ስለኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ስዕሎች ምን ያህል ያውቃሉ?

ጎንደር የሚገኘው የደብረብርሀን ስላሴ ቤተክርስቲያን ስዕሎች Image copyright ABEBAW AYALEW
አጭር የምስል መግለጫ ጎንደር የሚገኘው የደብረብርሀን ስላሴ ቤተክርስቲያን ስዕሎች

ኢትዮጵያ ከሶስት ሺ አመታት የሚሻገር የስነ ጥበብ ታሪክ እንዳላት አጥኝዎች ያወሳሉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና ከፍ ያለ ሚና እንደተጫወተ የሚመሰክሩ በየአብያተ ክርስትያናቱና በየገዳማቱ ግድግዳዎች ላይ ፤ በኃይማኖታዊ ድርሳናት ውስጥ እንዲሁም በእንጨት ላይ የተሰሩ በርካታ ስዕሎች ለዘመን መደራረብ እጅ ሳይሰጡ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ የስነጥበብና ዲዛይን ትምህርትቤት የስነ ጥበብ ታሪክ መምህርና ተመራማሪው አበባው አያሌው 'ኧ ግሊምስ ኦፍ ኧ ስሪ ሚሊኒያ ኦፍ ኢትዮፒያን አርት' በተሰኘ ፅሁፋቸው እንደሚያስረዱት በሶስተኛው እና በአራተኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አካባቢ የቅድመ ክርስትና ስነ ጥበባዊ ስኬት ተመዝግቦ ነበር።

በወቅቱ የአክሱም ስርወ መንግስት በአገር ውስጥና ከሌሎች የውጭ አገራትም ጋር የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች እጅጉን ስኬታማ መሆኑ በተለይም ለኪነ ሕንፃና ለቅርፃ ቅርፅ ባለሞያዎች ከፍተኛ ድጋፍ ችሮታል።

በ4ኛው ምዕተዘመን ክርስትና የአክሱም መንግስታዊ ኃይማኖት ሊሆን ከበቃ በኋላ ግን ለሙታን መታሰቢያ የሚሆኑ ምስለ-ቅርፆችን እና ግዙፍ ሃውልቶችን ማቆም አንድም ከእምነቱ አስተምህሮ ጋር የሚፃረር ሆኖ በመታየቱ፤ በተጨማሪም የአረማዊ ዘመን ልማድ ተደርጎ በመቆጠሩ የቅርፃ ቅርፅ ጥበብ እየከሰመ ሲመጣ በፋንታው ክርስቲያናዊ ስነ-ስዕል አብቧል።

ነገር ግን በአክሱም ዘመን ከተሰሩት ክርስትያናዊ ስዕሎች ብዙዎቹ በተደጋጋሚ የአብያተ ክርስትያናትና የገዳማት እድሳት ምክንያት ጠፍተዋል።

ከቅድመ ክርስትያናዊ የጥበብ ስራዎች መካከል እስካሁን ያለው ትክክለኛነቱ የተረጋገጠው ብቸኛ ስዕል የአቡነ ገሪማ የወንጌሎች የድርሳን ውስጥ ምስል ነው።

Image copyright ABEBAW AYALEW
አጭር የምስል መግለጫ ጎንደር የሚገኘው የደብረብርሀን ስላሴ ቤተክርስቲያን ስዕሎች

(እ.ኤ.አ ከ1150 እስከ 1270)የነበረው የዛግዌ ስርወ መንግስት በስነ ጥበብ፣ በኪነ ሕንፃ እንዲሁም በስነ ፅሑፍ የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱን የታሪክ ሊቃውንት እንዲሁም የተለያዩ ድርሳናት የሚመሰክሩ ሲሆን፤ ክርስትያናዊ ስዕል አብሮ በልፅጎ እንደነበርም ከመውደም የተራረፉ የግድግዳ ላይ ስዕሎች እንደሚመሰክሩ የአበባው ፅሁፍ ያሳያል።

በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ይበልጡኑ እየተስፋፋ በመጣበት ከ14ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ የቁም ጽሕፈት፣ ክርስትያናዊ ስነ ጽሑፍ እንዲሁም ስነ ስዕል አብረው ዳብረዋል።

የኢትዮጵያ ስነ ጥበባዊ ትውፊት ባልተቋረጠ ቅብብሎሽ ከዘመን ዘመን ለመቀጠሉ አንደኛው ምክንያት በየጊዜው የሚነሱትን ፈተናዎች ተቋቁማ ኢትዮጵያ እንደአገር መቀጠል መቻሏ ነው ሲሉ ፖላንዳዊው የስነ ጥበብ ታሪክ እና የስነ ስብ ተመራማሪ ስታኒስላቭ ኮይናትስኪ 'ኢትዮፒያን አይከንስ' በተባለው መጽሐፋቸው ያትታሉ።

ምንም እንኳ ከቀረው ዓለም ክርስትያናዊ ስነ ስዕል ጋር የይዘትና የቅርፅ ተመሳሳይነትን መያዙ ባይቀርም፤ የኢትዮጵያ ክርስትያናዊ ስነ ስዕል የራሱ ልዩ መገለጫዎችም አሉት።

ኮይናትስኪ በየጊዜው ከምዕራባዊውም ከምስራቃዊውም ዓለም ጋር ያዳበረቻቸው የቻለ ግንኙነት አሻራውን የቤተ ክርስቲያን ስነ ስዕል ላይ ማሳረፉን ይጠቅሳሉ።

ለዚህም በምሳሌነት የግሪክ፣ የኮፕት (የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን)፣ የኑቢያ እንዲሁም የአርመን ዱካዎች መስተዋላቸውን በአስረጅነት ይጠቅሳሉ።

ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ እውነታ እና በከፊልም በእርሱ ላይ ተመስርቶ ለምዕተ ዓመታት ያህል ከቅርብ የአፍሪካ አገራት እንኳ ተነጥላ መቆየቷ በመሰረታዊነት የራሷ የሆነ ልዩ ቤተ ክርስቲያናዊ የአሳሳል ጥበብን ታዳብር ዘንድ አስችሏታል።

ለምሳሌም በምዕራብ፣በመካከለኛውና በደቡባዊ አፍሪካ የስነ ቅርጽ ጥበብ በዋናነት ተመራጭ የስነ ጥበብ ዘርፍ ሲሆን የኢትዮጵያ ክርስትያናዊ ስነ ጥበብ ግን ዐብይ መገለጫው ስነ ስዕል ነው።

Image copyright ABEBAW AYALEW
አጭር የምስል መግለጫ ጎንደር የሚገኘው የደብረብርሀን ስላሴ ቤተክርስቲያን ስዕሎች

ቅዱስ ቀለማት

ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስነ ስዕል ልዩ መልኮች አንደኛው አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቀለማት ግልጋሎት ላይ መዋላቸው ነው።

ከጥቁርና ነጭ ቀለማት በተጨማሪ ሰማያዊ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ብቻ ለስዕል ስራ ይውላሉ።

የአበባው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው እነዚህ ቀለማት እንደቅዱስና መለኮታዊ ቀለማት ይቆጠራሉ።

እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀለማት በየአካባቢው ከሚገኙ ዕፆች ተጨምቀው ይሰሩ የነበረ ሲሆን ሰማያዊ ደግሞ ከውጭ አገራት እንዲመጣ ይደረግ ነበር።

ጥልቀት አልባነት እና የጀርባ ከባቢ ያለመኖር

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስነ ስዕል ውስጥ ጥልቀት፣ ርቀትና ቅርበት እንዲሁም የጀርባ ከባቢን የሚያሳይ ገጽታ ማየት ያልተለመደ ሲሆን ስዕሎቹም ባለ ሁለት አውታር ብቻ ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን "ቅርጽን ሳይሆን ኃሳብን" ነው የሚስሉት ሲሉ በሌላኛው 'ሜጀር ቲምስ ኢን ኢትዮፒያን ፔይንቲንግ ' መጽሐፋቸው የሚያስረዱት ኮይናትስኪ እንዲህ የሆነበትን ምክንያት ሲተነትኑ ለግለሰባዊ ስብዕና በአውሮፓዊያን የሚቸረውን ያህል አፅንዖት ስለማይሰጥ ነው ይላሉ።

Image copyright ABEBAW AYALEW
አጭር የምስል መግለጫ ደብረማርቆስ የሚገኙ የቤተክርስቲያን ስዕሎች

የእይታ ቅብብሎሽ

በኦርቶዶክሳዊው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የስዕል ጥበብ ተመልካቹ ስዕሉን የሚያየውን ያህል ስዕሉም ተመልካቹን ያያል ተብሎ ይታመናል።

ይህም ሁኔታ ስዕሎች ኃይል እንዳላቸው እንዲታሰብ አስችሎታል።

የሌሎች ምስራቃዊ አብያተ ክርስትያናትን ያህል የቅዱሳን ምስሎች አምልኮ ባይኖርም በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ምስሎች ለጸሎት እንደሚያገለግሉ ኮይናትስኪ ይገልፃሉ።

ለቅዱሳን ስዕል የሚሰጥ የገዘፈ ክብር ከሚስተዋልባቸው መንገዶች አንዱ ምስሎቹ የሚቀመጡበት ሁኔታ ነው፤ እንደአብነት ከቅድስት ማርያም ወይንም ከስቅለት ስዕሎችን ጨርቅ የሚደረግ መሆኑን ልብ ማለት ይቻላል።

Image copyright ABEBAW AYALEW
አጭር የምስል መግለጫ ደብረማርቆስ የሚገኙ የቤተክርስቲያን ስዕሎች

የሰው ፊት አቀማመጥ

የቤተ ክርስቲያን ምስሎች ባለሶስት አውታር ካለመሆናቸውም በላይ እንቅስቃሴ አይኖራቸውም። ብዙ ጊዜ ሰዎች፣ ቅዱሳን እና የመሳሰሉት ሲሳሉ እንቅስቃሴ አልባ ሆነው ነው።

አልፎ አልፎ ብቻ ፈረስ ጋላቢ ቅዱሳን በተወሰነ ድርጊት ውስጥ ሆነው ይታያሉ።

እንቅስቃሴንና አቅጣጫ በዓይን ውርወራ ወይንም የምልከታ አቅጣጫ ብቻ ይመላከታሉ።

የሰው ልጅ ፊት ሶስት ዓይነት ብቻ አቀማመጦች ይኖሩታል።

ቅዱሳን እና ፃድቃን ሙሉ በሙሉ ፊት ለፊት ሆነው ወይንም ሁለት ሶስተኛው ፊታቸው እየታየ ይሳላሉ።

ይህ የሚሆንበት ምክንያት ምስሉ በተመልካቹ ላይ ኃይሉን እንዲፈነጥቅ ከማሰብም በመነሳት ነው።

ኃጥኣን እና እርኩሳን ደግሞ ፊታቸው የጎንዮሽ ወይም አንድ አይናችው ብቻ እንዲታይ ይደረጋል።

Image copyright ABEBAW AYALEW
አጭር የምስል መግለጫ ደብረሲና ጎርጎራ የሚገኙ የቤተክርስቲያን ስዕሎች

ያልታወቁ ሰዓሊያን

በድርሳናት ውስጥ የሚሳሉ ስዕሎች ላይ የሰዓሊያን ስም ሰፍሮ የሚገኝባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

ይሁንና ኃይማኖታዊ ስዕሎችን መስራት እንደኃይማኖታዊ ተግባር ስለሚቆጠር የሰዓሊያን ስም እምብዛም አይገኝም።

ብዙ ጊዜም ሰዓሊያን የአብያተ ክርስትያናትን ግድግዳዎች በኃይማኖታዊ ስዕሎች እንዲያስውቡ ስራ ሲሰጣቸው ተግባራቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ ሱባዔ ገብተው መንፈሳዊ አመራርን ይሽታሉ።

ተያያዥ ርዕሶች