የግዙፉ ዘንዶና የጥበቃ ሰራተኛው ትንቅንቅ መጨረሻ

ዘንዶ Image copyright AFP/GETTY IMAGES

የጥበቃ ሰራተኛው ከግዙፍ ዘንዶ ታግሎ ዘንዶውን ለዕራት እራት አድሶታል።

በኢንዶኔዢያ ሱማታራ በምትባል ግዛት ውስጥ ሮበርት ናባባን የተባለ የጥበቃ ሰራተኛ በእርሻ ውስጥ ከግዙፍ ዘንዶ ጋር ይፋጠጣል።

የጥበቃ ሰራተኛው ሮበርት ከመሸሽ ይልቅ 8 ሜትር ቁመት ካለው ዘንዶው ጋር ትግል ገጠመ።

ሮበርት ዘንዶውን ለማሸነፍ የቻለውን ሁሉ አደረገ፤ ከረጀም ትግል በኋላ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ደርሰውለት ዘንዶውን ለማሸነፍ ቻለ።

የጥበቃ ሰራተኛው ከዘንዶው ጋር ባደረገው ፍልሚያ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

ከዘንዶው ጋር ለምን ትግል መግጠም እንደፈለገ ግልፅ ባይሆንም፤ የአካባቢውን ነዋሪዎች ደህንነት ለመጠበቅ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

የአካባቢው ፖሊስ ለኤ ኤፍ ፒ የዜና አገልግሎት እንደገለጸው፤ ዘንዶው የሮበርትን ግራ እጅ በፊት ጥርሶቹ ነክሶ ይዞት ስለነበረ እጁ ከመቆረጥ ለጥቂት ነው የተረፈው ።

የጥበቃ ሰራተኛው አሁን በህክምና ላይ ይገኛል።

የዘንዶው መጨረሻም አላማረም። ለእይታ በመንደሩ ውስጥ ተንጠልጥሎ ከዋላ በኋላ ሥጋው ተከታትፎና ተጠብሶ እራት ሆኖዋል።

ከዚህ በፊትም እዚያው ኢንዶኔዢያ ውስጥ አንድ ግዙፍ ዘንዶ የአካባቢውን ነዋሪ ውጦ አስክሬኑ ከዘንዶው ሆድ ውስጥ ወጥቶ ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች