ለነፃነት በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ካሜሮናውያን ህይወታቸውን አጡ

ካሜሮን የተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ
አጭር የምስል መግለጫ ካሜሮን የተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ

የእንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆነው የ ካሜሮን ግዛቶች ነፃነትን የሚደግፉ ሰልፈኞች ያደረጉትን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ የካሜሮን ወታደሮች ስምንት ሰዎች ገድለዋል።

ሰላማዊ ሰልፎቹ የተካሄዱት የነዚህ ግዛቶች ከካሜሮን ጋር ያደረጉትን ውህደት አስመልክቶ 56ኛው አመት ክብረበአል ላይ ነው። የኩምቦ ከተማ ከንቲባ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በጥይት ተመትተው ከሞቱት መካከል አምስቱ በእሳት ከተያያዘ እስር ቤት ለማምለጥ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው። ከባለፈው አመት ጀምሮ ሰልፈኞቹ ባደረጉዋቸው ተቃውሞዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን የመብት አቀንቃኞችም የታሰሩ እስረኞችም እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

ካሜሮን በእንግሊዝና በፈረንሳይ ለሁለት ተከፍላ ቅኝ ግዛት የተገዛች ሲሆን እአአ በ 1961 ሁለቱ ግዛቶች ተጣምረው አንድ አገር መስርተዋል። ሆኖም የ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ብዙ የህዝብ ቁጥር ባለው የፈረንሳይኛ ተናጋሪ መድልዎ ይደርስብናል ሲሉም ይወነጅላሉ። የ ኩምቦ ከንቲባ ዶናተስ እንጆነግ ፎንዩይ እንደሚሉት የተገንጣዮች ጎራ የሆነው ባንዲራ ዋነኛ በሚባሉ በከተማዋ ቦታዎች ተሰቅለዋል። ሌሎችም ሰላማዊ ሰልፎች በተለያዩ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆነው የ ካሜሮን ግዛቶችም ተደርገዋል። የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ተምሳሌታዊ የሆነ የነፃነት አዋጆችንም በዚሁ አጋጣሚ አሰምተዋል።

በተቃራኒው የዚህ ሰልፍ ተቃዋሚዎችም መንግስትን በመደገፍ አንድ ካሜሮን በሚል መፈክር በዱዋላ ከተማ ሰልፍ አካሂደዋል። በባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ካሜሮን ህዘባዊ የሆኑ ስብሰባዎችን እንዲሁም ጉዞዎችን የእንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆነው የ ካሜሮን ግዛቶች አግዳለች። በእነዚህ ግዛቶች ተቃዋሚ ሰልፎችም የጀመሩት ባለፈው አመት ሲሆን ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መገለል እንዲሁም ፈረንሳይኛ ቋንቋና ህጋዊ ስርአቱ በግዴታ ተጥሎብናል የሚሉ ጥያቄዎችንም አንስተዋል። ለመብት የተጀመረውም እንቅስቃሴ አሁን ወደ ነፃነት ጥያቄም ሊቀየር ችሏል።

ተያያዥ ርዕሶች