨማሪም የአይ ኤስ ጠንካራ ይዞታ የነበረቸው ሞሱልን ለማስመለስ የጦርነትን አስፈላጊነት ያወራል። ሞሱል በሐምሌ ወር በኢራቅ ኃይሎች እጅ ተመልሳ መግባቷ የሚታወስ ነው።

በአደባባይ ከታየ ሦስት ዓመት ያለፈውን ባግዳዲን አድኖ ለመያዝ የሚደረገውን ጥረት ለተባበረ የ25 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ይሰጣል ተብሎ የታወጀ ሲሆን፤ በዕጣ ፈንታው ላይ ብዙ መላምቶች እየተነገሩ ነው።

ለመጨረሻ ጊዜ አቡበከር አል ባግዳዲ የታየው ሞሱል በሚገኘው ታላቁ የአል ኑሪ መስጊድ ላይ በሰብከበት ወቅት ሲሆን፤ አይ ኤስ ከተማዋን ተቆጣጥሮ የኢስላማዊ መንግሥት አካል መሆኗን ባወጀበት ወቅት ነበር።

ይህንን ድምፅ አስመልክቶ አይ ኤስን እየተዋጋ ያለው የአሜሪካ ኃይል ቃል አቀባይ ራያን ዲሎን ሲጠየቁ "ስለሞቱ ምንም የተጣራ መረጃ በሌለበት ሁኔታ፤ በህይወት እንዳለ ነው የምናስበው" በማለት ተናግረዋል።

ከሱኒ ሙስሊም ጎራ የሚፈረጀው የአይ ኤስ ታጣቂ ቡድን ሰላማዊ ህዝብ ላይ ባነጣጠረው ከፍተኛ ጭካኔ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ሥጋትን ፈጥሯል። ባለፈው ዓመትም ከባድ ሽንፈት ገጥሞት ወደ ኢራቅና ሶሪያ ተገፍቷል።

ይህ የ45 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ድምፅ የወጣው ከአይኤስ ቡድን ጋር ግነኙነት ባለው ድረ-ገፅ ላይ ሲሆን፤ ከባለፈው ኅዳር ወር ወዲህ እንደዚህ አይነት መረጃ ሲወጣ የመጀመሪያው ነው።

ይህንንም ተከትሎ ባግዳዲ በአይ ኤስ ቁጥጥር ስር ባለው በኢራቅና ሶሪያ ድንበር አካባቢ አሁንም ተደብቆ ይሆናል የሚሉ ግምቶች እየተሰጡ ነው።

በዘርፉ ላይ ያሉ አጥኚዎች እንደሚሉት አቡበከር አል ባግዳዲ ያለበትን የሚያውቁ እፍኝ የማይሞሉ ሰዎች ናቸው። ይህ ክስተት ልዩ ኃይልን አደራጅታ እያደነችው ላለችው አሜሪካ አስቸጋሪ ሁኔታን እየፈጠረ ነው።