ከሰሞኑ የኢትዮ-ቴሌኮም የተንቀሳቃሽ ስልኮች ምዝገባ ጀርባ

ሰሞኑን ኢትዮ-ቴሌኮም ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ለመመዝገብ የወጣው ጥሪ
አጭር የምስል መግለጫ ሰሞኑን ኢትዮ-ቴሌኮም ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ለመመዝገብ የወጣው ጥሪ

ሰሞኑን ኢትዮ-ቴሌኮም በሃገሪቱ ዉስጥ ያሉ ሁሉም የሞባይል ቀፎዎች እና ሌሎች በሲም ካርድ የሚሰሩ የቴሌኮም መገልገያ መሳሪያዎች እንዲመዘገቡ ባስቀመጠው ቀነ-ገደብ መሰረት ብዙዎች ተመዝግበዋል።ይህንንም ተከትሎ ምዝባው ምንድን ነው? ለምን አስፈለገ? እንዲሁም መንግስት በዜጎች ላይ የሚያደርገውን "የስለላ ስራ ለማጧጧፍ ነው" የሚሉ መረጃዎች ከተለያየ የሕብረተሰቡ ክፍል እየመጣ ነው።

ተንቀሳቃሽ ስልኮች ከተመረቱ በኋላ አምራቾቹ 15 አሃዝ የያዙ ቁጥሮች ለእያንዳንዱ ስልኮች ይሰጣል፤ ይህም አይኤምኢአይ (IMEI) ቁጥር ይባላል። ይህ ቁጥር አንድን ስልክ ከሌላ የሚለይ እንደሆነ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ደኅንነት ባለሙያው አቶ ተክሊት ኃይላይ የሚናገር ሲሆን ቁጥሩም ለአንድ ስልክ ብቻ የሚሰጥ ነው።

ምዝገባው አዲስ እንዳልሆነ የሚናገረው አቶ ተክሊት፤ አሁን የተደረገው ምዝገባ በተጨማሪም ተንቀሳቃሽ ስልኮችን መክፈትና መዝጋት ለማስቻል ኮርፖሬሽኑ አዲስ ሶፍትዌርንም አስገብቷል።

ለምን መመዝገብ አስፈለገ?

የኢትዮ-ቴሌኮም የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ እንደሚሉት የዚህ ምዝገባ ዋና አላማ ተገልጋዩን ደንበኛ ከስርቆት እንዲሁም ደረጃቸውን ያልጠበቁ ስልኮች ከሚያስከትሉት የጤናና የአገልግሎት ጥራት መጓደል ለመከላከል ነው። በሲም ካርድ የሚሰሩ የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎች በስርቆትም ሆነ በሌላ ምክንያት ከደንበኞች እጅ ሲጠፉ ደንበኞች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ቀፎው የቴሌኮም አገልግሎት እንዳይሰጥ ለማድረግም ይረዳልም ይላሉ። እነዚህንም ተንቀሳቃሽ ስልኮች በጥቁር መዝገብ ላይ የሚያሰፍሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ሃገር መጠቀም አይቻልም።

አቶ አብዱራሂም እንደሚሉት በህጋዊ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ እና ኦሪጅናል የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎች የመኖራቸውን ያህል ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ጥራታቸውንና ደረጃቸውን ያልጠበቁ ተመሳስለው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መሣሪያዎች አገልግሎት ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡

ይህም ሁኔታ አገር ውስጥ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ገጣጥመው የሚሸጡ ነጋዴዎች ቀረጥ ከፍለው በሚያስገቡት ላይ ኢ-ፍትሐዊ የገበያ ውድድር እየፈጠረ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አብዱራሂም፤ ይህ ምዝገባ ይህንን ለማስቀረት ይረዳልም ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሃገሪቷ የምታገኘውን ቀረጥ ለማሳደግ፣ በኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ኔትወርክ ውስጥ ያሉ ሁሉንም የሞባይል ተጠቃሚዎችን ባሉበት ለመለየትና በባለቤቱ ወይም በደንበኛው ስም ለመመዝገብ ያስችላል።

በአጠቃላይ በሃገሪቷ 58 ሚሊየን ያህል ደንበኞችን ሲስተሙ በቀጥታ እንደመዘገባቸው የሚናገሩት አቶ አብዱራሂም ተጨማሪ ቀፎ እንዲሁም አይ ፓድና ሌሎች ሲም ካርድ የሚወስዱ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ሲም ካርድ በማስገባት መመዝገብ ይችላሉ።

ይህ የምዝገባ ሂደት ለኢትዮጵያ የተለየ እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ አብዱራሂም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የቴሌኮም አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ባደጉ ሃገራትና በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጭምር እየተተገበረ ያለ ዘመናዊ አሰራር ነውም ይላሉ።

ከምዝገባው ጀርባ?

አቶ ተክሊት በበኩሉ የግለሰቦችን ፕራይቬሲ (ግላዊ ምስጢር) በተመለከተ ምንም አይነት ለውጥ እንደማያመጣ ቢናገሩም ቁጥጥርን በተመለከተ ሥራን እንደሚያቀል ጨምረው ይገልፃሉ። "ሌላ ጊዜ አስመስለው በተሰሩ ስልኮች ያመልጡ የነበሩት አሁን በዚህ አሰራር ማምለጥ አይችሉም" ይላሉ።

የ አይኤምኢአይ ቁጥር ግለሰቦች አድራሻቸውን ቢቀይሩ እንኳን በቁጥሩ አማካይነት ትክክለኛ አድራሻቸውን ለማወቅ ያስችላል። "የምትከታተለውን ሰው እንዳያመልጥህ ይረዳሃል።" በማለትም ያስረዳል።

አቶ ተክሊት እንደሚለው አንድ ሰው ሲምካርዱን ትቶ ሌሎች አይኤምኢአይ ቁጥራቸው የማይታወቁ ስልኮችን በመያዝ በሌላ ሲም ካርድ መጠቀም ይችል ነበር "ሲምካርድ በመቀየር ያመልጥ የነበረ ሰው አሁን አያመልጥም"ይላል።

አጭር የምስል መግለጫ ጦማሪው በፍቃዱ ኃይሉ

መንግሥት ምንም እንኳን ስርቆትን ለመከላከልና አስመስለው የተሰሩ ከጥራት በታች ያሉ ስልኮችን አገር ውስጥ እንዳይገቡ ለመከላከል ነው ቢልም ከዚህ ቀደም ስልካቸው ተጠልፎ እንደ መረጃ የቀረበባቸው እንደ በፍቃዱ ኃይሉ ያሉ ጦማሪዎች "አስጨናቂ ጉዳይ ነው" በማለት ይገልፁታል። የሽብር ድርጊት ፈፅማችኋል በሚል ምክንያት ታስረው ከነበሩት የዞን ዘጠኝ ቡድን አባል የሆነው በፍቃዱ "መንግስት በስልክ በኩል ዜጎቹን ይሰልላል የሚባለው ውሸት አይደለም። " ይላል።

ከመታሰራቸው በፊት ለአንድ ዓመት ያህል ያለምንም ፍርድ ቤት ፍቃድ ስልካቸው እንደተጠለፈ የሚናገረው በፍቃዱ እንደ መረጃም የተያያዘው ሰነድ የስልክ ንግግሮቻችን ናቸው ይላል። "እኛ በቁጥጥር ስር የዋልነው ሚያዝያ 2006 ዓ.ም ቢሆንም የቀረበብን መረጃ ከግንቦት 2005 ጀምሮ የተቀዳ ነው።" በማለትም ያስረዳል።

ምንም እንኳን በፀረ-ሽብርተኝነት ህጉ የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሽብርተኝነት የተጠረጠረን ሰው የስልክ፣ የፋክስ፣ የሬድዮና የኢንተርኔት፣ የኤሌክትሮኒክስና የፖስታ ግንኙነቶችን የመሳሰሉትን ለመጥለፍ ወይም ለመከታታል የፍርድ ቤት ፍቃድ እንደሚያስፈልግ በግልፅ ቢያትትም እንደ በፍቃዱ ላሉ በሽብር ለተፈረጁ ግለሰቦችም ህጉ ተፈፃሚ እንዳልሆነም ጨምሮ ይናገራል።

ብዙ የሽብር ክሶችን የተከታተለው በፍቃዱ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች የሚቀርብባቸው መረጃ በስልክ ያደረጉዋቸው ንግግሮች መሆናቸውንም ይጠቅሳል።

ከተፈታ በኋላ በነበረው የስልክ ቁጥር መጠቀም ከብዶት የተለያዩ ሲምካርዶችን እየለዋወጠ እንደነበር የሚናገረው በፍቃዱ፤ በድጋሚ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ከታሰረ በኋላ "ወደ ዱሮው እንደተጠለፈ ወደማውቀው ስልክ ተመልሻለሁ፤ ሲም ካርድ እየቀያየርኩ መሸወድ እችል ነበር። ነገር ግን መንግሥት የማወራውን ሰምቶ ንፁህነቴን ቢረዳልኝ ይሻላል የሚል ነው"በማለትም ይናገራል።

ምንም እንኳን በፍቃዱ ወደ ቀድሞ ሲም ካርዱ ቢመለስም ብዙ ታስረው የተፈቱ ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች ሲም ካርዳቸውን እንደሚቀይሩ በፍቃዱ ይናገራል። "ያለፍርድ ቤት ፍቃድ የስልክ ንግግሮችን የሚሰማ የመንግሥት ፀጥታ ኃይል መኖሩ በራሱ የሚፈጥረው የሚያሸብር ስሜት አለው" ይላል በፍቃዱ።

የ አይኤምኢአይ ቁጥር ምዝገባ መምጣት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የስለላ መረብን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያጠናክረውም ጨምሮ ይናገራል። "ፕራይቬሲን ከማጣት በተጨማሪ አሁን ደግም አካላዊ ነፃነታችንም ሊገደብ ነው" በማለት ይናገራል።

አጭር የምስል መግለጫ የሶፍትዌር ባለሙያው ሐፍቶም በርኸ

ሌላኛው የሶፍትዌር ባለሙያና የየሓ ቴክኖሎጂስ ሥራ አስኪያጅ የሆነው ሓፍቶም በርኸ የቴሌፎን ጠለፋ በተለያዩ ሃገራት በፍርድ ቤት ትእዛዝ ይደረጋል፤ ይህም ህጋዊ ጠለፋ ይባላል ይላል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የጠለፋ ተግባር ይፈፀማል። ይህንንም ተግባር ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተደራጁ ቡድኖች እንዲሁም በመንግሥታት ጭምር እንደሚካሄድም ይናገራል።

ከዚህ ቀደም የነበሩ ጠለፋዎች

ሂውማን ራይትስ ዎች ከሁለት ዓመት በፊት ባጠናቀረው ሪፖርት ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን እንደተናገሩ በኬንያ እንዲሁም በአውሮፓ የመኖርያ ፍቃድ አግኝተው ወይም ጥገኝነት ጠይቀው የሚጠባበቁ በርካታ ግለሰቦች ስልካቸውና ኢሜይላቸው በፀጥታ ኃይሎች ተጠልፎ የተናገሩትና የተፃፃፉትን መልሰው ለራሳቸው እንዳሳዩዋቸው ይናገራሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግስትም በተለያዩ ጊዜያት በሽብር የተጠረጠሩ ሰዎች ያደርጓቸዋል የተባሉ የተጠለፉ የስልክ ንግግሮች በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር መሰማቱ የሚታወስ ነው።

ከቻይናና ከጣልያን የተገኙ የጠለፋ ሶፍትዌር ቴክኖሎጂዎች በተለይ በኢትዮጵያ ያለአግባብ የሰዎችን ግለሰባዊ ሚስጢራዊነትን ለመበርበር ተግባር እንደሚውል ሲንትያ ዎንግ የተባሉ በሂውማን ራይትስ ዋች የኢንተርኔት ከፍተኛ ተመራማሪ ይናገራሉ። ይህ ድርጊት መሰረታዊ የሆኑ ሰብአዊ መብትን የሚጥስ ድርጊት እንደሆነ፤ ሃገራቱም እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት ከመሸጣቸው በፊት ለምን ጥቅም እንደሚዉሉ ማረጋገጥ አለባቸውም ይላሉ ተመራማሪዋ።

ምዝገባውን በተመለከተ ብዙዎች መንግሥት ዜጎቹ ላይ ጠለፋ ለማካሄድ እንዲቀለው ነው ሲሉ፤ ሃፍቶምም የሰዉን ጥርጣሬ አያጣጥለውም።

የአይኤምኢአይ ቁጥር ምዝገባ ዋናው የመንግሥት ትኩረት ስርቆትን እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ የሚያስቀምጣቸውን ጥቅሞች ለመስጠት ቢሆንም ስለላን በተመለከተ ለመንግሥት ቀላል ሥራ እንደሚያደርግለትም ጨምሮ ይጠቅሳል።

ይህ አስተያየት ከፍራቻ የመነጨ ነው የሚሉት አብዱራሂም አንድን ሰው ለመከታተል ከአይኤምኢአይ ቁጥር ጋር እንደማይገናኝና ክትትልን በተመለከተ ኤችኤልአር ከሚባል ሶፍትዌር ጋር የተያያዘ አሰራር እንዳለም ይናገራሉ።