በማዕከላዊ አሜሪካ አውሎ ነፋስ 22 ሰዎችን ሲገድል ቀጣይ አቅጣጫውን ወደ ሜክሲኮ እና አሜሪካ አድርጓል

አውሎ ንፋስ በኮስታ ሪካ ያሰረሰው ጉዳት Image copyright Reuters

በማዕከላዊ አሜሪካ ኔት ተብሎ የተሰየመው አውሎ ነፋስ በኮስታ ሪካ፣ በኒካራጓዋ እና በሆንዱራስ ቢያንስ 22 ሰዎችን ገድሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ካወደመ በኋላ አቅጣጫውን ወደ ሜክሲኮና አሜሪካ አድርል።

በማዕከላዊ አሜሪካ የሚገኙ ሃገራት 20 ሰዎች የገቡበት ከጠፋ በኋላ አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ አውጀዋል።

ከፍተኛ ዝናብ የቀላቀለው አውሎ ነፋስ የመሬት መንሸራተት እና ጎርፍ በመፍጠሩ መንገዶች ተዘግተዋል፤ ድልድዮች ተንደዋል፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ፈራርሰዋል።

በኮስታ ሪካ 400ሺ የሚሆኑ ሰዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሲቋረጥባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ።

በኮስታ ሪካ ቢያንስ 6 ፣ በኒካራጓዋ ደግሞ 11 ሰዎች ህይታቸውን አጥተዋል። በሆንዱራስ 3 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ በርካቶች የገቡበት አልታወቀም።

Image copyright Reuters

ሃሙስ በኮስታ ሪካ የባቡር ጉዞ እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን በርካታ በረራዎችም ተሰርዘዋል።

አውሎ ነፍሱ በኒካራጓዋ በመሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን አስከትሏል።

የአየር ትንበያ እንደሚያሳየው ከሆነ ኔት አቅሙን በማጠናከር 'ደረጃ አንድ አውሎ ንፋስ' በመሆን እሁድ የአሜሪካን ደቡባዊ የባህር ዳርቻዎች ይመታል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ