የሩስያ ወታደሮች 'ሰልፊ' እንዳይነሱ ሊታገዱ ነው

Russian sailors take selfies in the naval base at Sevastopol, Crimea Image copyright AFP

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ወታደሮቹ 'ሰልፊ' በሥራ ላይ ሳሉ እንዳይነሱ የሚያዝ ሕግ አርቅቋል።

ረቂቁ ፎቶዎች፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንዲሁም ማንኛውም ወታደራዊ ይዘት ያላቸው ጽሁፎች በይነ-መረብ ላይ እንዳይጫኑ ያዛል።

አቅጣጫ ጠቋሚ ቴክኖሎጂዎች ወታደሮቹ ያሉበትን ቦታ ለጠላት አሳልፈው ሊሰጡ ይችላል ሲል ረቂቁ አፅንኦት ይሰጣል።

የሩሲያ ወታደሮች ፎቶ ተነስተው በተለያዩ መንገዶች ካሰራጯቸው ምስሎች በመነሳት ሃገሪቱ በዩክሬይን እና በሶርያ ጦር ማዝመቷን ማወቅ ተችሏል።

ለምሳሌ በፈረንጆቹ 2014 አንድ የሩሲያ ወታደር፤ ሮኬቶችን በሩሲያ ለሚደገፈው የዩክሬይን አማፂ ቡድን አድርሶ መምጣቱን የሚጠቁም ፎቶ ለጥፎ ነበር። ይህንንም የቢቢሲዋ ሚሮስላቫ ፔትሳ በትዊተር ገጿ ላይ አስፍራዋለች።

መጋቢት 2014 ላይ ሩሲያ ክሬሚያን ከወረረች ከጥቂት ወራት በኋላ የዩክሬይን አማፂ ቡድን የሃገሪቱን ምሥራቃዊ ክፍል መቆጣጠሩ የሚታወስ ነው።

ምዕራባዊያን ሩሲያን የዩክሬይን አማፂ ቡድንን ከባድ የጦር መሣሪያ በማቅረብ ትደግፋለች በማለት ይወቅሱ እንደነበር ይታወሳል። ሩሲያም አንዳንድ ወዶ ገቦች ያግዙ ይሆናል እንጂ ከባድ የጦር መሣሪያ አላስታጠኳቸውም ስትል አስተባብላ እንደነበርም አይዘነጋም።

የቫይስ ኒውስ ጋዜጠኛ ሳይመን ኦስትሮቭስኪ በዩትዩብ ገጹ፤ የሩሲያ ወታደሮች በይነ-መረብ ላይ የሚለጥፉትን ፎቶ በመከታተል የሩሲያን በዩክሬይን ያላትን ቀጥታ ጣልቃ ገብነት ማረጋገጥ መቻሉን የሚያሳይ ምሰል ጭኖ ነበር።

በነሐሴ 2014 ደግሞ ሌላ ጋዜጠኛ የሩሲያ ወታደሮችን የማህበራዊ ድረ-ገጽ ፎቶዎች በመከታተል 76ኛው የሩሲያ አየር ኃይል ክፍል ጉዳት እንደደረሰበት እና ፒስኮቭ በምትባለው የምዕራብ ሩሲያ ክፍል እንደሚገኝ ማረጋጥ ችሏል።

ከሩሲያ የጦር ክፍል ውስጥ ሁለት ክፍሎች ወታደሮቻቸው በይነ-መረብ ላይ ማንኛውም ዓይነት ወታደራዊ ፍንጭ ሊሰጥ የሚችል ፎቶ እንዳይለጥፉ ሙሉ በሙሉ አግዷል።

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከጥር 2018 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር ይጠበቃል።

ተያያዥ ርዕሶች