ኢትዮጵያ በኮሌራ በርካታ ሰዎች ከሚሞቱባቸው ሃገራት ሁለተኛ ናት

የኮሌራ ህመምተኞች Image copyright EPA

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እአአ በ2030 በኮሌራ ሰበብ የሚደርሰውን ሞት 90 በመቶ ለማስቀረት ፈረንሳይ ላይ ስብሰባ ተቀምጠዋል።

ንፅህናውን ባልጠበቀና በተበከለ ውሃ አማካኝነት የሚተላለፈው ኮሌራ በየዓመቱ የመቶ ሺዎችን ህይወት ይቀጥፋል። ከአስር ሺህ በላይ ሞት የሚደርሰው ደግሞ በኢትዮጵያ ሲሆን ይህም ቁጥር ሃገሪቷን በዓለም ሁለተኛ ያደርጋታል።

የተለያዩ መንግሥታት፣ የአለም ጤና ድርጅት፣ የእርዳታ ድርጅቶች፣ ለጋሾች በተቀናጀ መንገድ በሽታውንም ለማጥፋት ቃል ሲገቡ ይህ የመጀመሪያው ነው። በአሁኑ ወቅትም የመን መጥፎ የሚባለውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በመታገል ላይ ናት።

በጦርነት በፈራረሰችው በዚህች ሃገር ኮሌራ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዛመተ ሲሆን ይሄም በውሃ እጥረትና በንፅህና መጓደል አማካኝነትም የመጣ ነው።

በቀላሉ መፈወስ በሚችለው በዚህ በሽታም ከ770 ሺህ በላይ ተጠቅተዋል፤ ከ2 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። እንደተነገረውም አብዛኛዎቹ ተጠቂዎች ህፃናት ናቸው።

የድህነት በሽታ

በተበከለ ውሃና ምግብ የሚመጣው ይህ በሽታ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከትን ያካትታል። በተጨናነቀና በንፅህናው ባልተጠበቀ አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች መካከል በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት የሚዛመት ሲሆን በሌሎች አካባቢዎችም በአጭር ጊዜ የመዛመት ባህርይ አለው።

በሽታው በህክምና የሚድን ሲሆን፤ ጨርሶ እንዳይከሰት ደግሞ የንፁህ ውሃና የንፁህ መፀዳጃ ቤት አቅርቦትን ማሳደግ ወሳኝ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ሁለት ቢሊዮን ህዝብ የንፁህ ውሃ አቅርቦት የሌለው ሲሆን ይሄም ለኮሌራ ተጋላጭነትን ይጨምረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጤና ወኪሎች እንደሚሉት ደካማ የሆነ የጤና ሥርዓት በተዘረጋበት ሁኔታ እንዲሁም በሽታው ሲጀምር አለመታወቁ በፍጥነት ለመዛመት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።

Image copyright Getty Images

ፍረት ካባ

ዋተር ኤይድ የተባለ የ እርዳታ ድርጅት ለአንድ ሰው ንፁህ ውሃ እንዲሁም ንፅህናው የተሟላ አቅርቦት ለመስጠት 30 ዶላር ብቻ እንደሚያስፈልግ ግምቱን ሰጥቷል። የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ቲም ዌይንራይት እንደሚሉት "በአስደናቂ ሁኔታ ርካሽ ነው።''

"በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ በኮሌራ የሚጠቁ አካባቢዎችን ብንመለከት ድህነት የሰፈነባቸውና ከተለያዩ አገልግሎቶች የተገለሉ ናችው። ይህ በቀላሉ ሊድን የሚችል በሽታ በየዓመቱ 2.9 ሚሊዮን ህዘብን ለስቃይ ይዳርጋል፤ 95 ሺህ ህዘብንም የመግደል አቅም አለው። ይህ በዓለም አቀፍ ሁኔታ የሚያሳፍር ነው።" በማለትም ይናገራሉ።

በፈሳሽ መልክ የሚሰጠው ክትባትም በሽታውን ለመከላከል ጠቃሚ ነው። ምንም እንኳን ክትባቱ እንደመከላከያ የሚያገለግለው ለሦስት ዓመታት ቢሆንም፤ ወረርሽኙ አደገኛ በሆነባችው አካባቢዎች የሺዎችን ህይወት ለመታደግ ያስችላል። የሰሜን አውሮፓ ሃገራትና አሜሪካ የኮሌራ በሽታን ከ150 ዓመታት በፊት ለማጥፋት ችለዋል።

ለም አቀፍ ደረጃ በመት ውስጥ ኮሌራ ያስከተለው ጉዳት

  • ህንድ፡ 675,188 በበሽታው የተያዙ፣ 20,266 የሞቱ
  • ኢትዮጵያ፡ 275.221 በበሽታው የተያዙ፣ 10,458 የሞቱ
  • ናይጀሪያ፡ 220,397 በበሽታው የተያዙ፣ 8,375 የሞቱ
  • ሃይቲ፡ 210,589 በበሽታው የተያዙ፣ 2,584 የሞቱ

ምንጭ፡ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ