ላስ ቬጋስ ውስጥ በተፈፀመ ጥቃት ከ59 በላይ ሰዎች ተገደሉ

የጥቃቱ ፈፃሚ ስቴፈን ፓዶክ Image copyright Facebook
አጭር የምስል መግለጫ የጥቃቱ ፈፃሚ ስቴፈን ፓዶክ

በአሜሪካ ላስቬጋስ ውስጥ የሙዚቃ ኮንሰርት በታደሙ ሰዎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ 59 ሰዎች ሲገደሉ ከ 500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆሰሉ።

ስቴፈን ፓዶክ የተባለው የ64 ዓመት ታጣቂ፤ ማንዳላይ ቤይ ከተሰኘ ሆቴል 32ኛ ፎቅ ላይ ሆኖ በአቅራቢያው ይካሄድ በነበረና 22 ሺህ ሰዎች በታደሙበት የሙዚቃ ፌስቲቫል ተሳታፊዎች ላይ ተኩስ ከፍቶ ነው ጉዳቱን ያደረሰው።

የአካባቢው ነዋሪ እንደሆነ የታወቀው ተጠርጣሪ ከጥቃቱ በኋላ በፖሊስ እንደተገደለ ቢነገርም፤ ፖሊስ በሰጠው መረጃ መሠረት ግን የጦር መሳሪያዎችን ያስቀመጠበትን ክፍል ሰብረው ሲገቡ እራሱን አጥፍቶ አግኝተውታል።

ጥቃቱ በአሜሪካ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ከተፈፀሙት የከፋው እንደሆነ ተነግሯል።

ፖሊስ እንዳለው ግለሰቡ ጥቃቱን የፈፀመው ብቻውን ሊሆን ይችላል ተብሎ ቢታመንም ከጥቃቱ ቀደም ብሎ አብራው ነበረች የተባለችን እስያዊት ሴትን ከሃገር እንደወጣች ፖሊስ አስታውቋል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
በላስቬጋስ የሙዚቃ ኮንሰርት ታዳሚዎች ላይ ተኩስ ተከፈተ

የሆስፒታል ቃል አቀባይ እንደገለፀችው ከቆሰሉት መካከል 14ቱ በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

ጥቃቱ ወደተፈፀመበት ሥፍራ የታጠቁ ፖሊሶች እንደደረሱ የተወሰነው የከተማዋ ክፍል እንቅስቃሴ ዝግ ሆኖ ነበር።

ሰዎች በሆቴሎች፣ በምግብ ቤቶችና በላስ ቬጋስ ማካረን አየር ማረፊያ ውስጥ ከጥቃቱ ለማምለጥ ተጠልለዋል።

Image copyright Getty Images

የዚህ ጥቃት ዜና ከተሰማ በኋላ የተወሰኑ በረራዎች አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ተደርጓል።

ይህ የካንትሪ ሙዚቃ ኮንሰርት ከአርብ ጀምሮ በጥቃቱ አቅራቢያ በሚገኙ በርካታ ሆቴሎች ውስጥ ሲካሄድ የቆየ የኮንሰርት አካል ነበር።