ባለፈው ዓመት በመንግሥት የተገባው ቃል ከምን ደረሰ?

ወጣቶች በሥራ ላይ Image copyright Michael Gottschalk

ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ከህዝብ በኩል ከባድ የሚባሉ ፈተናዎች ገጥሞታል። የመጀመሪያውና ድርጅቱ ክፉኛ የፈተነበት የ1997ቱ ምርጫ ነበር።

ሁለተኛውና ገና ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ያላገኘው ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው ተቃውሞ ነው።

ይህንን ሃገር አቀፍ የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት መንግሥት መዘጋጀቱን ያበሰረው በፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ባለፈው ዓመት የምክር ቤት የመክፈቻ ንግግር ላይ ነበር። "ለመሆኑ መንግሥት ቃሉን በተግባር ተርጉሟል?" የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።

መንግሥትን ወክለው መስከረም 30/2009 ዓ.ም ለሁለቱ ምክር ቤቶች ሰፊ የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የህዝቡ ጥያቄ ለመፍታት አንዳንድ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን ጠቁመው ነበር።

''ችግሮቻችንን መላ የሃገራችንን ሕዝቦች በሚያረካ ደረጃ ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ በዝርዝር ልንመክርባቸው ይገባል'' በማለት።

በዚህም መሠረት ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ህዝብን ከጫፍ እስከ ጫፍ አስለቅሷል ያሉትን የፍትህና የመልካም የአስተዳደር ችግሮች፣ እንዲሁም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ እና ሌሎች የፖለቲካ መብቶችን ለማስከበር መንግሥት አበክሮ እንደሚሰራ ቃል ገብተው ነበር።

በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የቀረበው የመፍትሄ ሃሳብና በተቃዋሚዎችና በፖለቲካ ተንታኞች የቀረበው አማራጭ ልዩነት ነበረው።

10 ቢዮን ብር "ማስታገሻ"?

ኢህአዴግ በመጀመሪያዎቹ የተቃውሞ ወራት ችግሩን ወደ ውጪ የመግፋት አዝማሚያውን በማቆም፤ የወጣቶቹ ጥያቄ አግባብነት ያለውና አጠቃላይ የፖለቲካ ነፃነት ማነስ ውጤት መሆኑን፤ እንዲሁም ችግሩ የሁለት ክልሎች ብቻ ሳይሆን ሃገር አቀፍ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አምነው ተቀብለዋል።

ወጣቶች የሚገኙበትን ሁኔታ በትክክል መገንዘብና ለችግራቸውም ሆነ ለጥያቄዎቻቸው የሚመጥን መሠረታዊ መፍትሔ ማቅረብ አጣዳፊ እንደነበር ፕሬዝዳንቱም ጠቁመዋል፡፡

አብዛኛው ወጣት በገጠር የሚገኝና መሬት አልባ በመሆኑ ገጠርን እየለቀቀ ወደ ከተማ እንዲፈልስ ተገዷል። ፕሬዝዳንቱ ይህን የወጣቶች ጉዳይ አፅንኦት ሰጥተው መፈታት አለባቸው ካሏቸው ግንባር ቀደም ችግር መካከል አስቀምጠውት ነበር።

በዚህ ረገድ መንግሥት በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚሁ ተግባር ብቻ የሚውል አሥር ቢሊዮን ብር መመደቡ ይታወሳል።

ለአፈፃፀሙም ይህ የወጣቶች ፈንድ በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በኩል ለክልሎች እንዲከፋፈል ተደርጓል።

በአጠቃላይ በገጠር 1.7 ሚሊዮን በከተማ ደግሞ 1.5 ሚሊዮን ወጣቶች ከዚሁ አዲስ ፈንድ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እቅድ ተይዞ ነበር።

ከተዘዋዋሪ የወጣቶች ፈንድ አተገባበር ጋር ተያይዞም ብድር የሚያቀርቡ ተቋማት አቅም ማነስ የአመራር ችግር እንደነበር ይነገራል።

በአጠቃላይ የተቀረፀው ዕቅድ ከምን እንደደረሰ የቅርብ ጊዜ መረጃ ባይገኝም፤ ጥያቄዎች ግን አሁንም እየተነሱ ናቸው።

"ከመጀመሪያውም ችግሩ ተፈትሾና ተመርምሮ የረዥም ጊዜ መፍትሄ አልነበረም የቀረበው" የሚሉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ፤ "መፍትሄው ጊዜያዊ ማስታገሻ ነበር" በማለት ተግባራዊነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባው ከመነሻው እንደነበር ያመለክታሉ።

"በተመደበው በጀት የወጣቱ ህይወት መሻሻሉን የሚያሳይ ምንም ምልክት የለም" በማለት አቶ ሙሼ ይናገራሉ።

"ግማሽ ያህሉ እንኳን ጥቅም ላይ አልዋለም" የሚሉት የመድረክ መስራችና አመራር አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፤ ወጣቶች በተለይ አንዳንድ ቦታ ብድር ለማግኘት 20 በመቶ እንዲያስይዙ የሚጠይቀው አሰራር ልክ እንዳልነበረ ይናገራሉ። እንዲሁም ኢህአዴግ በራሱ የፖለቲካ ጉዳይ ተጠምዶ ለዚህ ጉዳይ በቂ ትኩረት አልሰጠውም ይላሉ።

በተጨማሪም "ሲጀመር ትክክለኛ መፍትሄ አልነበረም፤ ማስታገሻ እንጂ" የሚሉት አቶ ገብሩ፤ የወጣቶች ጥያቄ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን በነፃነት ተንቀሳቅሰው የሚሰሩበት ሁኔታ ማግኘት እና ለተሻለ ዕድል የሚያበቃ ትምህርት ማግኘት ቢሆንም "ዛሬ ትምህርት ቤቶች ጊዜ ማሳለፊያ ነው የሆኑት" ይላሉ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ

"ጥልቅ" ተሃድሶ?

ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ በመንግሥትና በድርጅቱ ውስጥ መሠረታዊ ጥልቅ ተሃድሶና የአወቃቀር ለውጥ እንደሚደረግ ቃል ገብተው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንቱ በገቡት ቃል መሠረት ኢሕአዴግ ለበርካታ ወራት በዝግ ከፍተኛ ግምገማ አድርጎ ነበር፡፡ በተናጠልም አባል ድርጅቶቹ በየፊናቸው ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ እስከ ታችኛው የአመራር እርከን ድረስ ተገማግመዋል።

ብዙ ብዙ ቢባልም "በተግባር ግን የነበረውን አካሄድ ለመለወጥ ያደረገው ነገር የለም ይላሉ" አቶ ገብሩ ኣስራት።

የፌዴራል መንግሥትም ካቢኔውን እንደ አዲስ በማዋቀር በርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ወደ ከፍተኛ ሥልጣን አምጥቷል።

አቶ ሙሼ ምሁራን ወደ ሹመት መምጣታቸውን በራሱ አልተቃወሙትም። ስም እየጠቀሱ አንድ ሰው በሦስት የተለያየዩ የሚኒሰቴር ቦታዎች ላይ ሲቀያየር ማየታቸው፤ ድርጅቱ አቅመ ቢስ ሆኖ መቅረቱን እና ሰው አለማብቃቱን ማሳያ መሆኑን አመላካች ነው ይላሉ።

"መንግሥትን መልሶ የማደራጀት ሥራ አይጠላም" የሚሉት አቶ ሙሼ፤ "ሃገሪቱ ሌላ ብቁ ሰው የላትም ወይ?" በማለት ይጠይቃሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀሰቀሰው አመፅ የብዙ ውስብስብ ችግሮች ውጤት በመሆኑ ህዝቡ በጉዳዩ ላይ በነቂስ ወጥቶ በግልፅ መነጋገር ያለበት ጉዳይ እንጂ የአንድ ድርጅት ጉዳይ እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ሙሼ፤ "እራስን ስልጣን ላይ ለማቆየት የሚደረግ እንቅስቃሴ አይጠቅምም፤ ይህ አካሄድ ሃገሪቷን ብዙ ዋጋ ሊያስከፍላት ይችላል'' በማለት ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

ሃገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ ኢህኣዴግ እንደሚለው የቢሮክራሲ ችግር እንዳልሆነ የሚያምኑ አቶ ገብሩ፤ የፖሊሲና የርዕዮተ ዓለም ለውጥ እንዲደረግ ይጠይቃሉ።

"አሳሪና ታሳሪ አይደራደሩም"

ግንቦት 2007 ዓ.ም በተካሄደው አምስተኛው ዙር ሃገራዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ማሸነፉን ያወጀው ኢህአዴግ፤ ይህንን ተከትሎ መንግሥት በመሰረተበት ማግስት ነበር በኦሮምያ ክልል አመፅ የተቀሰቀሰው። ከዚያም ወደ አማራ ክልል ተዛምቷል።

ይህ በሁለቱ ትልቅ የህዝብ ቁጥር ባላቸው ክልሎች የተቀሰቀሰው አመፅ መነሻው የመልካም አስተዳደር ጉድለት ነው ሲል መንግሥት፤ እንደእነ ጄነራል አበበ ተክለሃይማኖት ዓይነት የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ፤ "ለረዥም ጊዜ የተጠራቀመው የፖለቲካ ነፃነት ማጣት ውጤት" በማለት ያስቀምጡታል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ተቃዋሚዎችን የመረጠው የኅብረተሰብ ክፍል ድምፅ አለመወከሉ የምርጫ ሕጉ ላይ ክለሳ ማድረግን እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ነበር፡፡

ይም ብቻ ሳይሆን፤ አፋኝ የተባሉ ሌሎች ሕጎች ማለትም የፕሬስ ሕጉ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ሕግ እንዲሁም ፀረ ሽብር አዋጁ እንደሚሻሻሉ ተስፋ ተደርጎ ነበር።

መንግሥት ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መደራደር እንደ መፍትሄ ይዞት የነበረ ሲሆን ቁጥራቸው 20 ከሚደርሱ ጋር ድርድር ማድረግ ጀምሮም ነበር።

ሆኖም ድርድር የተባለው ገና ከመነሻው መግባባት የራቀው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ተጠቃሽ ከሆኑት ፓርቲዎች መካከል መድረክ፣ ሰማያዊ እና መኢአድ ከሂደቱ ወጡ።

"እነዚህ እነማን ናቸው የሚደራረደሩት? የትኛውን ህዝብ ይወክላሉ?" በማለት የሚጠይቁት አቶ ሙሼ፤ ከሂደቱ የሚጠብቁት ምንም ነገር እንደሌለ ገልፀዋል።

ቀደም ሲል ሌላ ቀርቶ ሕገ-መንግሥቱን እስከማሻሻል ቃል ገብቶ እንደነበር አስታውሰው፤ ሁኔታው የተረጋጋ ሲመስል ገዢው ፓርቲ በራሱ ሜዳ እየተጫወተ እንደሆነ ይናገራሉ።

ፓርቲያቸው መድረክ ከስድስትጊዜ በላይ በድርድሩ እንደተሳተፈ የሚናገሩት አቶ ገብሩ በበኩላቸው፤ በርካታ አባሎቻቸው በእስር ላይ ሆነው በአሳሪና በታሳሪ መካከል ድርድር አስቸጋሪ እንደሆነ ያስረዳሉ።

"መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ስናነሳ ቆይተናል፤ አሁን ቀውሱ የተቀዛቀዛ ሲመስል ኢህአዴግ ፊቱን እያዞረ ነው" በማለት ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

ተያያዥ ርዕሶች